በሶማሊያ የኮንስትራክሽን መስፋፋት ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት ሴቶች

በሶማሊያ ዋና ከተማ ግንባታዎች እየተስፋፉ ነው።

ሞቃዲሾ በተደጋጋሚ ካጋጠማት ከባድ የሽብር ጥቃቶች ለመውጣት በምታደርገው መፍጨርጨር ውስጥ እንደ ፋቲ መሀመድ አብዲ እና ሳዲያ አህመድ ኦማር ላሉ ሴቶች ያልተጠበቀ እድል እየሰጠ ይገኛል።

ሁለቱ ሴት መሐንዲሶች በታሌ ከተማ በሚገነባው ባለ 10 ፎቅ ሕንጻ ላይ እየሰሩ ነው።

የራስ ቅል መከላከያ ቆብ ለብሰው በግንባታ ቁሳቁሶች መካከል እየተጓዙ ለሠራተኞች መመሪያዎችን ይሰጣሉ። በዚህ ስፍራ የሚሠሩት በአጠቃላይ ወንዶች ናቸው።

የ24 ዓመቷ ወይዘሮ አብዲ፣ የሶማሌ ንብረት የሆነው የአርካን ኢንጂነሪንግ አገልግሎት ዋና ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር፣ "ስጀምር ሰዎች ተጠራጠሩኝ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የአርካን ኢንጂነሪንግ ሰርቪስ ዋና መሐንዲስ የሆነችው የ24 ዓመቷ አብዲ "እንደጀመርኩ አካባቢ ሰዎች ተጠራጥረውኝ ነበር" ብላለች።

" 'ሴት የሰራችውን ቤት እንዴት እናምናለን? ገንዘቤን እና ንብረቴን እንዴት ለወጣት ሴት መሐንዲስ አምኜ እበትናለሁ' ብለው ይጠይቁ ነበር።"

እሷ እና የስራ ባልደረባዋ ኦማር ላለፉት አምስት ዓመታት በምህንድስና ሙያ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል።

የ24 ዓመቷ ዑማር "ሞቃዲሹ ትፈልገናለች" ስትል ተናግራለች። "እኔ ልጅ ሳለሁ ይህች ከተማ ትርምስ ውስጥ ነበረች፣ አሁን እኛ የመልሶ ግንባታው አካል ነን።"

የጣሊያን የቀድሞ ቅኝ ግዛት የሆነችው ሶማሊያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በጥር 1991 የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ መንግሥት ከፈራረሰ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

አሁንም ቢሆን ለአስርተ ዓመታት የቆየው ጦርነት ጠባሳ በጉልህ ይታያል።

በሻንጋኒ ማዕከላዊ አውራጃ በቦምብ የፈራረሱ ሕንፃዎች ይገኛሉ። ነገር ግን ፍርስራሾቹ እየተሸፈኑ ወይም በረዣዥም የቢሮ ሕንፃዎች እና የመኖርያ አፓርተማዎች እየተተኩ ነው።

ሁለቱም ሴቶች የተወለዱት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሲሆን ያደጉት ደግሞ አገራቸው በግጭቶች ምክንያት ስትፈራርስ እያዩ ነው።

በርካታ ሶማሊያውያን አገሪቱን ለቅቀው ለመሄድ ሲወስኑ ምንም እንኳ አሁንም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ የተለያዩ ጥቃቶችን የሚፈጽም ቢሆንም እነርሱ ግን አገራቸውን ለመገንባት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

"ሴቶች በዚህ መስክ ብዙ ዕድሎችን የሚያገኙበት አንዱ ምክንያት ብዙ የሚሠራ ሥራ ስላለ እና በቂ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ይመስለኛል። ያ ለእኛ ዕድል ይፈጥርልናል" ትላለች።

የሶማሌ መሐንዲሶች ማኅበር ሊቀመንበር ኢብራሂም አብዲ ሄይሌ፣ ምንም እንኳ በሶማሊያ የወንዶች የበላይነት ገንኖ የሚታይበት ማኅበረሰብ ቢሆንም የሰለጠነ ባለሙያዎች ፍላጎት ግን ለውጥ እየፈጠረ ነው በሚለው ይስማማሉ።

"በርካታ በመካሄድ ላይ ያሉ የመሠረተ ልማት፣ የኢነርጂ እና የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች የስራ ጫናው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በመሆኑም ማህበሩ የሴቶችን ተሳትፎ በንቃት ያበረታታል። እንዲሰሩ ብቻ ሳይሆን በሰው ኃይል ረገድ ያሉ ወሳኝ ክፍተቶችን በመሙላት ወሳኝ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ማኅበሩ ሴቶችን በምህንድስና ሙያ ማብቃት እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አመለካከቶችን እና ለኢንዱስትሪው አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሄዎችን ያመጣል ብሎ ያምናል።"

የሞቃዲሾ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ6,000 በላይ ሕንጻዎች ተገንብተው በከተማዋ ገጽታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አሳይተዋል።

የከንቲባው ቃል አቀባይ ሳላህ ሀሰን ኦማር "በሞቃዲሾ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተሻሽሏል፣ ይህም ረዣዥም ፎቆች እና የንግድ ሕንፃዎች እንዲጨምሩ አድርጓል" ብለዋል።

ቢሆንም ለአብዲ እና ለዑመር ካሉት መሐንዲሶች መካከል 5 በመቶዎቹ ብቻ ሴቶች በሆኑበት ዘርፍ ላይ መስራት ቀላል መንገድ አልነበረም።

ብዙ ጊዜ ምክር የሚሰጡም አይገኙም።

"ለስራ ልምምድ ሳመለክት አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች አይቀበሉኝም ነበር" ስትል ኦማር ታስታውሳለች። "አንዲት ሴት የምሕንድስና አካላዊ ተግዳሮቶች መቋቋም ትችላለች ብለው አላሰቡም። በመጨረሻ አንድ ግለሰብ ዕድል እስኪሰጠኝ ድረስ ለሦስት ወራት ያህል ፈልጌ ነበር።"

ዛሬ ሁለቱ በሞቃዲሾ ከሚገኙ ሴት መሐንዲሶች መካከል ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፕሮጀክቶችን በበላይነት በመምራት ከታወቁ መሐንዲሶች መካከል ናቸው።

"ከተማዋ አሁን የረጃጅም ሕንጻዎች እና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች መገኛ ሆናለች። ይህም ከበፊቷ ሞቃዲሾ ጋር ሲታይ በእጅጉ በተቃርኖ የቆመ ነው" ስት አብዲ በኩራት ተናግራለች።

ነገር ግን ሁሉም ሰው በለውጡ ደስተኛ አይደለም። አንጋፋው አርክቴክት ሲኢዶው አብዱል ቡላይ ከተማዋ ታሪካዊ ገጽታዋን እያጣች በመምጣቷ ያዝናል።

"ከጦርነቱ በፊት ሶማሊያን ያደመቁ ሕንፃዎች ውብ ብቻ ሳይሆኑ በጣሊያን ዘመን እና ስልት የተገነቡ በመሆናቸው በወቅቱ በአፍሪካ ብርቅ እና ትኩረትን የሳቡ ነበሩ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የሞቃዲሾ የከተማ ፕላን በሚገባ የተደራጀ ነበር።"

ቦሌይ በተጨማሪም የደህንነት ስጋቶች አሏቸው። "በሞቃዲሾ ሕንጻዎች ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውለው አሸዋ ጨዋማ ነው። ይህም ውጤታማነቱን ይጎዳል።"

ከሶማሊያ ረዣዥም የባሕር ዳርቻ የሚገኘው አሸዋ ብዙውን ጊዜ ሲሚንቶ ለማምረት ይውላል።

ይህ አሰራር በአጠቃላይ የማይበረታታ ሲሆን በብዙ ሁኔታዎች በዓለም አቀፍ የግንባታ ደረጃዎች የተከለከለ ነው።

ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ የጨው ይዘት መኖር ብረትን በቀላሉ እንዲበላሽ ስለሚያደርግ ነው።

"እነዚህ ረዣዥም ሕንፃዎች እሳትን ወይም ከባድ ዝናብን እንዲቋቋሙ እንዲሁም የተከራዮች ደኅንነት ከግምት አስገብተው የተነደፉ አይደሉም። ከእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ ብዙዎቹ የእሳት ማጥፊያዎች እና ትክክለኛ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ይጎድላቸዋል" በማለት ቅሬታቸውን በግልጽ ይናገራሉ።

ሕንፃዎች እየተገነቡበት ያለው ፍጥነት ደግሞ የጥራት ቁጥጥርን እየጎዳው ነው ብለው ያምናሉ።

ለዓመታት ምንም ደንቦች አልነበሩም። ይህም የሕንፃው መዋቅር ላይ ስጋት ያስከትላል።

የከንቲባ ጽህፈት ቤት ባልደረባ ኦማር፣ ይህ ከሦስት ዓመት በፊት እውነት አንደነበር ተናግረዋል።

እናም በእነዚያ ሕንፃዎች ላይ ምንም ማድረግ አይቻልም ሲሉ ያክላሉ።

ነገር ግን አሁን "የጥራት ቁጥጥር አለ እና ማንም በዘፈቀደ ሕንፃ አይገነባም" ብለዋል።

"እኛ ከፍታ ያላቸው ሕንፃዎች የት እንደሚሠሩ እና የመኖሪያ ሕንጻዎች የት መገንባት እንዳለባቸው በግልጽ የሚወስኑ አዳዲስ ሕጎችን እያዘጋጀን ነው" ብለዋል።

ነገር ግን ደንቦች በሥራ ላይ እስኪውሉ ድረስ የሕንፃ ግንባታው ፍጥነት እና ምንም ዓይነት ክትትል አለመደረጉ ስጋት ፈጥሯል።

ከፕላዝማ ዩኒቨርሲቲ ከሲቪል ምሕንድስና ፋኩልቲ የተመረቁት አብዲ እና ኦማር በድርጅታቸው ስር ሁሉም ፕሮጀክቶች በአካባቢው ባለስልጣናት ተቀባይነት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

የግንባታዎች ፈጣን እድገት የታየው ከአገር ውጪ የሚኖሩ ሶማሊያውያን መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰሳቸው እና እየተሻሻለ በመጣው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

ሰፊ የደቡብ ሶማሊያ ግዛቶችን የሚቆጣጠሩት እስላማዊ ታጣቂዎች አሁንም ከተማዋን ዒላማ በማድረግ ጥቃት ይሰነዝራሉ።

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ እአአ በ2022 ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 16.7 በመቶ የሚሆነው ከውጪ የሚላክ ገንዘብ ለሕንፃ ባለሙያዎች እና መሐንዲሶች እድል የሰጠ ነው።

ነገር ግን ፈጣን የከተሞች መስፋፋት ሞቃዲሾን ለመሰረተ ልማት ተግዳሮቶች አጋልጧታል።

ከተማዋ በቂ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት የሌላት ሲሆን ቁጥጥር የማይደረግበት የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ የከተማዋን የከርሰ ምድር ውሃን እያመናመነው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ደኅንነት እና የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ ክሪስቶፍ ሆደር፥ ቁጥጥር ያልተደረገበት ግንባታ በረዥም ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ላይ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"የውሃ ቁጥጥርን በተመለከተ የተቀናጀ አካሄድ እንፈልጋለን። አለበለዝያ ለወደፊቱ ቀውስ ውስጥ እንገባለን። እያንዳንዱ አዲስ ሕንፃ የራሱን ጉድጓድ እየቆፈረ ነው። በትንሽ ቦታ 10 እና 20 የውሃ ጉድጓዶች ሊኖሩ ይችላሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንግሥት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አዲስ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት በመዘርጋት ላይ ቢሆንም፣ አተገባበሩ ግን ያሉትን ሕንፃዎች ማፍረስ ሊያስፈልግ ይችላል።

ይህ ደግሞ አወዛጋቢ እርምጃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎችን እና የንግድ ድርጅቶችን ሊያፈናቅል ይችላል።

ሆደር አክለውም በሞቃዲሾ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አለ ። በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎች በርካቶች ናቸው ይላሉ።

በከተሞች ውስጥ ያለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር በተለይም በዝቅተኛ ኑሮን በሚገፉ አካባቢዎች ድኀነትን እና ማኅበራዊ ልዩነቶችን የበለጠ ሊያሰፋ ይችላል ብለዋል ።

እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም የሞቃዲሾ የወደፊት ጊዜ ተስፋ ሰጪ ይመስላል። ከተማዋ የከተማ ልማት መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማሻሻል እና ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ነው።

የአልሸባብ ተዋጊዎች ፖለቲከኞች በሚያርፉባቸው ውብ ሆቴሎች ላይ የሚያደርሱት የቦምብ ጥቃት እንኳ የሶማሌ መሐንዲሶች ማኅበርን ትጋት አልቀነሰውም።

ሄይሌ ሕንፃዎቻቸው ለወደሙ እና ለፈረሱባቸው አርክቴክቶች እና መሐንዲሶች ቅር ሊያሰኛቸው እንደሚችል ቢናገሩም ሱማሌዎች ግን ጠንካሮች እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻሉ፤ በተለይም ምሕንድስና ለሚማሩ።

"ብዙ ፍንዳታዎች ተከስተዋል፤ ሕልማችን በዚህ አልቆመም። ዛሬ ከ30 ዓመታት በፊት የወደቀው የምሕንድስና ሙያ እያንሰራራ ነው። ያ ማለት ተስፋ አለ ማለት ነው።"

እናም ዓላማው በአምስት ዓመታት ውስጥ ሞቃዲሾ ዘመናዊ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከግጭት በኋላ የመልሶ ግንባታ ሞዴል እንድትሆን ማድረግ ነው።

ኦማር "ሞቃዲሾ ከ1990ዎቹ ጋር ሲነጻጸር የተለየች ከተማ ናት ብዬ አምናለሁ፤ ከተማዋ ወደ አዲስ ዘይቤ ተቀይራለች፣ የሞቃዲሾ እድገትም ከአዲሱ ዓለም ጋር የተጣጣመ ነው" ትላለች።

"በጎዳናዎቿ ላይ ስንቀሳቀስ የገነባኋቸውን ሕንፃዎች ሳይ ኩራት ይሰማኛል ። ሕንጻዎችን ብቻ እየገነባን አይደለም ፣ ተስፋ እየገነባን ነው።"

አብዲም በዚህ ትስማማለች።

"ሴቶች ሕንፃዎችን ከመንደፍ ባለፈ ፕሮጀክቶችን መምራትና ከተማዋን ማነጽ እንደሚችሉ እያረጋገጥን ነው።"