ቲክቶክ፡ አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ሲታገድ ምን ይከሰታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቲክቶክ ከአራት ዓመታት በፊት በሕንድ እስኪታገድ ድረስ በጣም ተወዳጅ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መተግበሪያ ነበር።
አሁን ደግሞ አሜሪካ ቲክቶክን ለማገድ ዳር ዳር እያለች ነው።
ከአራት ዓመት በፊት ሕንድ የቲክቶክ ትልቁ ገበያ ነበረች። በዚህም የ200 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ለመሙላት፣ የይዘት እና ተፅእኖ ፈጣሪዎች ሕይወትን ለመቀየር ብዙ ዕድሎችን ፈጥሯል።
በርካታ ባለ ተሰጥኦዎች እንዲሁም መደበኛው መገናኛ ብዙኃን የራቃቸው ማኅበረሰቦች መድረክ ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ሁሉ ግን በሕንድ እና በቻይና መካከል የድንበር ይገባኛል ውጥረት እስኪከሰት ድረስ ብቻ ነበር የዘለቀው።
የሁለቱ አገራት ውጥረት ሲካረር ቲክቶክ አገር አማን ብሎ በሕንድ ገበያ ውስጥ ይገማሸር እንደነበር ተጠቃሚዎቹ ያስታውሳሉ።
የድንበር ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ግን፣ ከሰኔ 22/2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሕንድ መንግሥት ቲክቶክን በግዛቴ እንዳላይ አለ።
በእርግጥ ሕንዳውያን ቲክቶከሮች የሠሯቸው ቪዲዮዎች አሁንም በመተግበሪያው ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ዛሬን ሳይሆን ትናንትን ለመዘከር የተቀመጡ ናቸው። የአሁን ሳይሆን የነበር ማስታወሻዎች ሆነዋል።
ይህ በአሜሪካ ሊሆን ስላለው እንደ መጥፎ ምልክት ሆኖ ታይቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ቲክቶክን ከአሜሪካ ምድር ማገድ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ፈርመዋል።
ይህ ሕግ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የመተግበሪያውን ድርሻ ከተጨማሪ የሦስት ወር የእፎይታ ጊዜ ጋር እንዲሸጥ ወይም በአገሪቱ ውስጥ ሊታገድ እንደሚችል ያዛል።
ባይትዳንስ ግን ማኅበራዊ ሚዲያውን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌለው አሳውቋል፤ ሕጉ ይሻርልኝ ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ከሄደ በኋላም ኅዳር 27/ 2017 ዓ.ም. ይግባኙ ውድቅ ተደርጎበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ በኋላም ወደ ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ ቢጠበቅም ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሚቀለበስ ውሳኔ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።
ምንም እንኳን እያንዣበበ ያለው የፍርድ ቤት ፍልሚያ በአሁኑ ጊዜ የቲክቶክን ዕጣ ፈንታ አጠራጣሪ ቢያደርገውም፣ ትልቅ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያን ማገድ በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም።
ነገር ግን የሕንድ ልምድ የሚያሳየው አንድ ትልቅ አገር ቲክቶክን ከዜጎቿ ስልክ ላይ ጠራርጋ ልታስወግድ እንደምትችል ነው።
ይህን ዓይነቱን እርምጃ የወሰደችው ሕንድ ብቻ አይደለችም። በ2016 ዓ.ም. ኔፓል ቲክቶክን ለማገድ ስትወስን፣ ፓኪስታን ደግሞ ከ2020 ጀምሮ በርካታ ጊዜያዊ ዕገዳዎችን በመተግበሪያው ላይ ጥላለች።
በእርግጥ የሕንድ የቲክቶክ ዕገዳ ታሪክ ተጠቃሚዎች በፍጥነት አዲስ ነገርን መላመድ እንደሚችሉ ቢያሳይም፣ ነገር ግን ቲክቶክ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም አብዛኛው ባህሉ አብሮ እንደሚሞት ቋሚ ተጠቃሚዎቹ ህያው ምስክር ሆነዋል።
በቦምቤይ የምትኖረው የፊልም ሃያሲዋ ሱሳሪታ ቲያጊ ቲክቶክ ሲታገድ አካውንቷ 11,000 ተከታዮች ነበሩት።
"ቲክቶክ በጣም ትልቅ ነበር። ሰዎች በመላ አገሪቱ ይጨፍሩ፣ አጫጭር ድራማዎችን ይሠሩ፣ በኮረብታ ላይ በምትገኘው ትንሽ ቤታቸው ሕይወትን እንዴት እንደሚገፉ ያጋሩ ነበር" ትላለች ቲያጊ።
"ብዙ ሰዎች ሁሌም የተነፈጉትን ይህንን ዕይታ ነበር በቲክቶክ ያገኙት።"
መተግበሪያው ልዩ ክስተት ነበር፤ ምክንያቱም ለገጠሪቷ ሕንድ ተጠቃሚዎች በሌላ መተግበሪያዎች የማይገኙ ከፍተኛ ተመልካቾችን የማግኘት፣ እንዲሁም በአንድ ጀንበር ታዋቂ የመሆን ከፍተኛ ዕድሎችን ሰጥቷል።
"ለመጀመሪያ ጊዜ የይዘት ፈጠራን ዲሞክራሲያዊ አድርጓል" ሲል በኒው ደልሂ መቀመጫውን ያደረገው የቴክኖሎጂ ፀሐፊ እና ተንታኝ ፕራሳንቶ ኬ ሮይ ያስረዳል።
"እነዚህ በጣም የገጠር ሰዎች በማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መሰላል ላይ ዝቅ ብለው የሚገኙ፣ ተከታይ ለማግኘት ወይም እርሱን ተመሥርተው ገንዘብ ለመሥራት አይችሉም የሚባሉትን ማየት ጀመርን። እና የቲክቶክ አልጎሪዝም እሱን ማየት ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ያደርሳል። ከፍ ብለው ከሚሠሩ ቪዲዮዎች አንፃር ምንም የሚመስለው ነገር አልነበረም።"
ቲክቶክ በአሜሪካ ተመሳሳይ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታ አለው፤ ቁጥራቸው የማይናቅ የቲክቶክ ማኅበረሰቦች ተፈጥረዋል። ቁጥራቸው ያልተነገረ አነስተኛ ይዘት ፈጣሪዎች እና ንግዶች በመተግበሪያው ዙሪያ መተዳደሪያቸውን መሥርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እምብዛም የማይታይ የስኬት ዓይነት ነው ቲክቶክ ላይ የተስተዋለው።
ለምሳሌ ኢንስታግራም በአጠቃላይ ትልቅ ተከታዮች ካላቸው አካውንቶች ይዘቶችን ለመውሰድ የበለጠ ተመቻችቶ የተሠራ ነው።
ቲክቶክ ደግሞ መደበኛ ተጠቃሚዎች ይዘቶቻቸውን እንዲያጋሩ በማበረታታት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቷል።
ቲክቶክ ሕንድ ውስጥ በታገደበት ወቅት፣ መንግሥት ከእሱ ጋር 58 ሌሎች የቻይና መተግበሪያዎችን አስቁሟል።
አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ታዋቂነት እያገኙ ያሉ የፋሽን መገበያያ መተግበሪያውን 'ሺን'ን ጨምሮ ያሉ ናቸው።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሕንድ ከመቶ በላይ ተጨማሪ የቻይና መተግበሪያዎችን ያገደች ሲሆን፣ በቅርቡ ከተደረገ ድርድር በኋላ ሺን ለተጠቃሚዎች ክፍት ሆኗል።
በአሜሪካም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። አዲሱ ሕግ ቅድመ ሁኔታን እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ሌሎች የቻይና መተግበሪያዎችን እንዲያስወግድ ዕድሎችን ይፈጥራል። ፖለቲከኞች ስለ ቲክቶክ የሚያነሱት የግላዊ መረጃ ጥበቃ እና የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሌሎች ተመሳሳይ ኩባንያዎች ላይም ሊተገበር ይችላል።
አንድ ታዋቂ መተግበሪያ ሲወገድ ሌሎች ክፍተቱን ለመሙላት ይጥራሉ።
የሕንድ የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ተንታኝ እና ናማ የተሰኘው ዜና ጣቢያ መሥራች ኒኪል ፓህዋ "ቲክቶክ እንደታገደ የብዙ ቢሊዮን ዶላር ዕድል ከፍቷል" ብሏል ።
"ክፍተቱን ለመሙላት በርካታ የሕንድ 'ስታርት አፖች' (የቴክኖሎጂ ጅምሮች) ብቅ ብቅ አሉ ወይም አቅጣጫቸውን ቀየሩ" ሲል ያስታውሳል።
የሕንድ ቴክኖሎጂ መገናኛ ብዙኃን ለወራት የዜና ርዕሶቻቸው ቺንጋሪ፣ ሞጅ እና ኤምኤክስ ታካ ታክ በሚባሉ አዳዲስ የሕንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ሆነ።
አንዳንዶች የቀድሞ የቲክቶክ ከዋክብትን ወደ መድረኮቻቸው በመሳብ እና ኢንቨስትመንቶችን እና የመንግሥትን ድጋፍ በማግኘታቸው የመጀመሪያ ስኬት አግኝተዋል።
አዲሶቹ መተግበሪያዎች የበላይነት ለማግኘት ሲታገሉ የሕንድ ማኅበራዊ ሚዲያ ገበያን ወደተለያዩ ማዕዘኖች ገፉት፤ ነገር ግን ያ የድኅረ-ቲክቶክ ወርቃማ ጊዜ ብዙም አልዘለቀም።
ከቲክቶክ እገዳ ከወራት በኋላ በነሐሴ 2020 ኢንስታግራም ሪልስ የተባለ አጭር የቪዲዮ ማሠራጫን አስተዋወቀ።
ዩቲዩብ ከአንድ ወር በኋላ ቲክቶክን አስመስሎ ሾርትስ የተባለ የቪዲዮ ማጋርያ አስተዋወቀ።
ኢንስታግራም እና ዩቲዩብ ቀድሞውንም በሕንድ ገበያ ውስጥ እግራቸውን ተክለዋል። በዚህም አዳዲስ ጀማሪዎች ይህንን ግዙፍ ገበያ ሰብሮ ለመግባት ዕድሉን አላገኙም።
በሕንድ የኢንተርኔት ፍሪደም ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ፕራቴክ ዋግሬ "ከቲክቶክ አማራጮች ጋር በተያያዘ ብዙ ሁካታ ነበር፣ ነገር ግን አብዛኛው በጊዜ ሂደት ደብዝዟል። በስተመጨረሻ፣ የበለጠ ተጠቃሚ የሆነው ምናልባት ኢንስታግራም ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አብዛኞቹ የሕንድ ቲክቶከሮች እና ተከታዮቻቸው ወደ ሜታ እና ጎግል መተግበሪያዎች እንደዞሩ ነበር ስኬት ፈገግ ብላ የተቀበለቻቸው።
ለምሳሌ የሕንድ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዋ ጌት፣ በቲክቶክ ላይ "የአሜሪካን እንግሊዘኛ" በማስተማር እና ሕይወትን ለመምራት ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት ዝናን ተጎናጽፋለች። ቲክቶክ በታገደበት ወቅት የተለያዩ አካውንቶች 10 ሚሊዮን ተከታዮች ነበራት።
በ2020 ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ጌት ስለወደፊት የሥራዋ ጉዳይ ስጋቷን አጋርታ ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላ ግን በኢንስታግራም እና በዩቲዩብ ላይ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮችን ማፍራት ችላለች።
ሆኖም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች እና ባለሙያዎች በድኅረ ቲክቶክ ሽግግር ውስጥ የሆነ ነገር እንደጠፋ ተናግረዋል።
ኢንስታግራም እና ዩቲዩብ የቲክቶክን ደንበኞች ነጥቀው ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን መተግበሪያው በሕንድ የፈጠረውን የቲክቶክ ስሜት መመለስ አልቻሉም።
በቲክቶክ ላይ ከመደበኛ ሕይወት የመጡ የየትኛውም የማኅበረሰብ አባላት፣ አለኝ የሚሉትን ሲያጋሩ በዚያም ዝናና ስም ሲሰበስቡ ቢታይም፤ ይህ ግን በኢንስታግራም እና ዩቲዩብ ላይ ሊደገም አልቻለም ሲሉ አስተየየታቸውን ያጠናክራሉ።
ቲክቶክ በአሜሪካ ከታገደ፣ የአሜሪካው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽታ ከሕንድ ጋር ተመሳሳይ መንገድ ሊከተል ይችላል።
እገዳው ከተጣለ ከአራት ዓመታት በኋላ ኢንስታግራም እና ዩቲዩብ ራሳቸውን የአጫጭር ቪዲዮች ጌታ አድርገው አቅርበዋል። ሊንክዲን እንኳን ሳይቀር የቲክቶክ ዓይነት ቪዲዮ እየሞከረ ነው።
የመተግበሪያው ተፎካካሪዎች ስኬትን ለማግኘት የቲክቶክን ባህል መፍጠር እንደማያስፈልጋቸው አረጋግጠዋል።
ልክ በሕንድ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ፣ ቲክቶክ በአሜሪካ ያመጣቸው የይዘት ፈጣሪዎች ሊጠፉ ይችላሉ። እንደ ተመራማሪዎች ግምት ከሆነ በአሜሪካ የሚፈጥረው የባህል መቃወስ ግን የበለጠ ጉልህ ይሆናል።
ለዚህም እንደ ምክንያት የተቀመጠው ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 ዓመት የሆናቸው አሜሪካውያን አንድ ሦስተኛ የሚጠጉት ዜናቸውን ከቲክቶክ ያገኛሉ የሚለው የፒው የምርምር ማዕከል ጥናት ውጤት ነው።
አሜሪካ ሕንድ በጊዜዋ ከነበራት 200 ሚሊዮን የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ያነሰ ቁጥር ቢኖራትም፣ ሕንድ ግን የ1.4 ቢሊዮን ዜጎቿ መኖሪያ ነች። ቲክ ቶክ በአሜሪካ ከአገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ፣ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ተዘግቧል።
"ሕንድ ቲክቶክን ስታግድ መተግበሪያው አሁን እንደሆነው ግዙፍ አልነበረም" ይላል ቲያጊ።
"ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ባህል አብዮትነት ተቀይሯል። አሁን በአሜሪካ መከልከሉ የበለጠ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።"
ኩባንያው በሕንድ ከወሰደው እርምጃ የተለየ ያደረገው የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው አዲስ ሕግ ፍርድ ቤት ወስዶ መሞገት ነው። ቲክ ቶክ በሕንድ ዕገዳ ወቅት ተመሳሳይ የሕግ መስመር መከተል ይችል የነበረ ቢሆንም ያንን ግን አልመረጠም።
የሕንድ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ በቻይና ውስጥ አለመኖሩ ቻይና ለሕንድ የዕገዳ ተግባር የሰጠችውን ምላሽ እንደሚጠበቀው አላደረገውም።
የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ግን ለአጸፋ ጥቃት ብዙ ዕድሎችን ይሰጣል። ቻይና የአሜሪካን ቴክኖሎጂዎች ሰርዛ፣ በአገር ውስጥ አማራጮች ለመተካት ከወዲሁ ጥረት ጀምራለች። የቲክቶክ ዕገዳ ያንን እንቅስቃሴ ሊያጠናክር ይችላል።












