አርሰናል ከአስተን ቪላ - የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

የአስተን ቪላው አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሪ በአውሮፓውያኑ 2019 የመድፈኞቹ አሠልጣኝ ነበሩ። በ18 ወራት ቆይታቸው ከአርሰናል ጋር የተሳካ የሚባል ጊዜ አላሰለፉም። ኡናይ የቀድሞው ቡድናቸውን በመርታት ዋንጫው ላይ ዐይናቸውን ይጥሉ ይሆን?
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን "የአርሰናል ደጋፊዎች ያደረሱባቸውን ግፍ ስመለከት ወደ ኤሜሬትስ አቅንተው ድል እንዲቀናቸው ተመኘሁ" ይላል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ሐሙስ ይከናወናሉ። የአውሮፓውያኑ አሮጌ ዓመት መሰናበቻ እና የአዲሱ ዓመት መቀበያ ጨዋታዎች ናቸው። ሱተን የዚህ ሳምንት ጨዋታዎችን ግምቶች እንዲህ አስቀምጧል።
በርንሊ ከኒውካስል ዩናይትድ
በርንሊ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ነገር ግን ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ ድል በጣም ያስፈልጋቸዋል።
አሠልጣኝ ስኮት ፓርከር ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ድል ቀንቷቸው ባያውቅም እኔ ጥሩ አቋም ላይ እንዳሉ ነው የማምነው።
ኒውካስል በበኩሉ ጥሩ ጨዋታ ይጫወታል፤ ነገር ግን ድል አይቀናውም። በተደጋጋሚ ኒውካስሎች ድል ይቀናቸዋል ብዬ ብገምትም አልተሰካልኝም።
ምንም እንኳ የኤዲ ሀው ቡድን ከሜዳው ውጭ ያለው አቋም ደካማ ቢሆንም አሁንም ግምቴ ለኒውካስል ነው።
ግምት፡ 0 - 1

ቼልሲ ከቦርንመዝ
ቼልሲ አምስተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጠም ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ያሸነፈው።
ባለፈው ኅዳር በ10 ተጫዋቾች ከአርሰናል ጋር አቻ ሲወጣ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ አለበት ብዬ አስቤ ነበር። ቀጥሎ ባሉት ጨዋታዎች ግን ቡድኑ መዳከም ታይቶበታል።
ቦርንመዝም ባለፉት 9 ጨዋታዎች አንድ እንኳ ድል ሊቀናው አልቻለም። አሠልጣኝ አንዶኒ ኢራዮላ አስጊ ጊዜ ላይ ናቸው።
ምናልባትም ድንቅ የሚባሉ ተከላካዮቻቸውን ለማድሪድ፣ ለሊቨርፑል እና ለፒኤስጂ መሸጣቸው ሳይቆጫቸው አይቀርም። አንትዋን ሴሜንዮም ይህ የመጨረሻ ጨዋታ ሊሆን ይችላል።
የኢራዮላ ቡድን ግል እንደሚያስቆጥር ባምንም የኤንዞ ማሬስካ ቡድን ድል ይቀናዋል።
ግምት፡ 2 - 1
ኖቲንግሀም ከኤቨርተን
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ኤቨርተን ኖቲንግሀምን በቀላሉ ነበር ያሸነፈው። በወቅቱ ኤቨርተን ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾቹን አላጣም ነበር።
ግሪሊሽ ከበሽታው አገግሞ እንደሚመለስ ቢጠበቅም ዲውዝበሪ-ሆል እና ንዲያዬ የሉም።
ኖቲንግሀም በሲቲ በሜዳቸው ቢሸነፉም ጥሩ የሚባል ጨዋታ አሳይተውናል። ኤቨርተን ወሳኝ ተጫዋቾቹን በማያሰልፍበት ጨዋታ ድል ይቀናዋል ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ 1 - 0
ዌስት ሀም ከብራይተን
ዌስት ሀም በየሳምንቱ ሁኔታዎች እየተባባሱበት መጥተዋል። የኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶ ቡድን የወራጅ ቀጣናው እየተንገዳገደ ይገኛል።
ብራይተን ወጥ አቋም ባይኖረውም ከሊቨርፑል እና አርሰናል ጋር በነበረው ግጥሚያ ምን ያህል ተፎካካሪ እንደሆነ ተመልክተናል።
ጨዋታው በጠባብ ጎል ልዩነት የሚጠናቀቅ ሲሆን ድሉ ግን የብራይተን እንደሚሆን አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 2

አርሰናል ከአስተን ቪላ
ቪላ አስደናቂ አቋም ላይ ነው። ቼልሲ ያሸንፋል ብዬ የገመትኩትን ጨዋታ ድል ነስተው ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል።
በተለይ ደግሞ ከመመራት ተነስተው በርካታ ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ የሚደርሳቸው የለም።
ዋትኪንስ በቼልሲው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ቪላ 11 ጨዋታዎች በተከታታይ እንዲረታ አስችሏል።
የቪላ ግስጋሴ የሚያስደንቅ ቢሆንም አርሰናል ይህን ጨዋታ ያሸንፋል። እርግጥ ነው ጨዋታው ለመድፈኞቹ ቀላል አይሆንም።
ጨዋታው በጠባብ ጎል ልዩነት የሚጠናቀቅ ሲሆን ድሉ ግን የመድፈኞቹ ነው።
ግምት፡ 2 - 1
ማንቸስተር ዩናይትድ ከዎልቭስ
ዩናይትድ በኒውካስል ይሸነፋል ብዬ በመገመቴ በርካታ ደጋፊዎች ሲወርዱብኝ ነው የከረሙት።
እርግጥ ነው የሩበን አሞሪም ቡድን ድል በማድረግ ግምቴ አበላሽቶታል። ነገር ግን ጨዋታቸው ግራ የገባው እንደነበር ደጋፊዎችም የሚክዱት አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ ይህን ጨዋታ ዩናይትድ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ። ዎልቭስ ከአሁኑ ከፕሪሚዬር ሊግ ወርደው ቢገላገሉ ይሻላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ከተኩላነት ወደ ግልገል በግነት ተቀይረዋል። ከ18 ጨዋታ ማግኘት የቻሉት 2 ነጥብ ብቻ ነው።
ግምት፡ 2 - 1
ክሪስታል ፓላስ ከፉልሀም
ፓላስ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል። ፉልሀም ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች በተከታታይ አሸንፈዋል።
ፉልሀም ወደ ወራጅ ቀጣና እየሄደ ነው ብዬ ወቀሳ የሰነዘርኩበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። አሁን በነጥብ ከፓላስ ጋር እኩል ሆነዋል።
እሑድ ፓላስ ከቶተንሀም ጋር ያደረገውን ጨዋታ ተመልክቻለሁ። ከጨዋታው የሆነ ነገር ማግኘት ይገባቸው ነበር። በዚህኛው ጨዋታ ይህ ይሳካለቸዋል። ድልም ይቀናቸዋል።
ግምት፡ 2 - 0

ሊቨርፑል ከሊድስ
ሁለቱ ቡድኖች በሊድስ ሜዳ ኤላንድ ሮድ በተገናኙበት ወቅት ሊድስ ነጥብ እንደሚያገኝ ገምቼ ተሳክቶልኛል።
አሁን የሚገናኙት በአንፊልድ ነው። ሊቨርፑል ደግሞ ድጋሚ ልበ ሙሉነት እየተሰማቸው ነው። ሊድስም ቢሆን አቋሙ እያገገመ ነው። አጥቂው ዶሚኒክ ካልቨርት ሌዊን በስድስት ጨዋታዎች 7 ግቦች አስቆጥሯል።
የአርን ስሎት ቡድን ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ነገር ግን ሲጫወቱ ስመለከታቸው አሁንም ክፍተት እንዳለባቸው አስተውላለሁ።
ሊቨርፑል ከዚህ ጨዋታ በኋላ ወደ ፉልሀም እና አርሰናል ያቀናል። ይህን ጨዋታ ግን ያሸንፋል።
ግምት፡ 2 - 1
ብሬንትፈርድ ከቶተንሀም
ስፐርስ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሜዳ ውጭ ያላቸው ውጤት መልካም ነው። ባለፈው ሰንበት ፓላስን በመርታት ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ብሬንትፈርድም ቢሆን እየከነፈ ነው።
ይህን ጨዋታ እንዴት ልገምት? እውነት ለመናገር የስፐርስ ጨዋታ ማራኪ የሚባል አይደለም።
ብሬንትፈርድ ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች 8 ነጥብ አግኝተዋል። በዚህ ጨዋታ አሸናፊ ያለ አይመስለኝም።
ግምት፡ 1 - 1
ሰንደርላንድ ከሲቲ
በአሁኑ ወቅት ሲቲን የሚያስቆም ያለ አይመስለኝም። ራያን ቼርኪ የሚገርም ብቃቱን እያሳየን። ፊል ፎደንም ወደምናውቀው ብቃቱ ተመልሷል። አጥቂው ኧርሊንግ ሀላንድ ግብ ከማስቆጠር ምንም አያግደውም።
ሰንደርላንድ ከአርሰናል ጋር አቻ የወጡበት ዓይነት ከባድ ጨዋታ ሊያሳዩን ይችላሉ። የተከላካይ መስመራቸው የተደራጀ ነው። ዘንድሮ በሜዳቸው ተሸንፈው አያውቁም።
ምናልባትም በሜዳቸው ይህ የመጀመሪያው ሽንፈት ይሆናል። ሰንደርላንድ ጎል ሊያስቆጥር ቢችልም ድሉ ግን የሲቲ ነው።
ግምት፡ 1 - 3















