የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ፓርላማው በእሳት ተያያዘ

የኔፓል ፓርላማ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር ኬፒ ሻርማ ኦሊ በአገሪቱ በጸረ- ሙስና በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ በደረሰባቸው ጫና ከሥልጣን ለቀቁ።

በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ አለመረጋጋት እየተናወጠች ባለችው ኔፓል ተቃዋሚዎች በዋና መዲናዋ ካታማንዱ የሚገኘውን ፓርላማ እሳት ለኩሰውበታል።

በተጨማሪም በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ህንጻዎች እና የፖለቲካ አመራሮች መኖሪያ ቤቶች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

በአገሪቱ ከተቀሰቀሰው የጸረ ሙስና ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ከፖሊስ ጋር በነበረ ግጭት 19 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በርካቶች ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ማክሰኞ ዕለትም ተጨማሪ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።በዚህ ግርግር የተነሳ 900 ያህል ታራሚዎች በአገሪቱ ምዕራባዊ ግዛቶች ከሚገኙ ሁለት እስር ቤቶች ማምለጣቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

እነዚህ ተቃውሞዎች የተቀጣጠሉት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እገዳ መጣሉን ተከትሎ ነው።

እገዳው ሰኞ ዕለት ቢነሳም ተቃውሞው ወደ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተቀይሮ ተቀጣጥሏል።

የኔፓል ጦር አዛዥ፣ተቃዋሚዎች በአሁኑ ወቅት የተቀሰቀሰውን ቀውስ በመጠቀም በግል እና በሕዝብ ንብረት ላይ ዘረፋዎችን፣ ውድመቶችን እንዲሁም የእሳት ቃጠሎዎችን አድርሰዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁከቱ ከቀጠለ "የኔፓልን ጦር ጨምሮ ሁሉም የጸጥታ ተቋማት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ቁርጠኛ ናቸው" ያሉት የጦር አዛዡ፣ በአገሬው አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ እሳቸውን ማን እንደሚተካ ግልጽ አይደለም።

የመሪውን ኃላፊነት የሚተካ አካል እስካሁን አለመኖሩን ተከትሎም በቀጣይ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም። ሚኒስትሮችን ጨምሮ አንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንዳሉ ተነግሯል።

ተቃዋሚዎቹ በጸረ ሙስና ጥላ ሥር ከመሰባሰብ በስተቀር ምን እንደሚፈልጉ ግልጽ አላደረጉም።

ተቃውሞው ሕዝባዊ መልክ የያዘ ሲሆን የተደራጀ አመራር ያለው አይመስልም።

በፓርላማው የህንጻ መግቢያ ላይ በተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ ዙሪያም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መፈክሮችን ሲያሰሙ፣ሲደንሱ የታዩ ሲሆን በርካቶቹም የኔፓልን ሰንደቅ አላማ አንግበው ነበር።

አንዳንዶቹ ወደ ህንጻው ውስጥ ዘልቀው የገቡ ሲሆን ሁሉም መስኮቶች ተሰባብረዋል።

በፓርላማው ውጭ ተሰባስበው ከነበሩ መካከል የካትማንዱ ነዋሪ ሙና ሽሬሽታ አንዷ ስትሆን ሙስና በአገሪቱ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ችግር እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ በሥልጣን ላይ ያሉ ማናቸውም መውረድ ያለባቸው ጊዜ ነው። ምክንያቱም ለውጥ እንፈልጋለን" ብላለች።

"በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወርደዋል እናም ይህንን በማየታችን በጣም ደስተኛ ነን። ትግላችንንም እንቀጥላለን።ይህ ለውጥ ለኛ አዎንታዊ ነገር እንደሚያመጣ ተስፋ አደርጋለሁ" ስትልም አክላለች።

ባለፈው ሳምንት የኔፓል መንግሥት የመመዝገቢያ ቀነ ገደብ አሳልፈዋል በሚል 26 የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

እንዲዘጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በኔፓል ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አሏቸው።

መንግሥት ሃሰተኛ ዜናዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮች እና ማጭበርበሮችን ለመዋጋት እገዳውን ለመጣል ምክንያት ሆኖኛል ብሏል።

ወጣቶች ይህንን የመንግሥት እርምጃ "የመናገር ነጻነትን ለማፈን የተወሰደ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

እገዳው ሰኞ ምሽት በችኮላ ቢነሳም ተቃውሞው ሕዝባዊ መልክ ይዞ በፖለቲካ ልሂቃን ላይ አነጣጥሯል፤ ሃገሪቷንም ወደ ቀውስ ከቷታል።

የማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ከመታገዳቸው በፊት የፖለቲከኞች ልጆች የተንደላቀቀ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም በመንግሥት ባለስልጣናት የሚፈጸሙ ሙስናዎች ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ተደርገዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሰኞ እለት ፓርላማውን ለመቆጣጠር ሞክረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ግዛቶች የሰዓት እላፊ አዋጆችን ጥለዋል።

እነዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በማግሥቱ ማክሰኞ ቀጥለው፣ ተቃዋሚዎቹ የገዢው መንግሥት ጥምረት አካል የሆነውን የኔፓል ኮንግረስ ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት እና የመሪው ሼር ባህዱር ዲዩባን መኖሪያ ቤትን አቃጥለዋል።

የኮሚኒስት ፓርቲን የሚመሩት የ73 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኬፒ ኦሊ ቤትም ተቃጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷን ለአራት የሥልጣን ዘመን አስተዳድረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው የለቀቁት አሁን ለተከሰተው ቀውስ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሄ ለማምጣት እንደሆነ ገልጸዋል።