የትራምፕ እንደገና መመረጥ ለዓለም ምን አንድምታ ይኖረዋል?

የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መንበሩ ሊመጡ ይችላሉ።

ትራምፕ ከተፎካካሪያቸው ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ያላቸው የድጋፍ ልዩነት ጠባብ መሆኑን ልብ ይሏል።

ማንም ያሸነፍ ማን ውጤቱ በዓለም ዙሪያ ተጽዕኖ አለው።ከአሜሪካ ባሻገር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ሕይወት ይነካል።

በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ስብሰባ ላይ የፓርቲው ዕጩ መሆናቸው የሚረጋገጠው ትራምፕ ስለ ዕቅዶቻቸው በዝርዝር መረጃ ሲሰጡ አይታይም።

ፖሊሲዎቻቸው ግን ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሚለዩባቸው ብዙ ዘርፎች እንዳሉ ግልጽ ነው። አንዳንዶቹን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

ዩክሬንን በመደገፍ ይቀጥላሉ?

ሩሲያ እአአ በ2022 ወረራ ከፈጸመች በኋላ ለዩክሬን የሚሰጠው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እና ወታደራዊ ድጋፍ በዶናልድ ትራምፕ ሲተች ቆይቷል።

በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የሩሲያው ፕሬሲዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በይፋ ያሞካሹት ትራምፕ፤ በድጋሚ ከተመረጡ “በ24 ሰዓታት ውስጥ” ጦርነቱን ለማስቆም ቃል ገብተዋል።

እንዴት እንደሚያሳኩት ግን አልገለጹም።ይህም ዩክሬን ግዛቶቿን አሳልፋ ለሩሲያ እንድትሰጥ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ወታደራዊ እርዳታን ጨምሮ ለኪዬቭ እንዲደርስ የተዘጋጀ 60 ቢሊዮን ዶላር በሪፐብሊካኖቸ ምክንያት ለወራት ከአገሪቱ ምክር ቤት የድጋፍ ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቶ ነበር።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ድጋፍ ሲያገኝ ግን ትራምፕ ብዙም አስተያየት አልሰጡም።

ከአጋሮቻቸው አንዱ የሆኑት የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በመጋቢት ወር ፍሎሪዳ ተገኝተው የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከጎበኙ በኋላ ትራምፕ ከተመረጡ ለዩክሬን “አንድ ሳንቲም አይሰጡም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ስለኦርባን አስተያየት ከታይም መጽሔት ጥያቄ የቀረበላቸው ትራምፕ “አውሮፓ እኩል ድጋፍ ካላደረገች በስተቀር አልሰጥም” ሲሉ መልሰዋል።

“ዩክሬንን ለመርዳት እሞክራለሁ” ቢሉም ግን አውሮፓም “ትክክለኛ ድርሻዋን እየተወጣች አይደለም” ብለዋል።

ወታደራዊ እርዳታን ማቋረጥ ከሪፐብሊካን መራጮች ጋር ይያያዛል። በግንቦት ወር በፒው የምርምር ማዕከል በታተመ የሕዝብ አስተያየት መሠረት ዋሽንግተን በዩክሬን ላይ በጣም ብዙ ወጪ ታወጣለች ሲሉ 49 በመቶ ሪፐብሊካኖች ገልጸዋል።

ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው የዴሞክራቶች መራጮች ቁጥር 17 በመቶ ብቻ ነው።

የትራምፕ መልዕክቶች ቀድሞውንም ተጽእኖ እያሳደሩ ሊሆኑ ከመቻላቸው ባለፈ የትራምፕ የማሸነፍ ዕድል ፑቲንን “ሊያበረታታ ይችላል” ሲሉ በለንደን ሮያል ሆሎዌይ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ የሆኑት ሚሼል ቤንትሌይ ተናግረዋል።

አሜሪካን ከኔቶ ያስወጡ ይሆን?

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ 32 አገሮችን ያቀፈው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ትራምፕ ከማያስደስታቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።

ሁሉም አገራት በተስማሙት መሠረት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 2 በመቶ የሚሆነውን ለመከላከያቸው ወጪ ማድረግ ካልቻሉ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ አሜሪካንን ከጥምረቱ እንደሚያስወጡ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

በኔቶ ሕግ መሠረት በአንድ አባል አገር ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በኅብረቱ ውስጥ ባሉ አገራት ላይ እንደተቃጣ ይቆጠራል።

የካቲት ወር ላይ ግን ግዴታውን “የማይከፍል” አገርን እንደማይጠብቁ እና ሞስኮ “የፈለገችውን” እንድታደርግ እንደሚያበረታቱ ትራምፕ ተናግረዋል።

ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ድረ-ገጻቸው ላይ ዓላማቸው የኔቶን ዓላማ እና ተልዕኮ በመሠረታዊነት መገምገም መሆኑን አስፍረዋል።

አሜሪካን ከጥምረቱ ያስወጣሉ የሚለው ላይ ሃሳብ ግን ብዙዎችን ከፋፍሏል።

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የመከላከያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ኤድ አርኖልድ “አሁንም ሊያዳክሙት ይችላሉ” ብለዋል።

በአውሮፓ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥርን በመቀነስ ወይም ሩሲያ የኔቶ አባል አገርን ከወረረች አሜሪካ የምትሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ይህንን ሊያደርጉ ይችላሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ስደተኞችን ከአገራቸው ያባርራሉ?

የትራምፕ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በአስጨናቂ የስደተኞች ፖሊሲ የተሞላ ነበር።

ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ የበለጠ እንደሚገፉበትም ቃል ገብተዋል።

በመጀመሪያው ቀን የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመናቸውም “በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ስደተኞችን የማስወጣት ዘመቻ” እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ሕጋዊ ሰነድ ከሌላቸው ስደተኞች የሚወለዱ ልጆች በቀጥታ የአሜሪካ ዜግነትን የሚያገኙበትን አሠራር ለማስቆም እና በሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጦርነት ለመክፈት ቃል ገብተዋል።

ባለፈው ዓመት በሥልጣን ዘመናቸው በበርካታ ሙስሊም አገራት ሰዎች ላይ የጣሉትን አወዛጋቢ የጉዞ እገዳን እንደሚያሰፉት ሃሳብ አቅርበዋል።

“በሚሊዮን የሚቆጠሩ ያልተፈቀደላቸው ስደተኞችን (ብዙዎቹ አሜሪካ ውስጥ ለአስርት ዓመታት የኖሩ ናቸው) በማስወጣት ትራምፕ ሕጋዊ ስደትን ለመቀነስ ይፈልጋሉ” ሲሉ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የፍልሰት ፖሊሲ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዶሪስ ሚስነር ተናግረዋል።

የአሜሪካን የስደተኞች መልሶ ማቋቋሚያ መርሃ ግብሯን እንደሚያግዱ ትራምፕ በድረገጻቸው አስታውቀዋል። ይህንን ለማድረግ እንደገና ሊሞከር እንደሚችልም ገልጸዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሃሳባቸውን ለማሳካት ሕጋዊ ፈተና ያጋጥማቸዋል ብለው ሚስነር ያምናሉ። በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው እንዳደረጉት ሁሉ ፍርድ ቤቶች የጉዞ እገዳዎች የመሳሰሉ ውሳኔዎቻቸው ላይ ጣልቃ ገብተው እንቅፋት ሆነዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በኢሚግሬሽን ላይ የበለጠ “ሰብአዊ” ፖሊሲ እንደሚተገብሩ ቃል ገብተው በርካታ የትራምፕ ዘመን የድንበር ፖሊሲዎችን አግደዋል ወይም ሰርዘዋል።

በግራም ሆነ በቀኝ ያሉ መራጮች የስደተኞች መጠን እንደሚያስጨንቃቸው ስለሚያሳይ ፕሬዚዳንቱ ሚዛኑን ለመጠበቅ እንዲገደዱ ያደርጋቸዋል።

በሰኔ ወር ባለሥልጣናት የጥገኝነት ጥያቄ ሳያስተናግዱ በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ስደተኞች በፍጥነት እንዲያስወጡ የሚያስችል ግልጽ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዜጎችን ያገቡ እና ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን የትዳር አጋሮችን ከማባረር የሚከላከል ፖሊሲ ይፋ አድርገዋል።

እስራኤልን መደገፋቸውን ይቀጥላሉ?

ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የእስራኤል እና የቀኝ ክንፍ መንግሥቷ ደጋፊ ነበሩ።

ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ እንድትሆን አሜሪካ ዕውቅና መስጠቷን አስታውቀዋል።

ይህም ለአስርተ ዓመታት አሜሪካ ስትመራበት የነበረውን ፖሊሲ በመሻር የአገራቸውን ኤምባሲ ከቴላ ቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም አዛውረዋል።

ባይደን ሁለቱንም እርምጃዎች አልቀለበሱትም።

የኢየሩሳሌም ጉዳይ ጋር በጣም አወዛጋቢ ከመሆኑ አኳያ ፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንቱ ወገንተኝነት እንዳሳዩ እንዲቆጥሩ አድርጓቸዋል።

የትራምፕ መንግሥት በዌስት ባንክ የሚደረገውን የአይሁዶች ሰፈራ ይደግፍ ነበር።ይህ ግን በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ተብሎ ቢታመንም እስራኤል ግን አጥብቃ ትከራከራለች።

የትራምፕ አስተዳደር በእስራኤል እና በአራት የአረብ ሊግ አገራት (ባህሬን፣ኤምሬትስ፣ ሱዳን እና ሞሮኮ) መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ ከሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ ለማድረስ ችለዋል።

አንዳንዶች ግን ትራምፕ እአአ ከ 2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማግስት በቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ቂም መያዛቸውን ይናገራሉ።

ምክንያት የሚሉት ደግሞ ትራምፕ ውጤቱን ባልተቀበሉበት ወቅት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፕሬዚዳንት ባይደን የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት በማስተላለፋቸው ነው።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ኔታንያሁ ለጥቃቱ ዝግጁ እንዳልነበሩ እና በሊባኖስ የሚገኘውን አክራሪ እስላማዊ ቡድን ሄዝቦላህን “ብልህ” ማለታቸው እስራኤልን በሚደግፉ ሪፐብሊካኖች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

ለእስራኤል የሚያደርጉትን ድጋፍ አሁንም አንደሚቀጥሉ ፍንጮች ሰጥተዋል። ጨምረውም እስራኤል ጋዛ ውስጥ በሐማስ ታጣቂዎች ላይ “የምታካሂደውን ዘመቻ ማጠናቀቅ አለባት” ብለዋል። ይህን ግን “በፍጥነት ማጠናቀቅ አለባት” ምክንያቱም “ተቀባይነትን እያጣች ነው” ሲሉ አክለዋል።

በኢራን እና በእስራኤል ጦርነት “ለእስራኤል ጥበቃ እንደሚያደርጉ” ለታይም መጽሔት ቢናገሩም ከኢራን ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ግን በዝርዝር አልተናገሩም።

ፕሬዚደንት እያሉ አሜሪካን ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት አስወጥተዋል። ማዕቀብ እንዲጣልባት ከማድረግ ባለፈ የኢራኑን የጦር አዛዥ ቃሴም ሱሌይማኒን እንዲገደል አዘዋል።

በቻይና ላይ ጫና ያሳድራሉ?

ትራምፕ በሥልጣን ላይ እያሉ ከቻይና ጋር መረር ያለ የንግድ ጦርነት ከፍተው ነበር። በድጋሚ ከተመረጡ በአገሪቱ ላይ ከ60 በመቶ በላይ ታሪፎችን እንደሚጥሉ ጠቁመዋል።

እንደ ኢነርጂ እና ቴሌኮሙኒኬሽን ባሉ ወሳኝ ዘርፎች ውስጥ የሚያስፈልጉትን ሁሉንም የቻይና የመሠረተ ልማት ግብዓቶች “ከቻይና ለመግዛት ለማቆም” ማሰባቸውን ባለፈው ዓመት ተናግረዋል።

በደቡብ ቻይና ባሕር እና በታይዋን ያለው ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ አንዳንድ የቅርብ አጋሮቻቸው የአሜሪካ የደኅንነት ፖሊሲ በቻይና ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረጉን መመልከት ይፈልጋሉ።

በትራምፕ አስተዳደር ወቅት የመከላከያ ቢሮ አማካሪ የነበሩት ኤልብሪጅ ኮልቢ በሪፐብሊካኖች የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከመሆን ባለፈ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ወግ አጥባቂው ምሑር ቤጂንግን ከውጪው ዓለም ቀዳሚ ትኩረታቸው እንድትሆን ከሚሹ ሪፐብሊካኖች መካከል ናቸው።

“ለዩክሬን ጀርባችንን መስጠት አለብን ማለት አይደለም።ነገር ግን ቻይና ከሩሲያ የበለጠ ለአሜሪካ የጥቅም ስጋት በመሆኗ ኪዬቭን መደገፍ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም” ብለዋል ኮልቢ።

አክለውም ትራምፕ “ይህን በሚገባ እንደሚያውቁ” እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

ታይዋን ራሷን የምታስተዳድር እና ከቻይና የተለየች፣ የራሷ ሕገ መንግሥት እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች ያላት ነች። ቤጂንግ ደግሞ እንደ ተገንጣይ ግዛቷ ትመለከታታለች።

ቻይና ደሴቲቱ በቁጥጥር ስር መሆኗን ከመግለጽ ባለፈ ደሴቲቱን ለመውሰድ የኃይል እርምጃን ልትጠቀም እንደምትችል አልካደችም።

ቻይና ታይዋንን ከወረረች ምን ምላሽ እንደምትሰጥ ዩናይትድ ስቴትስ ግልጽ አላደረገችም። ባይደን እስካሁን ካሉ የአሜሪካ መሪዎች አገራቸው ደሴቷን እንደምትከላከል የገለጹ መሪ ናቸው ።

ትራምፕ ምን እንደሚያደርጉ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም።

ይሁን እንጂ ትራምፕ እአአ በ 2016 በምርጫ ካሸነፉ በኋላ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቆየውን የአሜሪካ ፖሊሲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠፍ የታይዋንን የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት ከታይዋን ከተቀበሉ በኋላ ከቻይና ቅሬታ ደርሷቸዋል።

ስለ አካባቢ ጥበቃስ ምን ማለት ይቻላል?

ትራምፕ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት አሜሪካን ከ2015 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንድትወጣ ያደረጉ ሲሆን፣ ባይደን ወደ ሥልጣን ሲመለሱ ግን እርምጃውን ቀልብሰውታል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ድረ-ገጽ ግን ድጋሚ አገራቸውን እንደሚያስወጡ ይገልጻል።

ርካሽ ኃይል ለማቅረብ ነዳጅ ለማግኘት “በቁፋሮ” እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ስለአከባቢ ጥበቃ የሚደረገውን “የማይረባ ሙግት” እንደሚያቆሙም ድረገጹ ላይ ሰፍሯል።

ለንፋስ ኃይል የሚደረገውን ድጎማዎችን ማቆም፣ ለነዳጅ፣ ለጋዝ እና ለከሰል አምራቾች ግብርን መቀነስ እና በባይደን የተጣሉትን የተሽከርካሪ የብክለት ልቀቶች ደንቦችን እንደሚያነሱም አክለዋል።

በካሊፎርኒያ ሳንዲያጎ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴቪድ ጂ. ቪክቶር እንዳሉት ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በአየር ንብረት ላይ ሁለት ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች በዚህ ልክ ተራርቀው አያውቁም።

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል (አይፒሲሲ) የቀድሞ ኃላፊ ፕሮፌሰር ቪክቶር በበኩላቸው የትራምፕ ድል ለአሜሪካ መንግሥት ነባር የአየር ንብረት ትልሞች “አደጋ” ይሆናሉ ብለዋል።

“እርሱ አጋሮቻችንን ያርቃል…ስለዚህ የሚያስደነግጥ ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

ተጽዕኖ ፈጣሪው የአየር ንብረት ለውጥ ድረ ገጽ “ካርቦን ብሪፍ” ምክትል አዘጋጅ የሆኑት ዶ/ር ሲሞን ኢቫንስ ደግሞ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳካት የገባችውን ግብ ለሟሟላት “በጣም አስጊ ይሆንባታል” ብለዋል።

በፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ስርም ሆና አሜሪካ ግቧን በጥቂቱ ላታሳካ ትችላለች ብለዋል።

ባይደን ለአረንጓዴ ኃይል እና ለአየር ንብረት ታሪካዊ የተባለ 300 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ አድርገዋል።

አንዳንድ የአየር ንብረት ተሟጋቾች ግን በአላስካ የሚገኘውን የዊሎው ነዳጅ ፕሮጀክትን ጨምሮ የነዳጅ እና የጋዝ ምርትን ለማሳደግ የወሰዱትን እርምጃ ይቃወማሉ።

“ባይደን የቻለውን ያህል እየሠራ ይመስለኛል” ብለዋል ፕሮፌሰር ቪክተር።

“እኛ በእርግጠኝነት የማናሳካቸውን የልቀቶችን መቀነስ ለማሳካት በድፍረት ቃል ገብቷል።በአየር ንብረት ፖሊሲ ዙሪያ አስተዳደሩ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ብዙ መሥራቱ ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።