ምዕራባውያን አገራት አሜሪካ ክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ለመላክ መወሰኗ አሳሰቢ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካታ የአሜሪካ አጋር የሆኑ ምዕራባውያን አገራት ዋሽንግተን ለዩክሬን ክላስተር ቦምቦችን ለመላክ መወሰኗ አሳሰቢ ነው አሉ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሁለት ቀናት በፊት አወዛጋቢውን ጦር መሳሪያ ለዩክሬን ለመላክ “ከባድ የሆነ ውሳኔ” ማሳተላለፋቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካን ውሳኔን አሳስቦናል ካሉ የዋሽንግተን አጋር አገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ኒው ዚላንድ እና ስፔን ይገኙበታል።
ክላስተር ቦምቦች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ከ100 በላይ በሆኑ አገራት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እና እንዳይመረቱ ታግደዋል።
በክላስተር ቦምብ ውስጥ በርካታ ቦምቦች የታጨቁበት ሲሆን በሚፈንዳበት ጊዜ ወደ ብዙ ፍንጣሪ ቦምቦች በመለወጥ በፍንዳታው አካባቢ የሚያገኘውን ሰው በጅምላ ይሚገድል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቦምቦች ተወርውረው ሳይፈነዱ የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች ከፍተኛ በሆኑ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት መሬት ውስጥ ከቆዩ በኋላ ድንገት ስለሚፈነዱ አነጋጋሪ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ባይደን አርብ ዕለት ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ የ800 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አካል የሆኑትን የክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ስለመላክ ከአጋር አገራት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ባይደን ለዩክሬን ክላስተር ቦምቦችን ለመስጠት ብዙ ማሰባቸውን ገልጸው በመጨረሻ ቦምቦቹን ለመላክ የወሰኑት ዩክሬናውያኑ የጦር መሳሪያ እጥረት ስላጋጠማቸው ነው ብለዋል።
የአሜሪካ የክላስተር ቦምቦችን ወደ ዩክሬን የመላክ ውሳኔ በተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ነቀፌታ ደርሶበታል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እንኳ ክለስተር ቦምቦች ለሰላማዊ ሰዎች ከፍተኛ ስጋት ናቸው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮም የአሜሪካን ውሳኔ ተቃውሟል። “እነዚህ መሳሪያዎች በአስቸኳይ በየትኛውም ቦታ ጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም” ብሏል።
የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ክሪስ ሂፕኪንስ ክላስተር ቦምቦች ዒላማ ሳይለዩ “ምንም ባላጠፉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ነው የሚያስከትሉት” ካሉ በኋላ ቦምቦቹ በዩክሬን ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የኒው ዚላንድ አቋም ምን እንደሆነ ለዋይት ሃውስ ቀድመን አሳውቀናል ብለዋል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው አገራቸው የክላስተር ቦምቦችን ምርት እና ጥቅም ከተከለከሉባቸው 123 አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታውሰው ቦምቦቹ በዩክሬን ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደማይደግፉ ገልጸዋል።
የስፔን መከላከያ ሚንስትር ማርጋሪታ ሮቤልስ ደግሞ አገራት ወደ ዩክሬን መላክ የሌለባቸው የጦር መሳሪያ ዝርዝር ውስጥ ክለስተር ቦምቦች እንደሚገኙ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
የካናዳ መንግሥት ደግሞ ከፍተኛው ስጋቴ ሳይፈነዱ የቆዩ ክላስተር ቦምቦች በልጆች ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ነው ብሏል።
የካናዳ መንግሥት የክላስተር ቦምብ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም የሚለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ጽኑ የሆነ አቋም እንዳለው ገልጿል።
ጀርመን በበኩሏ የክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ባላቀርብም አሜሪካ ቦምቦቹን ለመስጠጥ እንዴት ከውሳኔ ልትደርስ እንደቻለች እረዳለሁ ብላለች።
አሜሪካ፣ ዩክሬን እና ሩስያ ይህን የክለስተር ቦምብ ማምረት እና ጥቅም ላይ ማዋል የሚከለክለው ስምምነትን አልፈረሙም።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር አገሪቱ ከአሜሪካ የምትቀበላቸው ክለስተር ቦምቦች የጠላት ምሽጎችን ለማፍረስ ብቻ እንጂ በከተማዎች ጥቅም ላይ እንደማይውሉ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ሩስያ የአሜሪካን ውሳኔ አጥብቃ ተቃውሟላች። አሜሪካ ክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ለመስጠት መወሰኗን የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “ብዙ የተወራለት የዩክሬን መልሶ ማጥቃ ውድቀንት ተከትሎ የመጣ የተስፋ መቁረጥ ደርጊት ነው” ብሎታል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን አሜሪካ ሰራሾቹ ክለስተር ቦምቦች ተወርውረው ሳይፈነዱ የሚቀሩበት አጋጣሚ 2.5 በመቶ ብቻ ነው ካሉ በኋላ በአንጻሩ ሩስያ ሰራሾቹ ከ30-45 በመቶ ነው ብለዋል።












