ጆ ባይደን በዩናይትድ ኪንግደም ከጠቅላይ ሚንስትር ሱናክ እና ንጉስ ቻርልስ ጋር ሊገናኙ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዩኬ ተጉዘዋል። በዚህ ሳምንት አጋማሽ ደግሞ የኔቶን ስብሰባ በሉቲኒያ ይሳተፋሉ። ለዩክሬን እሰጠዋለሁ ያሉት ክላስተር ቦምብ የብዙዎች የስጋት ምንጭ ሆኗል። ይህን ጉዳይም ከሚያገኟቸው ባለሥልጣናት ጋር ይነጋገሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ክላስተር ቦምብ በንጹሃን ላይ ከሚደቅነው አደጋ አንጻር ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ስጋታቸውን ከገለጹት አገራት መካከል ናቸው።
አሜሪካ ደግሞ የዩክሬን የመሣሪያ መጋዘን እያለቀ በመሆኑ ክላስተር ቦምቡ አስፈላጊ ነው ብላለች።
ዛሬ ባይደን ከእንግሊዙን ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ጋር ይገናኛሉ።
ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች የሚወያዩ ሲሆን የዩክሬን ጉዳይም ከመወያያ ርዕሳቸው መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል።
ጆ ባይደን የክላስተር ቦምብ ልገሳውን አርብ ዕለት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የእንግሊዙ አቻቸው ጉዳዩን በቀጥታ አልነቀፉም።
ነገር ግን ትናንት ባደረጉት ንግግር የክላስተር ተተኳሾች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ፊርማቸውን ካስቀመጡ 123 አገራት መካከል አገራቸው አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
በእርግጥ ሌሎች የአሜሪካ አጋሮች ከዚህም በላይ ሄደዋል። የኔቶ አካል የሆነችው ኒው ዚላንድ “የክላስተር ቦምቡ በንጹሃን ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ያደርሳል” ብላለች።
ክላስተር ቦምብ ብዙ ትንንሽ ቦምቦችን የሚጥልና ብዙ ሕይወት የሚቀጥፍ ነው። ያልፈነዳ የክላስተር ቦምብ አካል ደግሞ ለዓመታት መሬት ላይ ሊቆይ ይችላል።
የዩክሬን ወታደሮች ክላስተር ቦምቡን ሩሲያ ውስጥ ወይም በከተማ ውጊያ እንደማይጠቀሙት የጽሁፍ ማረገጋጫ እንደሰጧት አሜሪካ ገልጻለች።
ጆ ባይደን በዩኬ ቆይታቸው ንግሥናቸውን ከጫኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ንጉስ ቻርለስን ያገኟቸዋል። በመቀጠልም ማክሰኞ እና ረቡዕ በሚካሄደው የኔቶ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን ይሳተፋሉ።
በዩክሬን የመሣሪያ አቅርቦትን መጨመር እና የመከላከል እቅድን መገምገም የውይይቱ አጀንዳ ይሆናል።
በኔቶ ስብሰባ ባለፈው ሚያዚያ የተቀላቀለችው ፊንላንድ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ታደርጋለች። የስዊድን አባል የመሆን እቅድ በቱርክ ተገትቷል። ዩክሬንም የአባልነት ጥያቄዋን መጠየቋን ትቀጥላለች። ነገር ግን ጦርነቱ ሳይቋጭ የሚታስብ ነገር እንዳልሆነ ፕሬዝዳንት ባይደን ለሲኤንኤን ልጸዋል።
“በስምምነታችን መሰረት የአባል አገራትን እያንዳንዷን ኢንች መሬት መጠበቅ ኃላፊነት አለብን። ዩክሬን ጦርነቱን ሳትቋጭ የኔቶ አባል ሆነች ማለት ሁላችንም የዩክሬንን መሬት ለመጠበቅ ጦርነት ውስጥ ገባን ማለት ነው” ብለዋል ጆ ባይደን።
ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ኔቶን የመቀላቀል ተስፋ በመሰነቅ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ይህንን አቋም ባለፈው ደግፈውታል። የዚ ህሳምንቱን ስብሰባም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካ የዩክሬንን የክላስተር ቦምብ ጥያቄ ይሁን ያለችው ባለፈው አርብ ነው። የአሜሪካ ባለስልጣናት እንዳሉት ይህ እገዛ ቃል ከተገባው የ800 ሚሊዮን ዶላር የወታደራዊ እገዛ አካል ነው።
ዩክሬን ተተኳሽ በመጨረሷ ያደረጉት “ከባድ ውሳኔ” መሆኑን ፕሬዝዳንት ባይደን ገልጸዋል። ቢሆንም ግን በርካታ የአሜሪካ አጋሮች በፍጥነት ውሳኔውን ተቃውመውታል።
እንደ ኒው ዚላንድ ሁሉ ካናዳ እና ስፔን ምተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የኔቶ አባል የሆነችው ጀርመን ደግሞ ራሷ እንደዚህ አይነት መሣሪያዎችን ማቅረብ ባትፈልግም የአሜሪካን አቋም እንደምትረዳ ገልጻለች።
አንደኛው ስጋት ክላስተር ቦምቡ ሳይፈነዳ የመቆየት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ለዓመታት አደጋን የደቀነ መሆኑ ነው። አሜሪካ እንደምትለው ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ከምትጠቀመው ክላስተር ቦምብ አንጻር ይህኛው ውጤታማ ነው ብላለች።
ዩክሬን ክላስተር ቦምቡን ንጹሃን በሚገኙበት ላለመተኮስ እና አጠቃቀሙን በተመለከተም ሪፖርት እንደምታቀርብ ቃል ገብታለች። በሌላ በኩል ሩሲያ የዩክሬንን እቅድ “ረብ የለሽ ነው” ብላዋለች።












