በአሜሪካ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የአየር ጉዞ ቅነሳ ምክንያት ከ1 ሺህ 400 በላይ በረራዎች ተሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ አየር መንገዶች የሚደረጉ በረራዎችን እንዲቀንሱ ከተነገራቸው በኋላ ቅዳሜ ዕለት ከአሜሪካ የሚነሱ፣ የሚገቡ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚደረጉ ከ1 ሺህ 400 በላይ በረራዎች ተሰረዙ።
የአየር ጉዞ ቅነሳ የተደረገው የአገሪቱ ምክር ቤት በመጪው በጀት ዓመት የመንግሥት አገልግሎትን ለመደገፍ በወጣው ረቂቅ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ምክንያት የፌደራል መንግሥት ተቋማት በመዘጋታቸው ነው።
እንደ የበረራ ተቆጣጣሪው ፍላይትአዌር ከሆነ አርብ ዕለት ከ7 ሺህ በላይ በረራዎች የዘገዩ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ቁጥሩ ዝቅ ብሎ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ በረራዎች መዘግየት አጋጥሟቸዋል።
ይህ የሆነው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ የፌደራል ተቋማት በተዘጉ ጊዜ ያለ ክፍያ እየሰሩ ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ድካም አጋጥሟቸዋል በሚል ሥራ በሚበዛባቸው 40 የአገሪቷ አየር ማረፊያዎች የአየር ጉዞ አቅምን በ10 በመቶ እንደሚቀንስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ካስታወቀ በኋላ ነው።
ሪፐብሊካን እና ዴሞክራቶች ከባለፈው ወር አንስቶ የቀጠለውን የፌደራል ተቋማት መዘጋትን ማስቆም በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በሃሳብ ተከፋፍለዋል።
ሪፐብሊካኖች እና ዴሞክራቶች በገንዘብ ድጋፍ መፍትሔ ላይ እስካሁን መግባባት ባለመቻላቸው በአገሪቷ ታሪክ ያጋጠመው ረዥሙ የፌደራል መንግሥት ተቋማት መዘጋት ቅዳሜ ዕለት 39ኛ ቀኑን ይዟል።
የምግብ ዕርዳታ ክፍያዎች መቋረጥ እና የበረራ መስተጓጎሎች ባጋጠሙበት ወቅት የተቋማት መዘጋት በአሜሪካውያን ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የምክር ቤት አባላት ተቋማቱ እንዲከፈቱ የሁለትዮሽ ድርድሮችን ለማካሄድ ዋሽንግተን ይገኛሉ።
የአሜሪካ አየር መንገድ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ የዋሽንግተን ዲሲ መሪዎች አፋጣኝ መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ አሳስቧል።
የኒው ጀርሲ ኒዋርክ ሊበሪቲ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም ረዥም መጉላላት ገጥሞታል።
ቅዳሜ ዕለት ከሰዓት ጀምሮ በአየር ማረፊያው የሚደርሱ አውሮፕላኖች በአማካይ ለአራት ሰዓታት መዘግየት ያጋጠማቸው ሲሆን፤ ከአየር ማረፊያው የሚነሱ ደግሞ በአማካይ ለሁለት ሰዓት ገደማ መዘግየት እንዳጋጠማቸው የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ገልጿል።
እንደ ፍላይትአዌር ከሆነ ቅዳሜ ዕለት በርካታ የበረራ መሰረዝ ያጋጠመው አየር ማረፊያ ደግሞ ቻርሎቴ ዳግላስ፣ ኒዎርክ ሊበሪቲ እና ቺካጎ ኦ ሃሬ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ናቸው።
ከጆን ኤፍ ኬኔዲ ፣ ሃርትስፊልድ ጃክሰን አትላንታ እና ላ ጋርዲያ የሚነሱ በረራዎችም ለሰዓታት መዘግየት አጋጥሟቸዋል።
ከሳምታት በኋላ የሚከበረው የምስጋና ቀን እየተቃረበ በመምጣቱም ወቅቱ በአሜሪካ በርካታ በረራዎች የሚደረጉበት ነው።
በዚህ የተቋማት መዘጋት ተግዳሮት የገጠማቸው የንግድ በረራዎች ብቻ ሳይሆኑ የግል ጄቶች ጭምር መሆናቸው ተገልጿል።
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የሚሰረዙ በረራዎችን ቁጥር በመጨመሩ በሚቀጥሉት ቀናት ችግሩ ይበልጥ ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።
ሐሙስ ዕለት ኤጀንሲው የበረራ ቅነሳው ቀስ በቀስ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቅሶ፣ አርብ ዕለት በ4 በመቶ የጀመረው ቅነሳ በሚቀጥለው ሳምንት 10 በመቶ እንደሚደርስ አስታውቋል።
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደሩ ተቋማት በተዘጉበት ጊዜ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከሥራ ሰዓት በላይ እየሰሩ በመሆናቸው ለደኅንነት ሲባል ቅነሳው አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
"ዋና ሠራተኞች የሆኑት የአየር ተቆጣጣሪዎች ያለ ክፍያ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ በዚህም ምክንያት በርካቶች በህመም ወጥተዋል ወይም የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገር ለማሟላት ሁለተኛ ሥራ ጀምረዋል።" ብሏል።
የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ያለ ክፍያ እንዲሰሩ አሊያም በግዳጅ እንዲወጡ ከተደረጉ ከ1.4 ሚሊዮን የፌደራል ሰራተኞች መካከል ይገኙበታል።
ተቋማት ዝግ በተደረጉበት ጊዜ ለአብዛኞቹ የትራንስፖርት ደኅንነት ኤጀንሲ 64 ሺህ ወኪሎች ክፍያ አልመፈፀሙም በአየር ጉዞው ላይ ሌላ ተፅዕኖ አስከትሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 በትራምፕ አስተዳደር ዘመን በነበረው የፌደራል መንግሥት ተቋማት መዘጋት 10 በመቶ የሚሆኑ የትራንስፖርት ደኅንነት ኤጀንሲ ሰራተኞች ያለ ክፍያ ከመስራት ይልቅ ቤታቸው መቀመጥን መርጠው ነበር።















