ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በሐማስ ታግተው የተገደሉ ዜጎቿን አስከሬን ልትረከብ ነው
ሃማስ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 2023 በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ካገታቸው በኋላ ሕይወታቸው ያለፈውን የአራት እስራኤላውያን ታጋቾች አስከሬን ሊያስረክብ ነው።
ሃማስ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ እናት እና ሁለት ልጆቿን እንደሚያካትት የተነገረ ሲሆን፣ የቤተሰቡ እጣ ፈንታ በእስራኤላውያን ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።
የመጨረሻው ልጅ ክፊር የዘጠኝ ወር ልጅ ነበር።
ሃማስ ከሚያስረክባቸው አስከሬኖች መካከል አራተኛው የ84 ዓመቱ አንጋፋ የሰላም ታጋይ የኦዴድ ሊፍሺትዝ ነው ብሏል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ወር ከተጀመረ በኋላ ቡድኑ የሞቱትን ታጋቾች ሲያስረክብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "የመላው ሕዝብ ልብ በሐዘን ደምቷል" ካሉ በኋላ፣ እስራኤል ከ"ጭራቆች" ጋር እየተፋለመች ነው ሲሉ አክለዋል።
በሕይወት ያሉ ስድስት ታጋቾች ቅዳሜ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተነግሯል።
ምንም እንኳ ዜናው፣ በእስራኤል መንግሥት ባይረጋገጥም የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት፣ የ33 ዓመቷ ሺሪ ቢባስ እና ልጆቿ (አሁን አምስት እና ሁለት ዓመት እድሜ ይሆናቸዋል) መሞታቸው በመላ ሀገሪቱ ሀዘንን ቀስቅሷል።
መንግሥት የሟቾችን ስም ከፎረንሲክ ምርመራ በኋላ አረጋግጣለሁ።
በእስራኤል የሚገኙ የቢባስ ቤተሰቦች በሰጡት መግለጫ "አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነን" ሲሉ አክለውም "ትክክለኛ ማረጋገጫ እስክናገኝ ድረስ ጉዟችን አያበቃም" ብለዋል።
ሐማስ እስካሁን የለቀቃቸውን ታጋቾችን ያስረከበው ለቀይ መስቀል ሲሆን አሁን የአራቱ አስከሬኖች ለማን እና እንዴት አንደሚያስረክብ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የእስራኤል መንግሥት ረቡዕ ምሽት ላይ በሰጠው መግለጫ "ግልጽ መሆን አለብን፤ በሚለቀቁበት ወቅት የሚኖር ማንኛውም ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ድርጊት ተቀባይነት የለውም" ብሏል።
ሃማስ ታጋቾችን ለቀይ መስቀል ተወካዮች አሳልፎ ከመሰጠቱ በፊት በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ለፊት በማቅረብ ማሳየቱ ውግዘት አስከትሎበታል።
ምንም እንኳ እስካሁን ይፋዊ ማረጋገጫ ባይገኝም ሺሪ፣ ክፊር እና ወንድሙ ኤሪኤል እንዴት እንደሞቱ አይታወቅም።
ሃማስ በኖቬምበር 2023 እስራኤል ባደረገችው የአየር ጥቃት መገደላቸውን ገልጿል።
በወቅቱ የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል የነበረው ቤኒ ጋንትዝ ስለጉዳዩ ምንም ማረጋገጫ እንደሌለ ተናግሯል።
ቤተሰቡ ከአባታቸው ያርደን ጋር ከኪቡትዝ ኒር ኦዝ የተወሰዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በመግባት የተለያዩ ግለሰቦችን፣ የጸጥታ ኃይሎች ጣቢያዎችን እና በሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር።
በጥቃቱ አብዛኞቹ ንፁኀን የሆኑ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
እስራኤል በምላሹ በሃማስ ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተች ሲሆን ይህም ቢያንስ 48,297 ፍልስጤማውያን፣ በተለይ ሰላማዊ ዜጎች መገደሉን፣ በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
የ35 ዓመቱ ያርደን ቢባስ የካቲት 1 በነበረው የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ወቅት ተለቅቋል።
ኦዴድ ሊፍሺትዝ የተባለ ጡረታ የወጣ ጋዜጠኛም ከኒር ኦዝ ከዚች ሚስት ዮቼቬድ ጋር ተወስዷል።
የሰማንያ አምስት ዓመቷ ሴት ከሁለት ሳምንት በፊት ተለቅቃለች።
ኦዴድ ሊፍሺትዝ ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ በሃማስ እጅ ታግቶ ነበር።
እኤአ ከጥር 19 ጀምሮ በስራ ላይ በዋለው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት የታጋቾችን አስከሬን ለመስጠት ስምምነት ላይ ደርሷል።
እስራኤል በሃማስ እጅ ሳሉ የተገደሉ ታጋቾች ቁጥር ስምንት እንደሚሆኑ አረጋግጣለች።
የተኩስ አቁም በተጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ 6 ሳምንታት መጨረሻ ላይ ሃማስ 33 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በምላሹ 1,900 የሚጠጉ እስረኞች ለመልቀቅ ተስማምተዋል።
በዚህ ወር መጀመርያ ላይ ቀሪዎቹ ታጋቾች የሚፈቱበት እና ጦርነቱ በዘላቂነት የሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ንግግር ይጀመራል ቢባልም እስካሁን የታየ እንቅስቃሴ የለም።
ሃማስ እስካሁን 24 ታጋቾችን ሲለቅ፣ እስራኤል ከ1,000 በላይ እስረኞች አስረክባለች።
በጥቅምት 7 የተወሰዱ ሰባ ሰዎች አሁንም በጋዛ ታግተው ይገኛሉ።
ከአስር አመታት በፊት የተወሰዱት ሌሎች ሶስት ታጋቾችም በእስር ላይ ናቸው።
አሁንም በጋዛ ከሚገኙት ታጋቾች መካከል ግማሽ ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።