በኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 8 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ሲፒጄ ገለጸ

ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ

የፎቶው ባለመብት, social media

የምስሉ መግለጫ, ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ቢያንስ ስምንት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጥብቃ ተሟጋቹ ኮሚቴ - ሲፒጄ አስታወቀ።

በአገሪቱ ፖለቲካዊ ውጥረት በሚከሰትበት ጊዜ ከሕግ ውጪ ጋዜጠኞችን ማሰር እንዲያቆሙ እና የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ ፈጽመውታል የተባሉ ጥቃቶችንም እንዲመረምሩ ሲፒጄ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ጠይቋል።

ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም. ድረስ ባሉ አስራ አንድ ቀናት ውስጥ የደኅንነት ሠራተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ደግሞ ሁለት ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን እና ሁለቱ ላይ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

“ቢያንስ ስምንት ጋዜጠኞች የታሰሩበት በኢትዮጵያ አዲስ የተጀመረው የጋዜጠኞች አስር፣ በአገሪቱ ባለው የፕሬስ ነጻነት ዙሪያ ጨፍጋጋ ምስል የሚፈጥር ነው” ያሉት የሲፒጄ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት ተወካይ ሙቲኪ ሙሞ፣ መንግሥት ጋዜጠኞቹን በመልቀቅ በእስር ላይ ሳሉ ተፈጸሙ ስለተባሉ ጥቃቶችም ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት የአማራ ሚዲያ ማዕከል ዋና አዘጋጅ አባይ ዘውዱ፣ የአራት ኪሎ ሚዲያ አዘጋጅ ዳዊት በጋሻው፣ የኢትዮ ሰላም አዘጋጅ ቴዎድሮስ አስፋው፣ የየኛ ሚዲያ ሪፖርተር ገነት አስማማው፣ የነገረ ወልቃይት ሚዲያ አዘጋጅ አሰፋ አዳነ እና የኢትዮ ንቃት መሥራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ ናቸው ብሏል።

ሁሉም በቁጥጥር ስር የዋሉት ጋዜጠኞች በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዘገባዎችን እና ትንተናዎችን የሚያቀርቡ መሆናቸውን የጠቀሰው የሲፒጄ መግለጫ፣ ግጭትን ማነሳሳትን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸዋል ብሏል።

በተለይ አባይ፣ ገነት፣ አሰፋ እና መስከረም በዋናነት የአማራ ብሔርን በሚመለከቱ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባ እና ትንተናን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የታሰሩትም “የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን በመንግሥት የወጣውን ዕቅድ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ነው” ብሏል - ሲፒጄ።

በእስር ላይ ካሉት ጋዜጠኞች በተጨማሪ የሐበሻ ወግ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነችው የዓይኔአበባ ግዛው በግል ጉዳይዋ ላይ ሳለች አዲስ አበባ ውስጥ የደኅንነት ሠራተኞች ነን ባሉ ሰዎች ታፍና ተወስዳ ምርመራ እና ድብደባ ተፈጽሞባት በሦስተኛ ቀኗ መለቋቋን ለሲፒጄ ተናግራለች።

በተጨማሪም የኢኤምኤስ ዘጋቢ የሆነው ሳሙኤል አሰፋ በለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ ያለውን ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ለመዘገብ ባቀናበት ጊዜ በፖሊስ ተይዞ “ግጭት በመቅስቀስ እና ከባለሥልጣናት ፈቃድ ሳያገኝ ዘገባ ለመሥራት በመሞከር” ተከሶ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት በላይ በእስር ላይ ቆይቶ በ10 ሺህ ብር ዋስ መፈታቱን ሲፒጄ አመልክቷል።

ሲፒጄ በመግለጫው ላይ እንዳመለከተው አብዛኞቹ በእስር ላይ ያሉት እና የተለቀቁት ጋዜጠኞች የቀረቡባቸው ክሶች በሚሰሩባቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የግጭት ቅስቀሳ በማድረግ ነው።

እንዲሁም ጋዜጠኞቹ በተያዙበት እና በእስር ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ስድብ፣ ማንገላታት እና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ተቋም ካሰባሰባቸው መረጃዎች መገንዘቡን ገልጿል።

ሲፒጄ በጋዜጠኞቹ እስር ዙሪያ የፌደራል ፖሊስን፣ የአዲስ አበባ መስተዳደርን፣ የፍትሕ ሚኒስቴርን፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትን፣ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ኮሚዩኒኬሽንን በተለያዩ መንገዶች ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።