በርካቶች ለምን ማዕድ በጋራ ይቋደሳሉ? ምንስ ጥቅም አለው?

እንጀራ

ለበርካታ ሺህ ዘመናት የሰው ልጅ በማዕድ ዙሪያ መሰባሰቡን ቀጥሏል።

ብቻ ከመብላት ይልቅ ተሰባስቦ ማዕድ መቋደሱን የየዕለት ባህል አድርጎት ዘመናትን ተሻግሯል።

በሰርግ፣ በክርስትና፣ በእምነት በዓላት እንዲሁም በሐዘን ጊዜ ሳይቀር ማዕድ በጋራ ይበላል።

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ከጓደኞች ጋር ምግብ በጋራ በሬስቶራንቶች መመገብ፣ የተለያዩ በዓላትን በማዕድ ዙሪያ ማክበር አሁንም የዓለማችን እውነታ ናቸው።

ሆኖም ዓለማችን እየሄደችበት ባለው ከተሜነት እና ግላዊነት ጋር ተያይዞ እነዚህ በማዕድ ዙሪያ የሚደረጉ መሰባሰቦች እየቀነሱ ይመስላሉ።

በተለይም ቤተሰብ ተሰባስቦ የመብላት ባህል እየቀረ እንደሆነ የሚጠቅሱ ዘገባዎችም በተደጋጋሚ ሲወጡ ይታያል። ሆኖም ቤተሰብ በማዕድ ዙሪያ መሰባሰቡ የመቅረቱ ጉዳይ የወቅቱ ጉዳይ እንዳልሆነ እና በምዕራቡ ዓለም ቢያንስ 100 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ማስረጃዎች አሉ።

ማዕድ አብሮ መቋደስ ባህል ብቻ ነው? ወይስ ከዚህ በዘለለ ትርጉምን ያዘለ ነው።

ፒዛ አብረው እየተመገቡ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥንታዊው ሰው ጋር የቀረበ ዝምድና አላቸው የሚባሉት ቺምፓንዚ እና ቦኖቦስ የተሰኙ የዝንጀሮ ዝርያዎች በቡድን እንደሚመገቡ የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ተመራማሪዎች ተገንዝበዋል። ማዕድን በጋራ መመገብ ከአሁኑ የሰው ልጅ መምጣት የቀደመ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል።

ነገር ግን በአቅራቢያ ላለ ሰው ምግብ ማደል እና ተቀምጦ ማዕድ በጋራ መመገብ አንድ ዓይነት እንዳልሆነ በስዊድን የኡፕሳላ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ኒኮላስ ኑማን ያስረዳሉ።

“ምግብ ለሰዎች አድሎ አብረው ሳይቀመጡ እንዲሁም አለመመገብ ይቻላል” ይላሉ ባለሙያው።

ሆኖም የሰው ልጅ ማዕድ በጋራ ከመቋደስ ጋር በተያያዘ በርካታ ልምዶችን፣ ባህሎችን እና አሠራሮችን እየጨመረበት እዚህ ደርሷል።

ቺምንዚዎች በጋራ ሲመገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጅ ማዕድ የተጋራው በእሳት ዙሪያ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ቀደምቶቻችን መቼ ምግብ ማብሰል እንደተማሩ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። ግምቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ የሚለያዩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ከ1.8 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ያደርሱታል።

ይህም ወቅት የሰው ልጅ አድኖ ወይም ለቅሞ እና ሰብስቦ በሚበላበት ጊዜ ነው። ስለዚህ አድኖ ወይም ለቅሞ፣ ከዚያም እሳት አንድዶ እና አብስሎ መብላቱ ረዘም ያለ እና ፈታኝ ሥራ ከመሆኑ እና የበርካታ ሰዎችን ተሳትፎ ከመጠየቁ አንጻር በቡድን ሊያረጉት እንደሚችሉ ይታሰባል።

በምሽት ሰዓት ሁሉም በእሳት ዙሪያ ከተሰባሰቡ በኋላ አብረው ተቀምጠው ሊመገቡ እንደሚችሉ በእንግሊዝ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂካል አንትሮፖሎጂስት ሮቢን ደንባር ይገምታሉ።

በቀን ውስጥ ያሉ ሰዓቶች በምግብ ዙሪያ ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር ወርቃማ ዕድሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ደንባር ያስባሉ።

በማዕድ ዙሪያ አብሮ መሳበሰብ ላይ ያሉ መረጃዎች ምንም ይሁን ምን አብሮ ማዕድ መካፈል ከሰው ልጅ ደኅንነት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው አንድ ጥናት አመልክቷል።

ሮቢን ደንባር የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪዎችን ከሌሎች ጋር ምን ያህል ጊዜ ማዕድ እንደሚካፈሉ ጠይቀው በአውሮፓውያኑ 2017 አንድ ጥናት አጠናቅረው ነበር።

ከሰዎች ጋር በተደጋጋሚ ማዕድ አብሮ መካፈል በሕይወት ከፍተኛ እርካታን የሚያመጣ እንዲሁም ለመደጋገፍ እምነት የሚጣልባቸው በርካታ ጓደኞችን ከማፍራቱ ጋር የተሳሰረ ነው።

“መብላት በአዕምሮ ውስጥ ያለውን የሰዎችን ግንኙነት የሚቆጣጠረውን የኢንዶርፊን ሥርዓትን ያነቃቃል። በጋራ መመገብ ልክ በጋራ እንደ መሮጥ የኢንዶርፊን ተጽእኖውን መጠን በተመሳሳይ መንገድ ከፍ ያደርገዋል። የተለያዩ ተግባራትን እና እንቅስቃሴዎችን በጋራ ማድረግ የኢንዶርፊን መጠንን በሁለት እጥፍ ይጨምረዋል” ይላሉ።

በጋራ እየተመገቡ ያሉ ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰዎች ያበሰሉትን ምግብ በአንድነት በተመሳሳይ ጊዜ መመገብ የበለጠ እምነትን ሊጨምር እንደሚችል ሲንቲያ ግራበር እና ኒኮላ ትዋይሌይ የተሰኙት ጋዜጠኞች በአንድ የፖድካስት ዘገባቸው ላይ ጠቅሰዋል።

በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ ያደረጉላቸው በቺካጎ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ ጥናት ባልደረባ የሆኑት አይሌት ፊሽባች አብሮ መመመገብ “የኢንቨስትመንት መነቃቃት” እንደሚያመጣ ነግረዋቸዋል።

አብረው በተመገቡ ሰዎች ገንዘብ ለማውጣት የበለጠ ቀላል እንደሆነ ተመልክተዋል።

እንዲሁም ተመሳሳይ ምግብ አብረው የበሉ ሰዎች ካልበሉት ይልቅ በድርድሮች ላይ አጥጋቢ ፍጻሜ ላይ ለመድረስ ፈጣኖች እንደሆነ ይናገራሉ።

ፊሽባች እንደሚናገሩት የሰው ልጅ በምግብ ላይ ተመሳሳይ ጣዕም መኖሩ ከአሁኑ በበለጠ የጋራ እሴቶች እንዳሉት አመላካች ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን አብሮ መመገብ ሁልጊዜም አዎንታዊ ወይም ቀላል ላይሆን ይችላል።

በተለይም የተትረፈረፈ ድግስ በሚኖርበት ወቅት ሰዎች የሚበሉትን መመጠን እና መቆጣጠር ሊኖርባቸው ይችላል።

በተለያዩ ድግሶች ወቅት ዓይን ስለሚበዛ ይታዘቡኛል ወይም ሰው ምን ይለኛል በሚል በርካቶች የሚያነሱትን ምግብ መጠን ይጠነቀቃሉ።

በኢትዮጵያ አንዳንዶች በልተው ድግስ ላይ የሚገኙም አልታጡም።

እሱ ብቻ አይደለም ከቤተሰብ ጋር አብሮ ማዕድ መካፈል የሚመከረውን ያህል ግጭትም የሚያጣው አይደለም።

“ሰዎችን ብትጠይቁ ከጓደኞቻቸው እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር አብሮ ማዕድ መካፈል እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ። ነገር ግን ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር አብሮ መመገብ ቀላል ላይሆን ይችላል” ይላሉ ኒውማን።

“ማዕድም ቢሆን የበላይነት እና የቁጥጥር ስፍራ ስለሆነ” አለመግባባት የሚፈጠርበት አጋጣሚም ይኖራክ። ይህም ሰዎች የሚበሉትን የምግብ ዓይነት በተደጋጋሚ የሚተቹ ወይም ውፍረትን እያዩ ከምግቡ ጋር የሚያነጻጽር ስለማይታጡ እንደሆነ ኒውማን ያስረዳሉ።