54 ኮሌጆች የተቀበሏት እና 1.3 ሚሊዮን ዶላር የትምህርት ዕድል ያገኘችው አሜሪካዊት ምክር

ዳያ ብራውን

የፎቶው ባለመብት, Daya Brown

በአሜሪካ 54 ኮሌጆች የተቀበሏት እና የ1.3 ሚሊዮን ዶላር የትምህርት ዕድል ያገኘችው ታዳጊ እንዴት ይህንን እንዳሳካች ለቢቢሲ ተናግራለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ በሰው ልጅ አኗኗር ላይ ስር ነቀል ለውጥን አስከትሏል። በዚህም ምክንያት ሚሊዮኖች ትምህርት ቤት ዝር እንዳይሉ ተገድደው በየቤታቸው ተወስነው አማራጭ በሆነው የዲጂታል መንገዶች እንዲማሩ ሆነዋል።

በአትላንታ ጆርጂያ በሚገኘው ዌስት ሌክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው የዳያ ብራውንም ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።

በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርቷን በኢንተርኔት በምትከታተልበት ወቅት ነበር በቀጣይ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል የምትፈልግባቸውን ኮሌጆች ዝርዝር ማውጣት የጀመረችው።

“ለእኔ ማምለጫ መንገድ ነበር። ለራሴም አንድ ቃል ገባሁ። ኔትፍሊክስ የሚባል ነገር በጭራሽ ላለመልከት እና ዕቅዴን ማሳካት አለብኝ አልኩ” በማለት ዳያ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ቆይታዋ ለጋዜጠኝነት፣ ለግጥም እና ለክርክር ፍቅር ያላት ዳያ ከመደበኛ ትምህርት ውጭ በሆኑ ተግባራት መሳተፏ የወደፊቷን ቀድማ እንድታቅድ ረድቷታል።

“ተረጋግቼ እንዳስብ ረድቶኛል። ዓለም በወረርሽኙ ምክንያት ቆማለች፣ ነገር ግን የወደፊቱንም ማሰብና የማቀሣው ጊዜም ይኸው ወቅት ነበር” ትላለች።

መማር የምትፈልግባቸውን ዩኒቨርስቲዎች ዝርዝር ስታዘጋጅ አብራም የነጻ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እየፈለገች እና እየጠየቀችም ነበር።

“ዩኒቨርስቲ ከፍሎ መማር ለእኔ የማይታሰብ አማራጭ ነበር” የምትለው ዳያ፣ ውድ የሆነውን የዩኒቨርስቲ ትምህርቷንም ለመደገፍ በሚል ቤተሰቦቿን ጭንቀት ውስጥ ማስገባት አልፈለገችም።

በትዕግስት መጠበቅ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአራት ወራት በኋላ ተቀብለንሻል የሚሉ ደብዳቤዎችን ከዩኒቨርስቲዎቹ ይደርሳት ጀመር።

በዚህም “ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ተቀበሉኝ፣ እንዲሁም የ1.3 ሚሊዮን ዶላር የነጻ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ከተለያዩ ቦታዎች አግኝቻለሁ” ስትል ዳያ ትናገራለች።

ነገር ግን ምርጥ ካለችው ዩኒቨርስቲ ተቀብለንሻል የሚል ደብዳቤ ሲደርሳት ሌሎቹን ውድቅ ማድረግ ነበረባት።

“ከ70 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ማመልከቻ አስገብቻለሁ። ነገር ግን የዱክ ዩኒቨርስቲ ሲቀበለኝ ሌሎቹን ተውኳቸው” ብላለች።

በመጨረሻም የ18 ዓመቷ ዳያ በዱክ ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርቷን ለመቀጠል የወሰነች ሲሆን፣ ከወራትም በኋላ በቪዡዋል እና በሚዲያ ጥናቶች የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቷን ትጀምራለች።

ዩኒቨርስቲውም የአንድ ዓመት የገንዘብ ድጋፍ የነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቷታል። እንዲሁም በቱጃሩ ቢል ጌትስ ስም የተቋቋመው የጌትስ ስኮላርሺፕን ለማግኘት የመጨረሻዋ ዕጩ ሆናለች።

“ለእኔ የጌትስ የነጻ የትምህርት ዕድል በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከፍተኛ የትምህርት ዕድሎች አንዱ ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲ ትምህርት እስኪጠናቀቅ ለአራት ዓመት የትምህርት ክፍያ ይከፍላሉ" ስትል ተናግራለች።

እንደዚህ በዓይነቱ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ለማመልት አስቸጋሪው ምን ይሆን?

ለበርካቶች አሰልቺው በርካታ ገጾች ያሏቸውን ተደጋጋሚ ቅጾች መሙላት ቢሆንም፣ የሚገርመው ግን ለዳያ ግን ከባዱ ይህ አልነበረም።

“በጣም ከባዱ ነገር መጠበቁ ይመስለኛል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ትዕግስትን አስተማረኝ” ትላለች።

በአሁኑ ወቅት ዳያ ሌሎች ተማሪዎች በሚፈልጓቸው ዩኒቨርስቲዎች ገብተው የትምህርት ግባቸውን እንዲያሳኩ ለመርዳትም እየጣረች ትገኛለች።

“ለሌሎች ሴቶች እንዲሁም ጥቁር ተማሪዎች ‘እሷ ይህንን ማድረግ ከቻለች እኔም ማሳካት እችላለሁ’ በሚል እንዲነሳሱ እና እንደሚያበረታቸው ተስፋ አደርጋለሁ” ስትልም ተናግራለች።

ዳያ ብራውን ከቤተሰቦቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Daya Brown

ዩኒቨርስቲዎች እንዲቀበሉን ማመልከቻችን ምን ማካተት አለበት? የዳያ ጠቃሚ ምክሮች

ዳያ በእነዚህ ነጻ የትምህርት ዕድል ለማግኘት ለበርካታ ዩኒቨርስቲዎች በምታመለክትበት ወቅት ስለረዷት ሦስት ጉዳዮች ምክሯን ትለግሳለች፡

  • እርዳታ ጠይቁ ፡ “ከዩኒቨርስቲ አማካሪዎች እንዲሁም የሙያ አሰልጣኞች ጋር ተነጋገሩ። አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎቹ ከየዩኒቨርስቲዎቹ ምን ዓይነት እርዳታ ሊያገኙ እንደሚችሉም ሆነ ስላሉ ነገሮች ለመጠየቅ ይፈራሉ። በየዩኒቨርስቲዎቹ ለእነዚህ ጉዳዮች የተመደቡ ሰዎች አሉ፤ ብቸኛ ሥራቸውም ተማሪዎችን መርዳት ነው።”
  • የተደራጀ ይሁኑ፡ “ሂደቱ በጣም ከባድ፣ አስጨናቂ እንዲሁም ትርምስምሱ የወጣ ሊሆን ይችላል። ሁሉንም ማመልከቻዎች የሚዘረዝሩበትን መንገድ ያቀናጁ። ለአንድ ዩኒቨርስቲ የጻፉትን ማመልከቻ ወይም ደግሞ ጽሁፍ ከተወሰነ ማሻሻያ ጋር ለሌላ ዩኒቨርስቲ እንደገና መጠቀም ይቻላል።”
  • ከመደበኛ ትምህርት ውጭ ያለዎትን ተግባራት ይጠቀሙበት: "ከመደበኛ ትምህርት ውጭ ያለዎት እንቅስቃሴዎች በዩኒቨርስቲዎች ዘንድ እርስዎ ስላለዎት ማንነት መስካሪዎች ናቸው። ዩኒቨርስቲዎች ስለ ማንነትዎ በጥልቀት ለመረዳት ይፈልጋሉ። እነዚህንም ተግባራት በመጠቀም ስለ ማንነትዎ የበለጠ ለመግለጽ እንዲሁም የወደፊቱንም ዕቅድ ለማሳወቅ ይጠቀሙበት።”

ዳያ አሁን የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ለመጀመር ዋዜማው ላይ ብትሆንም አሁንም በተለያዩ ተግባራት ተደምጣለች።

በአሁኑ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች ባቋቋመችው ፕሮዳክሽን ኩባንያ እየሰራች ነው።

የኩባንያው አላማ በታዳጊዎች እና በወጣቶች የተጻፉ እንዲሁም የተዘጋጁ ግጥሞችን፣ ሙዚቃ፣ የጥበብ ሥራዎች እንዲሁም ፊልሞችን ማስተዋወቅ ነው ትላለች።

“አንዳንድ ጊዜ ለምንድን ነው ይህንን ሁሉ የማደርገው ብዬ ልጠይቅ እችላለሁ። ነገር ግን ወዲያውኑ ለራሴ የሰዎችን ሕይወት ለመቀየር እየሞከርሽ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ ነው። መግፋት፣ መቀጠል ይኖርብሻል እላለሁ።”