የአሜሪካ የመድኃኒት አስተዳደር ለክብደት መቀነሻ ለሚውል ኪኒን ማረጋገጫ ሰጠ

መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ክብደትን ለመቀነስ ለሚውለው ዊጎቪ ኪኒን ማረጋገጫ መስጠቱን የመድኃኒት ተቋሙ ኖቮ ሞርዲስክ አስታወቀ።

ዊጎቪይ ኪኒን ከመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣኑ ማረጋገጫ የተሰጠው በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ኪኒን ሲሆን ለክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች አዲስ ምዕራፍን ከፍቷል።

ኪኒኑን የሰራው የዴንማርኩ መድኃኒት አምራች ተቋም ኖቮ ኖርዲስክ፣ በቀን አንድ ጊዜ የሚወሰደው ይህ ኪኒን ከዚህ ቀደም በመርፌ መልክ ከሚወሰደው ይልቅ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ገልጿል።

በመርፌ መልክ እንደሚወሰደው ሁሉ ኪኒኑ ክብደት ለመቀነስ ይረዳልም ብሏል።

ኪኒኑ ማረጋገጫ እንዳገኘ የተሰማው ክብደት ለመቀነስ የሚረዳው ዊጎቪ በፌደራል የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ማረጋገጫ ከተሰጠው በኋላ ነው።

ሌሎች ክብደትን ለመቀነስ የሚረዱ እንደ ኦዝምፒክ ያሉ መድኃኒቶች ያሉ ሲሆን በዋናነት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ዓይነት 2 የስኳር ሕመም በሽታን ለማከም ነው።

ቢቢሲ የፌደራል የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስተያያት እንዲሰጥ ጠይቋል።

ኖቪ ኖርዲስክ ሙከራውን በሚያካሂድበት ጊዜ ዊጎቪ ኪኒን 16.6 በመቶ የሚሆን አማካኝ የክብደት መቀነስ ማሳየቱን ሰኞ ዕለት ገልጿል።

በሙከራው ላይ ከተሳተፉ 1 ሺህ 300 የሚሆኑ ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑትም 20 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ክብደት ቀንሰዋል ብሏል።

ኪኒኑ መጭው ወር በአሜሪካ ይፋ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።

የኖቪ ኖርዲስክ ዋና ኃላፊ ማይክ ዳውስትዳር " በቀን አንድ ጊዜ የሚወሰደው ኪኒን ለታማሚዎች ለአወሳሰድ አመቺ ሲሆን ከዚህ ቀደም ዊጎቪ መርፌን በመጠቀም ክብደታቸውን ለመቀነስ እንደሚችሉት ሁሉ ይህም ክብደታቸውን ለመቀነስ ይረዳቸዋል" ብለዋል።

በኪኒን መልክ የተሰራው ዊጎቪ፣ ኖቫ ኖርዲስክ የአክሲዮኖች ቅናሽ እና የትርፍ ማሽቆልቆል ማስጠንቀቂያ ካጋጠመው ከአንድ ዓመት በኋላ የመድሃኒት ገበያውን ሊጨምረው ይችላል።

ኩባንያው በክብደት መቀነስ ገበያ እንደ ኢሊ ሊሊይ ካሉ ተቀናቃኙ መድሃኒት አምራቾች ከባድ ውድድር ገጥሞታል።

ኖቮ ኖርዲስክ መድሃኒቱ ማረጋገጫ ማግኘቱ ከተሰማ በኋላ በኒው ዮርክ ገበያ በሰዓታት ውስጥ ያለው ድርሻ 10 በመቶ ገደማ ጨምሯል።