ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በዋስ እንዲለቀቅ ለሦስተኛ ጊዜ ቢወሰንም በእስር ላይ መሆኑ ተገለጸ
የ'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ተከብሮ ከእስር እንዲፈታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት ሐሙስ፣ ሰኔ 5/ 2017 ዓ.ም. ወሰነ።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዛሬ ውሎው የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን የጋዜጠኛው በዋስ ይለቀቅ ውሳኔ ማጽናቱን ጠበቃው አቶ ቤተማሪያም አለማየሁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጋዜጠኛው ለሦስተኛ ጊዜ በዋስ ከእስር እንዲፈታ በፍርድ ቤቶች ቢወሰንም መግለጫው እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ከእስር አለመፈታቱን ጠበቃው ተናግረዋል።
ፖሊስ በጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ሐሙስ የተሰየመው የሰበር ሰሚ ችሎት "ይግባኝ ያስቀርባል" ወይስ "አያስቀርብም" የሚለውን ከመረመረ በኋላ የፖሊስ ማመልከቻን ውድቅ ማድረጉን መግለጫው አመልክቷል።
በሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ፖሊስ ጋዜጠኛው በእስር ቆይቶ ምርመራ እንዲደረግና የዋስትና መብቱ ሊፈቀድ አይገባም በሚል ካቀረበው የጽሁፍ ክርክር በተጨማሪ በቃልም ቅሬታውን እንዲያሰማ መደረጉን ጠበቃው ያስረዳሉ።
ጠበቃው ደንበኛቸውን በተመለከተ ስላልተጠየቁ ምንም አይነት መከራከሪያ ባያቀርቡም ፖሊስ የማጣሪያ ጥያቄዎች እንደቀረቡለት እንዲሁም የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ጭምር አስቀርቦ ፍርድ ቤቱ እንደመረመረ ይገልጻሉ።
ይህንንም ተከትሎ የስር ፍርድ ቤቶች ለጋዜጠኛው የዋስትና መብት መፍቀዳቸው "ምንም የተፈጸመ የህግ ስህተት የለም። ህግን በተከተለ አግባብ የተሰራ ነው" በሚል የፖሊስ የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አለማግኘቱን ጠበቃው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም መጀመሪያ እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ቀጥሎም ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ውስጥ በእስር ላይ ነው።
ደንበኛቸው በፍርድ ቤቶች ቢወሰንለትም በዋስ አለመለቀቁ "ኢ-ህገ መንግሥታዊ" እንደሆነ ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ደንበኛዬ የዋስትና መብቱ የተፈቀደለት ማክሰኞ፣ ሰኔ 3/ 2017 ዓ.ም ሲሆን ፖሊስ እሱን በእስር የሚያቆይበት አንዳችም ከህግ የሚመነጭ ስልጣን የለውም። አስሮም ይግባኝ የሚጠይቅበት ከህግ የሚመነጭ ስልጣን የለውም። ፖሊስ [የዋስትና መብቱ ከተፈቀደለት በኋላ] ደንበኛዬን የያዘውበህገወጥ መንገድ ነው። ይህ ተገቢ አይደለም። ኢ-ህገ መንግሥታዊ ነው ብለዋል።"
በእስር ላይ አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው ጋዜጠኛ ተስፋለም የቂርቆስ ምድብ ችሎት በ15 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ሰኔ 3/ 2017 ዓ.ም. ወስኖ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ በማለቱ ጉዳዩ ለአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ተመርቶ ነበር።
የይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰኔ 4/ 2017 ዓ.ም. ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት ጋዜጠኛው የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት በድጋሚ በይኗል።
ሆኖም ፖሊስ "የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሕግ ስህተት አለበት" በሚል አቤቱታውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ የፖሊስ ይግባኝ አቤቱታ "አያስቀርብም" በሚል መወሰኑን የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ባለቤት ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሐሙስ የተሰየመው ይህ የሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤቶቹ ጋዜጠኛው የዋስትና መብቱ ተከብሮ እንዲፈታ መወሰናቸው "መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት እና ሕግን የተከተለ ሆኖ ስላገኘው ውሳኔዎቹ እንዲጸኑ" ትዕዛዝ መስጠቱም ተገልጿል።
ተስፋለም በፍርድቤቶች የዋስትና መብቱ ከተፈቀደለት ጀምሮ " ፖሊስ ትዕዛዙን አክብሮ ይለቃል" ብለው ይጠበቁ እንደነበር የሚገልጹት ጠበቃው የነገውን ሁኔታ አይተው የዋስትና መብቱን ለፈቀደለት አካል አቤቱታ በማቅረብ በዚያ አግባብ እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።
"የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈጸም አለበት፤ ትዕዛዝ አልፈጽም እያለ ያለ አካል አለ። ያንን አካል ፍርድ ቤት አስገድዶ እንዲያስፈጽምልን መጀመሪያ ትዕዛዝ ለሰጠው አካል አቤቱታ እናቀርባለን" ሲሉ ቀጣይ ሂደታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ተስፋለም በአሁኑ ወቅት በአካላዊና በስነልቦናዊ ያለበት ሁኔታ እንዴት ነው? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ተስፋማሪያም ሲመልሱ በስነ ልቦና ደረጃ የመረበሽ ውስጥ እንዳልሆነ ገልጸው "ከዚህ ቀደም የሚያውቀው ሂደት ስለሆነ የመረበሽ ነገር አላየሁበትም" ይላሉ።
ተስፋለም በአካላዊ ሁኔታው ምንም የደረሰበት ጉዳት ወይም አያያዙ ላይ ጥሰት የለም ቢሉም "አላግባብ መታሰሩ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተስፋለም ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስ እንዲፈታ ትዕዛዝ በተሰጠበት ደብዳቤ ላይ "ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት" ተጠርጥሮ መያዙ ተጠቅሷል።
ተስፋለም በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
ጠበቃው አቶ ቤተማሪያም አለማየሁ፣ጋዜጠኛው ሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ግዮን ሆቴል በስልክ እያወራ ሳለ በደኅነንት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ከቀናት በፊት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"በዕለቱ በወላይታ ዲቻ እና በሲዳማ ቡና መካከል ይደረግ የነበረ እግር ኳስ ውድድር ስለነበር፣ ደጋፊዎች ስታዲዮም ገብተው መከታተል እንደማይችሉና ጨዋታው በዝግ ይካሄድ እንደነበር ቀደም ሲል ተዘግቦ ስለነበር በዚህ ዙሪያ ከጓደኞቹ ጋር በስልክ እያወራ በነበረበት ጊዜ ነው የተያዘው" ብለዋል።
የደኅንነት አባላቱ ተስፋለምን "ምንድን ነው የምታወራው? ከማን ጋር ነው የምታወራው?" በማለት ስልኩን ወስደው፣ ከዚህ ቀደም የተሠሩ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባዎች ስልኩ ላይ ስለነበሩ እሱን ተመልክተው እስጢፋኖስ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ ማቆያ ወስደው እንዳሰሩት ገልጸዋል።
የጋዜጠኛውን እስር የመብት ተቆርቋሪው አምነስቲ አውግዞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሰኔ 4/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
"ይህ ክስተት ባለሥልጣናት የሰዎችን የግል ሕይወት እና አስተያየቶችን የሚከታተሉበት አሳሳቢ አዲስ እውነታን የሚያንጸባርቅ ነው። የእሱ የዘፈቀደ እስር በአገሪቷ ውስጥ ጨቋኝ ልምምዶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ያሳያል" ብሏል።
የጋዜጠኞች የመብት ተቆርቋሪ ሲፒጄ በበኩሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጋዜጠኛ ተስፋለምን እንዲለቁት ረቡዕ፣ ሰኔ 4/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቅ ብያኔ ቢያስተላልፍም ጋዜጠኛው በእስር ላይ እንደሚገኝ ያስታወሰው ሲፒጄ "ፍርድ ቤት እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ተስፋለም ወልደየስ በእስር ላይ መቆየቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፍትህ ሂደቶች እና የፕሬስ ነጻነት ግድየለሽ መሆኑን ያሳያል" ሲሉ የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ አሳስበዋል።
የኢትየጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በበኩሉ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው የዋስ መብቱ ተጠብቆለት ከእስር እንዲለቀቅ ጠይቋል።
"ፖሊስ መምሪያው ጋዜጠኛ ተስፋለምን እንዲፈታ ትዕዛዝ የተሰጠበትን ደብዳቤ ባለመቀበል በድጋሚ የዋስትና መብቱን ጥሷል። ምንም እንኳን ፖሊስ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም፣ የጋዜጠኛው የዋስትና መብት ያለ አግባብ በመገደብ መሆን የለበትም" ብሏል።
አክሎም "ፖሊስ በፍርድ ቤት የተሰጠውን የዋስትና መብት በተደጋጋሚ ያለአግባብ መንፈጉን፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የጋዜጠኝነትን ሙያን ጫና ውስጥ የመክተት ተግባር አድርጎ ይመለከተዋል" ሲል አትቷል።
ተስፋለም ወደልደየስ ዜናና ትንታኔ የሚቀርብበት 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የተባለው ድረገጽ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ ገጹ በተለይ ወቅታዊ የፖለቲካ ዜናዎችን በማቅረብ እየታወቀ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ ያለ ነው።
ተስፋለም ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ታስሯል። ከሦስት ዓመት በፊት መስከረም 22/2014 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ለሦስት ቀናት እስር በኋላ የተለቀቀ ሲሆን፣ ከዓመታት በፊትም ከዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ጋር ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ቆይቷል።
ተስፋዓለም ከእስር ከወጣ በኋላ በኬንያና በኡጋንዳ ውስጥ በስደት በቆባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያን እና የአካባቢው አገራትን የሚመለከቱ ዜና እና የተለያዩ ፊቸሮች የሚቀርቡበት ጋዜጣ ያዘጋጅ ነበር።
ተስፋለም በአገር ውስጥ በሰብ ሰሃራን ኢንፎርመር፣ አዲስ ፎርቹን እና በአዲስ ነገር ጋዜጦች ላይ የሠራ ሲሆን ወደ ጀርመን በመሄድ የጀርመን ድምጽ የአማርኛው ክፍል ውስጥ ሲሰራ ነበር።
ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ኢትዮጵያ ኢንሳይደርን መሥርቶ እየሠራ ይገኛል።