የወርቅ ዋጋ ባለፉት 11 ወራት ብቻ ከ68 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳየ

ጥፍጥፍ ወርቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ4,400 ዶላር በላይ በመሸጥ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለፀ።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ በሚቀጥለው ዓመት የወለድ መጠኑን ይቀንሳል ተብሎ ስለሚጠበቅ የከበሩ ማዕድናት ዋጋ ጨምሯል ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል።

ወርቅ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ አንድ ግራም 2,600 ዶላር የነበረ ቢሆንም፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት፣ የትራምፕ አስተዳደር የጣላቸው ታሪፎች እና የዋጋ ቅነሳዎች ይኖራሉ የሚሉ መላምቶች ባለሀብቶች እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶችን የመግዛት ፍላጎታቸው ጨምሯል።

እንደ ብርና ፕላቲኒየም ያሉ ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ዋጋም ጨምሯል።

የወርቅ ዋጋ ሰኞ ዕለት ወደ 4,420 ዶላር ከፍ ብሎ ታይቷል።

ባለፉት 11 ወራት ብቻ የወርቅ ዋጋ ከ68 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

በቡሊዮንቮልት የወርቅ ቡሊዮን ገበያ የምርምር ዳይሬክተር አድሪያን አሽ ይህ ጭማሪ እአአ ከ1979 ወዲህ ከፍተኛው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አሽ ለወርቅ ዋጋ ማሻቀብ እአአ በ2025 "የወለድ ተመኖች፣ ጦርነት እና የንግድ ውጥረቶች መባባስ ቀስ በቀስ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የከበሩ ማዕድናት ገበያ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዋጽኦ አንዳላቸው ይናገራል፤ እናም በዚህ ዓመት የወርቅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።"

"የንግድ ጦርነቱ፣ በአሜሪካ የፌዴራል ግምጃ ቤት ላይ የተሰነዘሩት ጥቃቶች እና ቀጠናዊ ውጥረቶች፤ እነዚህ ሁሉ መነሻቸው ከትራምፕ ነው" ብለዋል።

ዝቅተኛ የወለድ መጠን መጠበቅ ማለት እንደ ቦንድ ላሉ ኢንቨስትመንቶች ዝቅተኛ ትርፍ ማለት ነው።

ስለዚህ ባለሀብቶች ትርፍ ለማግኘት እንደ ወርቅና ብር ያሉ ሸቀጦችን መግዛት እና ማከማቸት ይፈልጋሉ።

በተጨማሪም መዋዕለ ነዋያቸውን በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ አፍስሰው ለኪሳራ ከመጋለጥ ይልቅ በተለያዩ መስኮች ላይ በመሰማራት ማትረፍ ያስባሉ።

በአሁኑ ጊዜ በተንታኞች መካከል ያለው ስምምነት አሜሪካ እአአ በ2026 ሁለት ጊዜ የወለድ ተመኖችን እንደምትቀንስ ነው።

የጎልድማን ሳክስ ለፍላጎቱ መጨመር ምክንያት የሆነው ማዕከላዊ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሳቸውን የወርቅ ክምችት በማስፋት የኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ለመቋቋም፣ በአሜሪካ ዶላር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የራሳቸውን ኢንቨስትመንት አማራጭ ለማብዛት እየተጠቀሙ መሆኑ ነው ይላል።

ቡድኑ ይህ ሁኔታ ​​እንደ አውሮፓውያኑ በ2026ም እንደሚቀጥል ተንብዮአል።

ደካማ የአሜሪካ ዶላር የወርቅ ዋጋን ከፍ ለማድረግም ለውጭ አገር ገዢዎች ወርቅን ርካሽ በማድረግ በጎ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በዚህ የፈረንጆች ዓመት ሌሎች የከበሩ ማዕድናትም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል። የብር መሸጫ ዋጋ ሰኞ ዕለት በግራም 69.44 ዶላር በመሆን ክብረወሰን አስመዝግቧል።

እአአ በ2025 የብር የመሸጫ ዋጋ በ138 በመቶ አድጓል፣ ፕላቲኒየም ደግሞ በ17 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ዋጋን በማስመዝገብ ከወርቅ በልጧል።

ከወርቅ በተለየ መልኩ፣ ሌሎች የከበሩ ማዕድናት በኢንዱስትሪ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ፣ ይህም የአክሲዮን ገበያ ፍላጎትን አነቃቅቷል።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወደ ቬንዚዌላ እንዳይገቡና እንዳይወጡ "እገዳ" ከጣለች በኋላ የነዳጅ ዋጋም ጨምሯል።

የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ53 ሳንቲም ወደ 60.99 ዶላር ከፍ ሲል የአሜሪካ ነዳጅ ደግሞ በ1.6 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 57.40 ዶላር ከፍ ብሏል።