በአሜሪካ ውዝግብ አስነስቶ የነበረው የሰይጣን አምላኪዎች ሐውልት እና ትርጉሙ

የፎቶው ባለመብት, AP
ሰይጣን አምላኪዎች በዲትሮይት ያቆሙት ሐውልት በርካቶችን አነጋግሯል። ከነሐስ የተሠራው ሐውልት 9 ጫማ ርዝመት አለው።
ባለ ቀንድ፣ ሁለት ፈገግ ያሉ ልጆችን የያዘ፣ የሴትም የወንድም መራቢያ አካል የያዘ ቅርጽ (Baphomet) በሐውልቱ ላይ ይታያል።
ሐውልቱን ለማሠራት 100 ሺህ ዶላር ወጥቷል። ሐውልቱ ሲመረቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰይጣን አምላኪዎች በሥፍራው ተገኝተዋል።
በወቅቱ በኦክላሆማ ግዛት አሥርቱ ትዕዛዛትን ከያዘው የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ፊትለፊት ሐውልቱን ለማቆም ዕቅድ ተይዞ ነበር።
የኦክላሆማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን የመንግሥት ይዞታ በሆነ መሬት ላይ ሃይማኖታዊ ምልክት ማኖር አይፈቀድም ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Chris Switzer/Facebook
ባፎሜት ምንድን ነው?
ሐውልቱ ላይ ያለው ቅርጽ ባፎሜት ይባላል።
12ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ 'ናይትስ ኦፍ ቴምፕለር' በመባል የሚታወቁ ቡድኖች ከደረሰባቸው ስቃይና እንግልት ጋር ይያያዛል። 1100 የሚደርሱት የቡድኑ አባላት ሰይጣንን በማምለክ ይታወቃሉ።
ይህነን ክስተትም ከመቶ ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ትስስር እንዳላቸው የሚገልጹ የታሪክ ምሁራንም አሉ።
በዘመናት ሒደት ስለቡድኑ የሚነገሩ ምሥጢራዊ መረጃዎች እየተስፋፉ መጡ።
የዳን ብራውን ዝነኛው ታሪካዊ ልብ ወለድ 'ዳ ቪንቺ ኮድ' መነሻ እንደሆኑም ይታመናል።
ባፎሜት የሚለው ቃል 'ሶፊያ' ወይም ጥበብ በሚል ይተረጎማል።
እአአ በ1856 የተሳለው የባፎሜት ምሥል ዝነኛ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።
ምሥጢራዊ ትርጉም ባላቸው ሥራዎቹ የሚታወቀው ፈረንሳዊ የሥነ ጥበብ ባለሙያ ኢፋስ ሌቪ ነው ያዘጋጀው።
በሁለት ቀንዶቹ መካከል ብርሃን ያለው፣ ሁለት ፈገግ ያሉ ልጆችን የያዘ እንዲሁም የሴትም የወንድም መራቢያ አካል የያዘ ቅርጽ ነው የሠራው።
ክንዱ ላይ በላቲን 'SOLVE' እና 'COAGULA' ተብሎ ተጽፏል። ትርጉማቸውም 'መለያየት' እና 'መገናኘት' ማለት ነው።
መገናኘትም መለያየትም የፈጣሪ ስጦታ ነው በሚል ይተረጎማል።
የሌቪ ሥዕል የ'ሳታኒክ ቴምፕል' ንቅናቄ መነሻ ነው።
የሰይጣን አምልኮ ተከታይ የሆነው ተንታኙ ግሬቪስ እንደሚለው ቅርጹ ሁሉንም ተቃርኖዎች የያዘ ነው። እነዚህም የበላይ እና የበታች፣ እንሰሳ እና ሰው እንዲሁም ወንድ እና ሴት ናቸው።
ተቃርኖዎችን ለማወደስ ያለመ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Other
የሁለት ጣት ሰላምታ
በሐውልቱ ላይ በቀኝ በኩል ሁለት ጣት 'ሰላም' የሚል ምልክት ለማሳየት ወደ ላይ ከፍ ብሎ ይታያል። በግራ በኩል ደግሞ ሁለት ጣቶች ወደታች ያመለክታሉ።
ይህም ወደላይ እና ወደታች ለመጠቆም በሚል ነው የተሠራው።
በተለይም በሬነሰንስ እና ሪፎርሜሽን ዘመናት ታዋቂ ከነበረው ፀሐፊ ኸርሜስ ትሪስመስተስ የተወረሰ ሐሳብ ነው።
ሐሳቡ በሳይንስ እና በዓለም አፈጣጠርም ይንጸባረቃል።
ሌቪ እንዳለው ቅርጹ የሚያመላክተው "ይቅርታ እና ፍትሕ" ያላቸውን ዝምድና ነው።

የፎቶው ባለመብት, Matt Anderson
ሁለቱ ሕጻናት
ሁለቱ ሕጻናት በሐውልቱ ላይ እንዲኖሩ የተደረገው "ልጆች እንደ ውብ የሥነ ጥበብ ሥራ እንዲመለከቱት እና እንዳይፈሩ ነው" ሲል ተንታኙ ግሬቪስ ያስረዳል።
የሚታየው የፍየል ፊት አስፈሪ ወይም የተቆጣ እንዳይሆን ተደርጓል። የተላበሰው ገጽታ እምብዛም ስሜት የማያንጸባርቅ እንዲሆን የተደረገው "በተለመደው የባህል ጫና ውስጥ እንዳይወድቅ" በሚል እንደሆነም ይነገራል።
ልጆች ስለ ሰይጣን ከሚሰሙት አንጻር በፍርሃት ሐውልቱን እንዳይመለከቱ ለማድረግ እንደተደረገ ባለሙያው ይገልጻል።
"ልጆች አንድን ሃይማኖት እንዲከተሉ ይገደዳሉ። እኛ ግን ያንን ማድረግ አንፈልግም" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Matt Anderson/Facebook
የእባብ ምልክት
በሐውልቱ ላይ ከጥንታዊ የግሪክ ታሪክ የተወሰዱ ሁለት የተጠላለፉ እባቦች ይታያሉ።
ሁለቱ የተጠላለፉ እባቦች (Caduceus) ንግድ፣ ድርድር እና መከባበርን የሚያመለክቱ ናቸው።
የሰይጣን አምልኮ ተከታይ የሆነው ግሬቪስ እንደሚለው ሁለቱ እባቦች "የሁለት ተቃራኒዎችን መቻቻል" ያሳያሉ።
"የሰይጣን አምላኪዎች ሐውልት ከክርስቲያኖች አሥርቱ ትዕዛዛት ፊት ለፊት ሲቆምም የሚያሳየው ይሄንን ነው። ግጭት ሳይኖር በልዩነት መቀጠል ይቻላል" ይላል።
ሌላ በሐውልቱ የሚታየው የሴትም የወንድም መራቢያ አካል የያዘ ቅርጽ ነው።
"በቅርጹ ላይ ጡት አይታይም። በፆታ ክርክር ውስጥ መግባት ስለማንፈልግ ነው ይህንን ያደረግነው" ሲል ተንታኙ ያስረዳል።
"ከተቃርኖ ይልቅ የሁለትዮሽ ትስስርን ያሳያል" በማለትም ያክላል።
አምስት ጎን ያለው ኮከብ
በሐውልቱ ፊትና ጀርባ ባለ አምስት ጎን ኮከብ (pentagram) ይታያል።
ይህ ቅርጽ በሰይጣን አምላኪዎች ዘንድ ታዋቂ ነው። ኮከቡ እና መስቀል ተገልብጠው ይታያሉ።
"ሰዎች በመጡበት ባህል የሚያምኑበትን ነገር ዳግመኛ እንዲያጤኑ የሚጋብዝ ነው። የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እና የሥነ ተዋልዶ መብት ላይ የተዛባ ምልከታ ሊኖራቸው ይችላል" ሲል የሰይጣን አምልኮ ተከታዩ ያስረዳል።
ሐውልቱ ላይ በቀንዶች መካከል ብርሃን ይታያል። ዕውቀትን መሻትን እንደሚያመለክት ሰይጣን አምላኪዎች ይናገራሉ።
ዕውቀትን መሻት የእምነቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ ተደርጎ ይወሰዳል።
ሠዓሊው ሌቪ "በቀንዱ መሀል የዕውቀት ብርሃን ፈንጥቋል። ዓለምን ሚዛናዊ ማድረግን ያመላክታል። ነፍስ ከምንም በላይ ናት። ቁስ ከነፍስ ቀጥሎ የሚመጣ ነው" ሲል ይገልጸዋል።
በሐውልቱ ላይ የሰይጣን አምላኪዎች ሰባት ዋነኛ ትዕዛዞች ተቀርጸዋል።
"ርሕራሔ፣ ጥበብ፣ ፍትሕ" የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ከጀርባው ከገጣሚው ሎርድ ባይረን የተወሰደ ጥቅስ ይገኛል። ይህም "ሰይጣን ማነው? እስከ ዘለዓለም በዕውቀት በተሞላ ሐሴት እንድትኖሩ የፈቀደው ወይስ እንድትኖሩ ያልፈቀደው?" የሚል ነው።
ሰይጣን አምላኪዎች ማን ናቸው?
ሰይጣን አምላኪዎች 'ሳታኒስት' 'ሰኪውላሪስት' እና ሌሎችም መጠሪያዎች አሏቸው።
'የግል ነጻነት አቀንቃኞች' ሲሉም ራሳቸውን ይጠራሉ።
የሰይጣን አምልኮ ተከታይ የሆነው ተንታኙ ግሬቪስ እንደሚለው፤ ሰይጣን አምላኪዎች "የሰው ልጅን ባሕሪ" ይረዳሉ።
"ከፈጣሪ ይልቅ ለዕውቀት መጓጓት፣ አመጸኛ መሆን፣ የግል ነጻነትን መሻት እንመርጣለን" ሲል ይገልጸዋል።
ስለዚህም ሰይጣን አምላኪዎች ምክንያታዊነትን እንደሚያበረታቱ ይናገራል።















