ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና የርችት ፋብሪካ ላይ ባጋጠመ ፍንዳታ 21 ሰዎች ሲሞቱ፤ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ታዘዙ
በቻይናዋ ሁናን ግዛት ውስጥ በሚገኝ የርችት ፋብሪካ ላይ በደረሰ የፍንዳታ አደጋ 21 ሰዎች መሞታቸውን እና ሌሎች 61 ደግሞ መጎዳታቸውን የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ሉያንግ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሁአሼንግ በተባለው የርችት ማምረቻ ፋብሪካ ላይ አደጋው የደረሰው በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት 40 ደቂቃ አካባቢ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ሠራተኞች በፋብሪካው ሦስት ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ከስፍራው ለቅቀው እንዲወጡ አዘዋል።
የቻይና ባለሥልጣናት አደጋውን ተከትሎ 500 የሚሆኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በማሰማራት ሰዎችን እንዲያድኑ እና የተጎዱትን እንዲያክሙ ከማሰማራታቸው በተጨማሪ፣ በሕንጻው ፍርስራሽ ውስጥ መውጫ ያጡ ሰዎችን ለማግኘት ሮቦቶችንም እየተጠቀሙ ነው።
በአደጋው ዙሪያ ምርመራ እያደረገ ያለው ፖሊስ የርችት ፋብሪካውን የሚመራውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የቻይና መንግሥት መገናና ብዙኃን ዘግበዋል።
አደጋው በደረሰበት የፋብሪካው ውስጥ የሚገኙ ሁለት የተቀጣጣይ ባሩድ ማከማቻ መጋዘኖች እየተደረገ ባለው የነፍስ አድን ጥረት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀናቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የነፍስ አድን ቡድኖች ፍንዳታው በደረሰበት ፋብሪካ በሦስት ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ እያደረጉ ሲሆን፣ ሌሎች ፍንዳታዎች እንዳይከሰቱ የሚያደርጉ እርምጃዎችን በአካባቢው ላይ እየወሰዱ ነው።
በርችት ፋብሪካው ላይ የደረሰው ፍንዳታ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር ከባድ ውድመትን ያደረሰ ሲሆን፣ በአቅራቢያ የሚገኙ የመኖሪያ ሕንጻዎች የመስኮት መስታዎቶች ተሰባብረዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በ20ዎቹ እና በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም በፍርስራሾቹ በደረሰባቸው ጉዳት የአጥንት መሰባበር የገጠማቸው ሰዎች እንዳሉ ተዘግቧል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አስካሁን በአደጋው ምክንያት የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን የማግኘቱ ሥራ እንዲቀጥል አዝዘዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ በፈንዳታው ላይ ምርመራ ተደርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
አንድ ፍንዳታው ከደረሰበት ፋብሪካ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ግለሰብ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው መንገዶች ፍንዳታው በፈጠረው ፍርስራሽ በመዘጋታቸው ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም ተገድደዋል።
"የቤቶቻችን የመስኮት መስታወቶች ተሰባብረዋል፣ የመስኮቶች የብረት መቃኖች ተጣመዋል፣ ከጠንካራ ብረት የተሠሩ በሮች ሳይቀሩ ተጣመው ጉዳት ደርሶባቸዋል" በማለት ፍንዳታው በአካባቢው ያስከተለውን ጉዳት ገልጾታል።
ሌለ ነዋሪ ደግሞ ፍንዳታው በፈጠረባት ፍርሃት ምክንያት የመኖሪያ መንደሯን ለቅቃ ለመሸሽ መገደዷን ተናግራለች።
አደጋው የደረሰባት ሉያንግ ከተማ በርችት ምርቷ የምትታወቅ ሲሆን፣ አንዳንድ ዘገባዎችም የዓለም ትልቋ የርችት አምራች በማለት ይገልጿታል።
በቻይና ውስጥ በርችት ፋብሪካዎች እና መሸጫዎች ላይ የሚከሰቱ ፍንዳታዎች ያልተለመዱ ካለመሆናቸው በተጨማሪ ካባድ ጉዳትን በሰው እና በንብረት ላይ የሚያደርሱ ናቸው።
ባለፈው የካቲት ወር ሁቤይ በተባለችው ግዛት ውስጥ በሚገኝ የርችት መሸጫ ላይ በደረሰ ፍንዳታ 12 ሰዎች መሞታቸው የታወሳል።