በቱርክ ኢስታንቡል በተፈጸመ “የሽብር” ጥቃት 6 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቱርክ ኢንስታንቡል መሃል ከተማ በተፈጸም “የሽብር” ጥቃት 6 ሰዎች መገደላቸውን እና 81 ሰዎቸ መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ትናንት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 10 ሰዓት አካባቢ ያጋጠመው ፍንዳታ በሴት የተፈጸመ የሽብር ጥቃት ነው ሲሉ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉአት ኦክታይ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ደግሞ ቦንቡን በማስቀመጠ የተጠረጠረ ሰው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መግባቱን ገልጸው ለፍንዳታው የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲን (ፒኬኬ) ተጠያቂ አድርገዋል።
ታክሲም ስኩዌር ተብሎ በሚጠራው የገበያ ስፍራ አደጋውን በማድረስ የተጠረጠረ ሰው በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተስምቷል።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ጥፋተኛ ይቀጣል ብለዋል። ከጥቃቱ በኋላ መግለጫ የሰጡት ኤርዶሃን፤ ፍንዳታውን አውግዘው የሽብር ጥቃት በከተማዋ ሊፈጸም እንደሚችል ምልክቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
የፍትሕ ሚንስትሩ ቤኪር ቦዛዳግ ደግሞ ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ አንዲት ሴት ለ40 ደቂቃዎች ከተቀመጠችበት ቦታ እንደተነሳች ፍንዳታ ማጋጠሙን ገልጸዋል።
ፒኬኬ የተሰኘው የሚሊሻ ቡድን ከቱርክ ግዛት ላይ ነጻ የኩርዲሽ አስተዳደር ለመመስረት ይፋለማል። ቱርክ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ይህን ቡድን አሸባሪ ሲሉ ፈርጀውታል።
ፍንዳታው ወዳጋጠመበት ቦታ ያቀናቸው የቢቢሲ ጋዜጠኛ በአካባቢው በርካታ የፖሊስ አባላት መሰማራታቸውን፣ ሄሊኮፍተሮች አካባቢውን ከላይ ሆነው ሲቃኙ እና በርካታ ቁጥር ያላቸው አምቡላንሶች ደግሞ በስፍራው ሲመላለሱ ተመልክታለች።
ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ የነበረች አንድ የዓይን እማኝ፤ “ሰዎች ሲሯሯጡ እና በነበርኩበት ካፌ በኩል ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ብዙ የተጎዱ ሰዎች አይቻለሁ” ብላለች።
ፍንዳታው ካጋጠመበት 50 ሜትር ርቆ የነበረው ሴማለ ዱኒዘሲ ለኤኤፍፒ ሲናገር፤ “ጥቁር ጭስ ነበር። የፍንዳታው ድምጽ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ጆሮ የሚደፍን ነበር” ብሏል።
በቱርክ ያልተለመደ የተባለው ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ በርካታ አገራት ከቱርክ ጎን እንደሚቆሙ መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
አሜሪካ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገሯ ቱርክ ጋር በጸረ-ሽብር ዘመቻ እንደምትተባበር ገልጻለች።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በትዊተር ገጻቸው ላይ በቱርክ ቋንቋ፤ “ሕመማችሁን እንጋራለን . . . በሽብር ላይ በሚደረገው ትግል አብረናችሁ አለን” ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚየር ዜሌንስኪ በተመሳሳይ በተርኪሽ ቋንቋ፤ “ወዳጅ የሆነው የቱርክ ሕዝብ ህመም እኛንም ይሰማናል” ብለዋል።
ፓኪስታን፣ ጣሊያን እና ግሪክ በተመሳሰይ ጥቃቱን ተከትሎ ለቱርክ አጋርነታቸውን የገለጹ አገራት ናቸው።












