በሽብር የተከሰሰው ቱኒዚያዊ እግር ኳስ ተጫዋች እራሱን በእሳት አቃጠለ

በኖዛር ኢሱዊ ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሰዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በኖዛር ኢሱዊ ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሰዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ

ቱኒዚያዊው እግር ኳስ ተጫዋች ኖዛር ኢሱዊ “በፖሊስ ተፈጸመብኝ ያለውን በደል” በመቃውም እራሱን በእሳት በማቃጠሉ በደረሰበት ጉዳት መሞቱን ቤተሰቦቹ ተናገሩ።

በበይነ መረብ ላይ በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ተጫዋቹ ከአንድ የፍራፍሬ ነጋዴ ጋር ከተፈጠረ አለምግባባት በኋላ በፖሊሶች በሽብር ድርጊት መከሰሱን እየጮኽ ሲናገር ታይቷል።

በሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ “በእሳት ተቃጥሎ ለመሞት” በእራሱ ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ሲናገርም ተሰምቷል።

የ35 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች ቀብር አርብ ዕለት በትውልድ ከተማው ሃፉዝ ውስጥ ሲፈጸም፣ በቁጣ ግጭት ተከስቶ እንደነበር የቱኒዚያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኖዛር ኢሱዊ የሙዝ ዋጋ በመናሩ መግዛት አለመቻሉን በመግለጽ ቅሬታውን በማሰማቱ ፖሊሶች ሽብርተኛ በማለት እንደከሰሱት ተነግሯል።

በፌስቡክ ገጹ ላይም “ሙዝ ለመግዛት ከሚገባው በላይ ከጠየቀኝ ነጋዴ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት፣ ፖሊስ ጣቢያ በሽብር ወንጀል ተከስሽላሁ። በሙዝ ዋጋ ላይ ቅሬታ ማቅረብ ሽብርተኛ ያስብላል... ይህንን መቋቋም አልችልም። ቅጣቱ ዛሬ መፈጸሙን ጨቋኙ መንግሥት ይወቅ” በማለት አስፍሮ ነበር።

ይህንንም በመቃወም ኢሱዊ እራሱን በእሳት አቃጥሎ ገድሏል።

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተቆጡ ለቀስተኞች በፖሊሶች ላይ ድንጋይ በመወርወራቸው አስለቃሽ ጋዝ ተተኩሶባቸዋል።

የአራት ልጆች አባት የሆነው ኖዛር ኢሱዊ በቱኒዚያ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ ዩኤስ ሞናስቲር ለተባለው ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ነበር።

ወንድሙ ለጋዜጠኞች እንደተነገረው ኢሱዊ በከፍተኛ ሁኔታ የመቃጠል ጉዳት ስለደረሰበት፣ ሐኪሞች ሕይወቱን ሊያተርፉ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የእግር ኳስ ተጫዋቹ ድርጊት ከ13 ዓመት በፊት በቱኒዚያ እና በአረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት ጅምሬ የሆነውን እራሱን በእሳት ያቃጠለውን የጎዳና ላይ ነጋዴ ሞሐመድ ቡአዚዝን ያስታወሰ ነው።

ከቡአዚዝ ሞት በኋላ በቱኒዚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀጣጥሎ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዚን አል-ኤቢዲን ቤን አሊ ሥልጣናቸውን ጥለው ለመሰደድ አብቅቷቸዋል።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ካይስ ሳኢድ ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩን አባረው የአገሪቱን ፓርላማ ከበተኑ በኋላ በአገሪቱ ውዝግብ ተፈጥሯል። ፕሬዝዳንቱ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር አዲስ ሕገ መንግሥት ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ነው።

የእግር ኳስ ተጫዋቹን ኖዛር ኢሱዊ ሞትን በተመለከተ የቱኒዚያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።