ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ በስደተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ተከትሎ ናይጄሪያ ዜጎቿን ልታስወጣ ነው
የናይጄሪያ መንግሥት፤ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ የተነሳ 130 ገደማ ዜጎቹ በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን አስታወቀ።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተፈጠረው ጥቃት ሊባባስ ይችላል በሚል ስጋት በተጀመረው በዚህ አሠራር ለመውጣት የሚመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቢያንካ ኦዱምግዉ ኦጁክዉ የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚዎች በውጭ ዜጎች ላይ የሚያደርሷቸውን ጥቃቶች ያወገዙ ሲሆን፣ "መጤ ጠል ትርክት፣ የጥላቻ ንግግር እና አቀጣጣይ ፀረ ስደተኛ መግለጫዎች" ታይቶባቸዋል ያሏቸውን ሰልፎችንም ኮንነዋል።
ሚኒስቴሩ የናይጄሪያውያን ዜጎች ደኅንነትን በተመለከተ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጠርቶ ማነጋገሩን አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር በበኩላቸው ዛሬ ሰኞ ከናይጄሪያ አቻቸው ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ያደረጉት ንግግር ፍሬያማ እንደነበር ተናግረዋል። ዜጎቿ ላይ ትኮሳ የተፈጸመባት ጋናም ባለፈው ወር ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳ ነበር።
በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች የሚካሄደውን ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ባለሥልታናት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እየተደረገባቸው ነው።
በተለያዩ የፀጥታ ኃይሎችን የተሳተፉባቸው ክስተቶች ሁለት ዜጎቿ የተገደሉተት ናይጄሪያ እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀች ሌላኛዋ አገር ሆናለች።
ለተገደሉት ዜጎች ፍትሕ እንዲሰጥ የጠየቀው የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ይህንን "የመጤ ጠል ጥቃት" በተመለከተ ከደቡብ አፍሪካ ጋር እየሠራ በመሆኑ በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎቹ እንዲረጋጉ ጠይቋል።
ባለሙያዎች ግን በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ ወደ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ እና የአጸፋ እርምጃ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሰላሳ በመቶ ገደማ የሚሆኑት ዜጎች ሥራ አጥ በሆኑባት ደቡብ አፍሪካ ውጥረቶች የሚከሰቱ ሲሆን አንዳንዴም አፍሪካውያን ስደተኞችን ዒላማ ያደረጉ ተቃውሞዎች ይነሳሉ።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የተቃዋሚዎችን ሕገ ወጥ ድርጊቶች ኮንነው፤ አገሪቱ ውስጥ ያለውን ከስደተኞች ጋር የተያያዘ ችግር እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል ውስጥ በነበረችበት ወቅት ያደረጉት እገዛ እውቅና እንዲሰጠው ይፈልጋሉ።