ከጋጣ ያመለጠ ፈረስ በፈጠረው ግርግር ምክንያት የጭነት አውሮፕላኑ በረራውን አቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቦይንግ 747 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ፈረስ አሳፍሮ እየበረረ ሳለ እንስሳው ከጋጣው አምልጦ ግርግር በመፍጠሩ ሊያርፍ ተገዷል።
አውሮፕላኑ 30 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ እያለ ነው ፈረሱ ጋጣውን ጥሶ ግርግር የፈጠረው።
አውሮፕላኑ ከኒው ዮርክ ወደ ቤልጂየም እያቀና 90 ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ ነው ፈረሱ አልምጦ ለያዥ ያስቸገረው።
ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር የተገኘ ድምፅ ፓይለቱ “በሕይወት ያለ አንድ እንስሳ ይዘናል፤ ፈረስ ነው። ፈረሱ ከጋጣው አምልጧል” ሲል አሰምቷል።
ፓይለቱ አክሎ “ፈረሱን መልሰን ወደ ጋጣው ማስገባት አልቻልንም” ይላል።
የኤር አትላንታ አይስላንዲክ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥር 4592 አውሮፕላን ፓይለት በወቅቱ በረራው ላይ አደጋ ባይደርስም ፈረሱ ግን ስጋት እንደጫረበት ይገልጣል።
አብራሪው አክሎ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያርፉ የእንስሳት ሐኪም እንዲጠብቃቸው ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
አውሮፕላኑ ድጋሚ በረራውን ማድረግ ሲጀምር ማሳቹሴትስ አካባቢ 20 ቶን አሊያም 20 ሺህ ኪሎ ግራም ነዳጅ ለማስወገድ ተገዷል።
አውሮፕላኑ ያን ያህል መጠን ያለው ነዳጅ ለማስወገድ የተገደደው ክብደቱ በረራው ላይ ጫና እንዳያሳድርበት ነው።
ፈረሱ እንዴት አድርጎ ከጋጣው ሊያመልጥ እንደቻለ ግልጥ ባይሆንም አውሮፕላኑ ለማረፍ በተገደደ ወቅት ያለማሠሪያ ታይቷል።
በረራዎችን በመከታተል የሚታወቀው ፍላይትራዳር24 አውሮፕላኑ ድጋሚ በረራ አድርጎ ሊዥ አየር መንገድ በሰላም ማረፉን አሳውቋል።
ኤር አትላንቲክ አይስላንዲክ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ፈረሱ ወደ ሌላ ሃገር ለምን ሊዘዋወር እንደሆነም እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።
ነገር ግን ባለሙያዎች ፈረሱ ምናልባት ተወዳዳሪ ይሆናል የሚል መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ሲኤንኤን አንድ የወሬ ምንጬ ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው እንስሳት በጭነት አውሮፕላን ሲሄዱ “የመጀመሪያ ደረጃ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚ የተባሉ የተለያየ መጠን ያላቸው በረቶች ይገጠምላቸዋል።”
አንድ እንስሳ በአውሮፕላን እየሄደ ሳለ ከጋጣው አምልጦ ግርግር ሲፈጥር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ነሐሴ አንድ ድብ ከዱባይ ወደ ባግዳድ እየሄደ ካለ የኢራቅ ኤርዌይስ አውሮፕላን በረት ማምለጡን አሶሲየትድ ፕሬስ መዘገቡ ይታወሳል።












