በቼክ ከኢንተርኔት በተገኘ መመሪያ የጥርስ ህክምና ሲሰጥ የነበረ ሀሰተኛ ሀኪም ተከሰሰ

በቼክ ሪፐብሊክ በኢንትርኔት ባገኙት መመሪያ ለበርካቶች የጥርስ ህክምና ሲሰጥ የነበረ አንድ የ22 ዓመት ወጣት እና ሁለት ረዳቶቹ ክስ ተመሰረተባቸው።

እነዚህ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ተካሳሾች ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ፍቃድ ሳይኖራቸው ሃቭሊኮቭ ብሮድ በሚገኝ ቤታቸው ውስጥ ቀዶ ህክምና ጭምር ለማድረግ የሚያስችላቸውን ክሊኒክ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የከፈቱት።

በዚህ ክሊኒክ "አስፈላጊው የባለሙያ እውቀት ሳይኖራቸው" በርካቶችን 'እያከሙ' እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ጨምሮም የ22 ዓመቱ ሀሰተኛ ሀኪም ጥርስ መንቀል፣ ውስብስብ የሆነ የመንጋጋ ህክምና እንዲሁም ለጥርስ ህክምና የሚውል የሰመመን ህክምን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጥርስ ህክምና ሲሰጥ እንደነበር አስታውቋል።

ሀሰተኛው ሀኪም እና ረዳቶቹ በበርካታ ክሶች ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ እና በዚህም እስከ 8 ዓመት የሚደርስ እስር ሊጠብቃቸው እንደሚችል ፖሊስ ገልጿል።

ሆኖም ፖሊስ በሀሰተኛው ክሊኒክ ህክምና ያገኙ ሰዎች ቅሬታ ስለማቅረባቸው የገለጸው ነገር የለም።

በክሊኒኩ አንዲት የ50 ዓመት ሴት እንደነርስ ስትሰራ የነበረ ሲሆን ሌላ የ44 ዓመት ግለሰብ ደግሞ ለጥርስ ህክምና የሚውሉ ምርቶችን ሲያዘጋጅ ነበር።

ህገ ወጡ ክሊኒክ በሠራባቸው አመታት በርካታ ታካሚዎችን ያስተናገደ ሲሆን አራት ሚሊዮን የቼክ ሪፐብሊክ ገንዘብ ወይም 185 ሺህ ዶላር ማግኘቱንም ፖሊስ ጠቁሟል።

"በክሊኒኩ ውስጥ እንደ ነርስ የምትሰራው ሴት የሰመመን ህክምና መስጠት ብቻ ሳይሆን ለጥርስ ህክምና የሚውሉ በርካታ ግብዓቶችን ታገኝ ነበር" ብሏል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ።

"የ22 ዓመቱ ወጣት በቂ የባለሙያ ዕውቀት ሳይኖረው በክሊኒኩ እንደ ጥርስ ሃኪም ሲሰራ ቆይቷል" ሲሉም አክሏል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ የሆነችው ሚቼላ ሌብሮቫ የህክምናው ላይ ታካሚዎች ቅሬታ አቅርብ እንደሆነ ተጠይቀው ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ሶስቱም ግለሰቦች ቀደም ብለው የታሰሩ ሲሆን በዚህ ሳምንት ክስ ተሰመስርቶባቸዋል። ክሶቹም በህገ ወጥ ንግድ በመሳተፍ፣ ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ ለማስመስል መሞከር፣ የጥቃት ሙከራ፣ ዕጽ ዝውውር እና ስርቆት ናቸው።

በዚህም ሁሉም ጥፋተኛ ተብለዋል።

የቼክ የጥርስ ሃኪሞች ማኀበር ኃላፊ ሮማን ሳምኩለር በዓመት ውስጥ በአማካኝ 10 ሰዎች ሀሰተኛ የጥርስ ሃኪም እንዳጋጠማቸው ሪፖርት እንደደረሰው ተናግሯል።

የቼክ ፓርላማ ባለፈው ዓመት ከአውሮፓ ህብረት ውጪ ያሉ ሀገራት ሃኪሞች በቼክ እንዲሰሩ የሚያስችል ህግ አጽድቆ ነበር።