ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፊቱ የማይታየው እና በእስራኤል ከሚፈለጉት አንዱ የሆነው የሐማስ አፈ ቀላጤ - አቡ ኡቤይዳ
የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የአል-ቃሳም ብርጌድ ቃል አቀባይ በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ጎልተው ከወጡት መካከል አንዱ ነው። “አቡ ኡቤይዳ” በመባል የሚታወቀው ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቡድኑን መልዕክት በበይነ መረብ ሲያሰራጭ ደጋግሞ ይታያል።
ቅጽል ስሙን ያገኘው ከቀደምት የሙስሊም የጦር አዛዦች አንዱ ከሆነው ከአቡ ኡቤይዳ ኢብን አል-ጃራህ ነው። ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ላይ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የአልቃሳም አዛዥ መሐመድ አል-ዴይፍ “የአል-አቅሳ ጎርፍ ዘመቻ” መጀመሩን ካወጀ በኋላ የአቡ ኡቤይዳ ስም ገነነ።
ቀዩ የአንገት ልብስ
የአቡ ኡቤይዳን ትክክለኛ ማንነት ማንም አያውቅም። መግለጫ ለመስጠት ካሜራዎች ፊት የሚቀርበው ፊቱን በፍልስጤም ባህላዊ የአንገት ልብስ [ስካርፍ] ተሸፍኖ ነው።
የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እና ዝርዝር ጉዳዮችን ሲገልጽ ከቁርዓን የተወሰዱ ጥቅሶች ከጎን ይኖራሉ። አቡ ኡቤይዳ ንግግሩን በ2020 እንደተጀመረ በሚነገርለት የቴሌግራም ቻናሉ ያካፍላል። በይፋ የሚታወቅ ሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ የለውም።
ንግግሮቹ በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭተዋል። በበርካታ መገናኛ ብዙኃንም ይሰራጫሉ።
መሠረቱን ለንደን ያደረገው የፓን አረብ ዕለታዊ ጉዳዮችን የሚዘግበው ታዋቂው አል ሻራቅ አል-አዋሳት ጋዜጣ “አቡ ኡቤይዳ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ2002 (እአአ) ነበር። ከአል-ቃሳም የጦር አባላት አንዱ በመሆን ይታወቅ ነበር” ሲል ጽፏል።
አቡ ኡቤይዳ መግለጫ ሲሰጥ ፊቱን ተሸፋፍኖ ሲሆን፣ ይህንንም ከቀድሞው የአልቃሳም መሪ ኢማድ አቀል ኮረጀው መሆኑ ተዘግቧል። አቀል በ1993 (እአአ) በእስራኤል ተይዞ በእስር ላይ ይገኛል።
የአልቃሳም ብርጌድ ቃል አቀባይ
እአአ በ2006 ደግሞ አቡ ኡቤይዳ የአል-ቃሳም ብርጌድ ኦፊሴላዊ ቃል አቀባይ ሆኖ ተሾመ። ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መታየት የጀመረው እአአ በ2006 ነበር። ወቅቱም ሐማስን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ከጋዛ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያ የወረሩበት ነበር።
ዘመቻው የተካሄደው ሁዳ ጋሊያ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ቤተሰብ ቤት በከባድ መሳሪያ ከተመታ በኋላ ነው። በጥቃቱ አባቷ የተገደለባት የ10 ዓመት ታዳጊ በጋዛ የባሕር ዳርቻ ላይ “አባቴ አባቴ አባቴ” እያለች ስትሮጥ እና ከአባቷ አስከሬን አጠገብ ስትወድቅ የሚያሳው ተንቀሳቃሽ በመላው ዓለም ትኩረትን ስቦ ነበር።
በወረራው ወቅት እስራኤል ወታደር ጊላድ ሻሊት ተማረከ። ሁለት ወታደሮች ሲገደሉ ከሻሊት ሌላ ሁለት ደግሞ ቆስለዋል።
ሻሊት እአአ 2011 ነፃ ወጣ። እሱን ለማስለቀቅ እስራኤል እና ሐማስ በተስማሙት መሠረት ከአንድ ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተፈትተዋል።
እአአ በ2014 የእስራኤል እና የጋዛ ጦርነት ሲካሄድ አቡ ኡቤይዳ ወደ ሚዲያ ብቅ ብሎ ሻውል አሮን የተባለ የእስራኤል ወታደር መያዙን ገለጸ። እስራኤል ግን ወታደሯ መሞቱን ገለጻ ተከራክራለች።
ምሥጢራዊ ማንነት
የአቡ ኡቤይዳን ማንነት ለማወቅ ብዙዎች ይፈልጋሉ። ዘንድሮ አቡ ኡቤይዳ ነው ያለውን ሰው የሚያሳይ ምሥል የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አቪሻይ አድራይ በኤክስ ገጹ ለጥፏል። አድራይ የሰውየው ትክክለኛ ስም “ሁዳይፋ ሰሚር አብዱላህ አል ካህሎት” ነው ብሏል። ስለጉዳዩ ሐማስም ሆነ አል-ቃሳም ትንፍሽ አላሉም።
የዲዮት አህሮኖት የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ አቡ ኡቤይዳ እአአ በ2013 ጋዛ ከሚገኘው እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ፋክልቲ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል። ጥናታዊ ጽሑፉም “በአይሁድ፣ በክርስትና እና በእስልምና መካከል ያለችው ቅድስት መሬት” የሚል ርዕስ ያለው ነው። ሦስተኛ ዲግሪውን ለመሥራትም እየተዘጋጀ ነበር ብሏል።
ጋዜጣው አክሎ እንደዘገበው አቡ ኡቤይዳ የተወለደው እስራኤል በ1948 በተቆጣጠረቻት የጋዛ ናሊያ መንደር ውስጥ ነው። እንደ ጋዜጣው ከሆነ ኡቤይዳ በጋዛ ሰሜናዊ ምሥራቅ ውስጥ በምትገኘው ጃባሊያ ውስጥ ነው የሚኖረው።
የእስራኤሉ ጋዜጣ አክሎም እአአ ከ2008 እስከ 2012 ድረስ መኖሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ በእስራኤል ጥቃት ተፈጽሞበታል። አሁን በጋዛ ሰርጥ በሚካሄደው ጦርነትም ቤቱ ጥቃት ደርሶበታል።
ቢቢሲ በፓን አረብም ሆነ በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የወጡትን ዘገባዎች ማረጋገጥ አልቻለም።