የኢንተርኔት አገልግሎትን መልሶ ያስጀመረው ታሊባን የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን ገደበ

ካቡል የሚገኝ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ

የፎቶው ባለመብት, QUDRATULLAH RAZWAN/EPA/Shutterstock

በአፍጋኒስታን በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በሚተላለፉ ይዘቶች ላይ ክልከላ መጣሉን የቢቢሲ ምንጮች ገለጹ።

ታሊባን በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ኤክስ ላይ የሚተላለፉ ይዘቶች እንዲገደቡ መወሰኑን በአፍጋኒስታን ኮምንኬሽንና መረጃ ሚኒስቴር የሚሠሩ የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

የትኞቹ ይዘቶች ላይ ክልከላው እንደተጣለ ግልጽ አይደለም።

በካቡል የሚገኙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በፌስቡክ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን መመልከት አልቻሉም።

ኢንስታግራም ላይም ገደብ እንደተጣለ ተናግረዋል።

የታሊባን መንግሥት ተቋርጦ የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት መልሶ ያስጀመረው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ኢንተርኔት ዳግመኛ መጀመሩ ሕዝቡን አስደስቷል። ብዙም ሳይቆይ ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶች ክልከላ ተጥሏል።

የታሊባን መንግሥት ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ "በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ኤክስ ይዘቶች ላይ ገደብ ተጥሏል። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ነው ዕገዳው የተተገበረው። ኢንተርኔት ላይ አጠቃላይ ማዕቀብ እንደማይጣል ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

ስለተጣለው ክልከላ ከታሊባን በይፋ ማብራሪያ አልተሰጠም።

የኢንተርኔት አቅርቦትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ "የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ክልከላው መጣሉን አረጋግጧል። ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሆነ ተብሎ የተጣለ ዕገዳ ነው" ብሏል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው በተንቀሳቃሽ ስልኮች የኢንተርኔት አቅርቦት መቆራረጥ ተስተውሏል።

በምሥራቃዊ የናንጋራር ግዛት የሚሠራ የመንግሥት ተቀጣሪ እንዳለው፤ ፌስቡክ ቢከፍትም ምሥሎችን መመልከት ግን አልቻለም። የኢንተርኔት ፍጥነት መቀነሱንም ገልጿል።

በደቡባዊ የካንዳሀር ግዛት የሚኖረው ነጋዴም ፌስቡክ እና ኢንስታግራም "በጣም ማዝገማቸውን" ተናግሯል።

ታሊባን ከዚህ ቀደም ለምን ኢንተርኔት እንደተዘጋ ባይገልጽም፣ የሰሜናዊ ባላክ ግዛት አገረ ገዢ ቃል አቀባይ "ኢንተርኔት የተዘጋው ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ለማገድ ነው" ብለዋል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ በሸሪዓ ሕግ መሠረት የተለያዩ ክልከላዎች ሲጥል ቆይቷል።

አፍጋኒስታናውያን ሴቶች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ኢንተርኔት ከተቀረው ዓለም ጋር የሚገናኙበት ድልድይ ነበር።

ታሊባን ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች እንዳይማሩ አግዷል። ሴቶች የሚሰማሩባቸውን የሥራ ዘርፎችም ተገድበዋል።

ታሊባን በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍት በዩኒቨርስቲዎች ማስተማሪያ እንዳይሆኑ ማገዱም አይዘነጋም።