ከሜክሲኮ ወደ ዩኬ በሚደረግ በረራ ላይ ተሳፋሪዎች በመደባደባቸው አውሮፕላኑ ለማረፍ ተገደደ

የቲዩአይ አየር መንገድ አርማ ያለበት ግዙፍ ሰማያዊ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሜክሲኮ ካንኩን ከተማ ወደ ለንደን ከተማ ሲበር የነበረ አውሮፕላን ሁለት ተሳፋሪዎቹ ድብድብ መጀመራቸውን ተከትሎ ጉዞውን ወደ አሜሪካዋ ሜይን ግዛት አዙሮ ለማረፍ ተገደደ።

አውሮፕላኑ ማክሰኞ ዕለት አቅጣጫውን ቀይሮ በአስቸኳይ በማረፉ በውስጡ የነበሩት 267 ተሳፋሪዎች በሙሉ ምሽቱን በሜይን ግዛት ባንጎር ከተማ ውስጥ እንዲያሳልፉ ተገደዋል።

አውሮፕላኑ ወደ የአሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ግዛት በደረሱበት ጊዜ የበረራው ሰራተኞች እረፍት ሳያደርጉ እንዲሰሩ የሚፈቀድላቸው የስራ ሰዓት አልፎ ነበር።

በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ ሌሎች ተተኪ ሰራተኞችን ለበረራው ያስመጣ ሲሆን በመጨረሻም አውሮፕላኑ በማግስቱ በረራውን ቀጥሏል።

ድብድብ የጀመሩት ሁለቱ ተሳፋሪዎች የወንጀል ክስ አልተመሰረተባቸውም። አልተመሰረተባቸውም። ይሁን እንጂ ሁለቱም "በተለያዩ ወደ በረራዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዲመለሱ" እንደተደረገ ተገልጿል።

ባለቤትነቱ የብሪታንያው ቲዩአይ አየር መንገድ የሆነው 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን፤ ረቡዕ ዕለት በለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ በሰላም አርፏል።

የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ተቋም (ሲቢፒ) ቃል አቀባይ፤ "ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ሲደረግ የነበረው በረራ ውስጥ ባጋጠመ ድብድብ ምክንያት የበረራ አቅጣጫውን ቀይሯል" ብለዋል።

"አውሮፕላኑ እንደደረሰ የሲቢፒ መኮንኖች ሁለቱንም ግለሰቦች ከአውሮፕላኑ አስወርደዋል። ምንም እንኳን የወንጀል ክስ ባይመሰረትም፤ ሲቢፒ ሁለቱንም ግለሰቦች በአፋጣኝ ከሀገር እንዲወጡ አድርጓል" ሲሉም አክለዋል።

አውሮፕላኑ በአስቸኳይ ከማረፉ በፊት አብራሪው ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ንግግር ሲያደርግ የተቀረጸ ድምፅ እንደሚያመለክተው፤ መሬት ላይ የነበሩ ባለስልጣናት አብራሪው ሜይን ውስጥ ለማረፍ ላቀረበው ጥያቄ ፈቃድ በመስጠት ወደ ማረፊያው የመሩት በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ነው።

አብራሪው፤ "ኮክፒቱ ደህንነቱ የተጠበቀ ሲሆን ሁለት ተሳፋሪዎች ግን እየተደባደቡ ነው፤ ሰራተኞች [ሁኔታውን] በቁጥጥራቸው ሥር አድርገውታል" በማለት ሁኔታውን ሲገልጽ ይደመጣል።

ከተወሰኑ ንግግሮች በኋላ በሜይን የነበረው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ፤ አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ጊዜ የደህንነት መኮንኖች እንደሚጠብቁት ለአብራሪው ተናግሯል።