የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎች በገንዘብ እና በቪላ ሽልማት ተንበሸበሹ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነው አይቮሪ ኮስት እና ሁለተኛ የወጣው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የገንዘብ እና የቤት ሽልማት ተበረከተላቸው።
የዋንጫው ባለቤት የሆነቸው አይቮሪ ኮስት ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 82 ሺህ ዶላር እና ተመሳሳይ ገንዘብ የሚያወጣ ቪላ ቤት እንደሚያገኙ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገደችው አይቮሪ ኮስት ፕሬዝዳንት አላሳኑ ኦታራ “ለዜጎቻችን በሙሉ ደስታን አስገኝታችኋላ” በማለት ተጫዋቾቹን አወድሰዋል።
በወድድሩ በአይቮሪ ኮስት ተሸንፈው ሁለተኛ የወጡት ናይጄሪያውያንም ወደ አገራቸው ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሱፐር ኢግልስ 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፈው ዋንጫውን በማጣታቸው የናጄሪያውያን ልብ ቢሰበርም፣ ያደረጉት ጥረት በፕሬዝዳንት ቦላ ቱኒቡ ሽልማት እውቅናን አግኝቷል።
እያንዳንዱ የናይጄሪያ ቡድን አባል የአገሪቱን ከፍተኛውን የክብር ሽልማት የሚያገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም የመኖሪያ አፓርታማ እና ከዋና ከተማዋ አቡጃ አቅራቢያ መሬት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ነገር ግን የናይጄሪያ ተጫዋቾች ምን ያህል የገንዘብ ሽልማት ከመንግሥት እንደሚበረከትላቸው አልታወቀም።
ለደረጃ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ገጥማ በማሸነፍ በውድድሩ ሦስተኛ የወጣችው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም እያንዳንዳቸው 52 ሺህ ዶላር እንደሚበረከትላቸው የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
እነዚህ ሁሉ ሽልማቶች ከውድድሩ አዘጋጅ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለቡድኖቹ ከሚሰጠው የሽልማት ገንዘብ ውጪ ነው። አዘጋጁ ለቡድኖቹ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት ከዚህ በፊት ከነበረው በ40 በመቶ ማደጉ ተነግሯል።
በዚህም ምክንያት አሸናፊዋ አይቮሪ ኮስት 7 ሚሊዮን ዶላር፣ ሁለተኛዋ ናይጄሪያ 4 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስተኛ እና አራተኛ የወጡት ደቡብ አፍሪካ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ እያንዳንዳቸው 2.5 ሚሊዮን ዶላር የሚሸለሙ ሲሆን፣ ሩብ ፍጻሜ የገቡ እያንዳንዳቸው ቡድኖች ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ።
በከፍተኛ የማስታወቂያ ስምምነት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባገኘው የጎላ ትኩረት ምክንያት በውድድሩ የ67 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ባልታየ ሁኔታ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛውን የቴሌቪዥን ተመልካች አግኝቷል።
ውድድሩን በዓለም ዙሪያ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቴሌቪዥን ተከታትለውታል።
በዚህ ውድድር የአፍሪካ ዋንጫ ያገኘው ዓለም አቀፍ ትኩረት የአፍሪካ አገራት ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ተጨማሪ ቦታዎችን ሊያስገኝላቸው እንደሚችል የስፖርት ተንታኞች ተናግረዋል።












