የእግር ኳስ ዳኞች ተጨዋቾችን ለ10 ደቂቃ ከሜዳ የሚያግዱበት ሰማያዊ ካርድ ሊሞከር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእግር ኳስ ዳኞች ከተለመደው ቢጫና ቀይ ካርድ በተጨማሪ ሰማያዊ ካርድ መዝዘው ተጫዋቾችን ለ10 ደቂቃ ከሜዳ የሚያሰወጡበት የሙከራ አሰራር በዛሬው ዕለት ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ይህ ሕግ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህብር ቦርድ ሕግ አውጪዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።
ሰማያዊ ካርድ በቅድሚያ ከዳኞች ጋር አለስፈላጊ ንትርክ ውስጥ የሚገቡ ተጨዋቾችን ለመቀጣት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ኳስን መሠረት ያለደረገ ጥፋት የሚፈጽሙ ተጫዋቾችንም ለመቅጣት ጥቅም ላይ ይውላል።
ይህ ካርድ የተመዘዘበት ተጫዋች ለ10 ደቂቃዎች ከሜዳ ውጪ እንዲቆይ ይገደዳል።
ሆኖም ሙከራው መቼ እና በየትኛው ውድድር እንደሚተገበር የተባለ ነገር የለም።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዚህ አሰራር ሙከራ እንደማይተገበርበት ገልጿል። በሌላ በኩል የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው ፊፋ ደግሞ “ ‘ሰማያዊ ካርድ’ የሚባለው ነገር ከፍ ባለ ደረጃ ለመተግበር ተገቢ ያልሆነ እና ያልዳበረ ነው” ብሎታል።
ጨምሮም “የትኛውም እንዲህ አይነት ሙከራ፣ ኃላፊነት በተሞላበት መንግድ በታችኛው የእግር ኳስ ውድድሮች መገደብ ይኖርበታል” ያለው ፊፋ ከሳምንታት በኋላ በሚያደረገው ስብሰባ ይህንን አቋም አጥብቆ እንደሚወያይበት አሳውቋል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህብር ቦርድ ዓመታዊውን ስብሰባ በስኮትላንድ ከሦስት ሳምንት በኋላ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ሰማያዊ ካርድን በከፍተኛ ውድድሮች መተግበር የስብሰባው አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ሰማያዊ ካርድ በአውሮፓውያኑ በ2018/19 የውድድር ዓመነት በ31 ሊጎች ተሞክሮ ከዳኞች ጋር ያለን አላስፈላጊ ንትርክ በ38 በመቶ እንደቀነሰው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህብር ቦርድ ሪፖርት ያመለክታል።
ቀጥሎም ከ2019 እስከ 20 በሁሉም የታችኞቹ የእግር ኳስ እርከኖች የመከባበር እና ፍትሃዊ ጨዋታን ለማሻሻል በማለም ተግባራዊ ሆኗል።
ከዚህም በመቀጠል እስከ ደረጃ አምስት ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ ድረስ የተሞከረ ሲሆን እስከ ደረጃ ሶስት ባሉ የሴቶች እግር ኳስ ተተግብሯዋል።
የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህብር ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ብሊንግኻም “ተመልካቾች የሚደግፉት ቡድን ተስፋ ያለው መልሶ ማጥቃት ላይ እያለ ቴክኒካዊ ጥፋት ቢፈጸም የሚበሳጩ ይመስለኛል” ይላሉ።
ቀጥለው “ጥያቄው ቢጫ ካርድ በቂ ነው ወይ የሚል ነው። . . . ሰማያዊ ካርድ የሚጀመረው በባህሪና ንትርክ ላይ ቢያተኩርም እንደ ታክቲካዊ ጥፋት ላሉ ጉዳዮች መተግበር ይገባናል” ብለዋል።












