ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍሪካ ደጋፊዎች ለቪዛ የሚያስይዙት ገንዘብ ቢቀርላቸውም በዓለም ዋንጫ ወቅት ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል
ከአምስት የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ደጋፊዎች የ2026ቱን የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለመከታተል ቲኬት እስከቆረጡ ድረስ ወደ አሜሪካ ለማምራት ለሚያስፈልጋቸው ቪዛ 15 ሺህ ዶላር ማስያዝ አይጠበቅባቸውም ተብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ረቡዕ ዕለት ከአልጄሪያ፣ ከኬፕ ቨርዴ፣ ከአይቮሪ ኮስት፣ ከሴኔጋል እና ከቱኒዚያ የሚጓዙ ደጋፊዎች ቲኬት ካላቸው ለቪዛ ተቀማጭ ገንዘብ ከማስቀመጥ ግዴታ ነፃ እንደሚሆኑ አረጋግጧል።
የአምስቱ አገራት ደጋፊዎች ባለፈው ዓመት በወጣው አሠራር ውስጥ ከተካተቱት 50 አገሮች መካከል ሲሆኑ እርምጃው የቪዛ ማራዘሚያዎችን ለመቀነስ የታሰበ እና በዋይት ሐውስ የተካሄደ ሰፊ የስደተኞች ቁጥጥር ዘመቻ አካል ነው።
በዚህ ዓመት ከሚደረገው የዓለም ዋንጫ 104 ጨዋታዎች መካከል 78ቱ በአሜሪካ በሚገኙ ሜዳዎች ላይ በመካሄዳቸው አሠራሩ ለደጋፊዎቹ መነሳቱ አስፈላጊ ነው።
ከሰኔ 4/2018 እስከ ሐምሌ 12/2018 ድረስ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ወደሚያዘጋጁት ውድድር ለመጓዝ ለሚፈልጉ አፍሪካውያን አሁንም ብዙ እንቅፋቶች ይጠብቃቸዋል።
ምን ተለወጠ?
ለቪዛ ተብሎ የሚጠየቀው የቦንድ መጠን ከ5 ሺህ ዶላር እስከ 15 ሺህ ዶላር ይደርሳል።
"የዓለም ዋንጫ ትኬቶችን ለገዙ ብቁ ደጋፊዎች የቪዛ ቦንዶችን አንስተናል" ሲሉ የአሜሪካ የቆንስላ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞራ ናምዳር ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ሆኖም ማስጠንቀቂያም አብሮት ተቀምጧል።
የቦንድ መስፈርቱ እንዲነሳ ለማድረግ ከአገሮቹ የተወጣጡ የቲኬት ባለቤቶች እስከ ሚያዝያ 7/2018 ድረስ በፊፋ ማለፊያ ስርዓት በበይነ መረብ መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።
ባለፈው ኅዳር ወር የተገለጸው ይህ ስርዓት የቲኬት ባለቤቶች ፈጣን የቪዛ ቀጠሮ እንዲያገኙ ለመርዳት የታሰበ ነው።
እነማን ከዚህ ውጭ ይደረጋሉ?
የቪዛ ቦንድ ገንዘብ መነሳቱን አስመልክቶ ፊፋ ባወጣው ማስታወቂያ ከዋይት ሐውስ ጋር ያለውን ትብብር "ስኬታማ፣ ክብረ ወሰን የሰበረ እና የማይረሳ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ለማድረግ" ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግሯል።
ወደ አሜሪካ ለመጓዝ እና ቡድናቸው ሲጫወት ለማየት ተስፋ ላደረጉ በርካታ ደጋፊዎች ግን ይህ በጣም የዘገየ ሊሆን ይችላል።
ከአምስቱ የአፍሪካ አገራት ባለቀ ሰዓት ትኬት የሚገዛ ሰው የቪዛ ተቀማጭ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅበታል የሚለውም ግልጽ አይደለም።
የአይቮሪ ኮስት እና የሴኔጋል ተጓዦች በትራምፕ አስተዳደር በተጣለ የጉዞ እገዳ ምክንያት ከፊል ገደቦች ይገጥሟቸዋል።
ከታህሳስ በፊት ቪዛቸውን ያላገኙ የሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ደጋፊዎች ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የጉብኝት ቪዛ አይሰጣቸውም።
የቦንድ ክፍያ ባልተጣለባቸው አገራት የሚገኙ ሰዎችም ቪዛ ለማግኘት ሲቸገሩ ይስተዋላል።
በቦስተን እና ፊላዴልፊያ ቡድናቸውን ለማየት ተስፋ ያደርጉ አንዳንድ ጋናውያን የአሜሪካ የመግቢያ ቪዛ እንደተከለከሉ ቢቢሲ ተረድቷል።
የአፍሪካ ደጋፊዎች ሌሎች መሰናክሎች
የበረራ፣ የምግብ እና መጠጥ እንዲሁም የአገር ውስጥ መጓጓዣ ዋጋ ጉዳይም ይነሳል።
ውድድሩ በሦስት የተለያዩ አገሮች የሚካሄድ በመሆኑ የአፍሪካ አገራት ደጋፊዎች ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል። አልጄሪያ፣ ኬፕ ቨርዴ እና ሞሮኮ ብቻ የምድብ ጨዋታዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ አሜሪካ ውስጥ ያከናውናሉ።
የግብጽ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት እና ሴኔጋል ደጋፊዎች በቶሮንቶ ወይም ቫንኩቨር ለሚደረጉ ጨዋታዎች ወደ ካናዳ ለመግባት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል። ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱኒዚያ ቢያንስ አንድ ጨዋታ በሜክሲኮ ያከናውናሉ።
ከዚያም ከፍተኛ ዋጋ የወጣላቸው የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶች ዋጋ ይነሳል።
ሐሙስ ዕለት በፊፋ ይፋዊ ድረ ገጽ በኩል ግብፅ ከቤልጂየም ለሚያደርጉት ጨዋታ 600 ዶላር የሚያወጡ የተወሰኑ መቀመጫዎች ነበሩ። ቀሪዎቹ የአፍሪካ ቡድኖች የሚያከናውኗቸው የመጀመሪያዎቹ 10 ጨዋታዎች የቲኬት ዋጋቸው ከ1,170 ዶላር በላይ ነው።
ለውድድሩ ዝግጅት አሁንም በመሸጥ ላይ የሚገኙት ጥቂት ቲኬቶች መካከል በሜክሲኮ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ለሚደረገው ጨዋታ 3,840 ዶላር ይጠየቃል።
የፊፋ የድጋሚ የቲኬት መሸጫ መድረክ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋነኑ ዋጋዎች ይታያሉ። ሁለት የምድብ ያላቸው ሦስት ትኬቶች ያሉት ሲሆን በሜክሲኮ ሲቲ የመጀመሪያውን ጨዋታ በሚያስተናግደው ስታዲየም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለው ዋጋ 34,500 ዶላር ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የአሜሪካ መንግስት ከደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች የሚመጡ ቱሪስቶች የአምስት ዓመት የማህበራዊ ሚዲያ ታሪካቸው እንደ መግቢያ ቅድመ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቋል። ይህም በዓለም ዋንጫ ወቅት ጎብኚዎችን ሊጎዳ የሚችል ሌላ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ነው።
የመብት ቡድኖች እንደዚህ ያሉ ፖሊሲዎች የመግቢያ ክልከላ፣ የእስር አደጋዎች፣ የጉዞ ገደቦች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ማጣሪያዎች፣ የዘር መድልኦ እና የክትትል መጨመርን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተጓዦችን አስጠንቅቀዋል።
10 የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፋቸው ክብረ ወሰን ቢሆንም ግን ቡድናቸውን በአካል ለመደገፍ የሚፈልጉ ሰዎች ከፍተኛ ገዘንዘብ ያስፈልጋቸዋል።