የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ ኔዘርላንድስ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ስዊዲናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ገሬታ ተንበርግ፤ ኔዘርላንድስ ዘ ሄግ ተቃውሞ እያደረገች ሳለ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለች።
የ21 ዓመቷ ተሟጋች ቅዳሜ ዕለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን ተቀላቅላ ተቃውሞ ስታሰማ ነበር።
ሰለፈኞቹ ዋናውን መንገድ ለመዝጋት መሞከራቸውን ተከትሎ ነው እግረኛ እና ፈረሰኛ ፖሊሶች ሰልፉን ለመበተን የተነሱት።
የአካባቢው ፖሊስ ግሬታ ተንበርግን ከሌሎች ሰልፈኞች ጋር አንድ ባስ ውስጥ በማስገባት ከሥፈራው ይዘዋት ሄደዋል።
ግሬታ እና አጋሮቿ ዘ ሄግ የሚገኘውን ዋና መንገደ በመዝጋት ነበር ድምፃቸውን ማሰማት የሻቱት።
የኔዘርላንድስ መንግሥት ሼል እና ኬኤልኤም አየር መንገድን ጨምሮ ለሌሎች በማይታደስ ኃይል ለሚሠሩ ኩባንያዎች የግብር እፎይታ ለማድረግ ማቀዱን ተከትሎ ነው የተቃውሞ ሰልፍ የተጠራው።
የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች መንግሥት በሚመጣው ሰኔ ሊያደርግ ያሰበውን የግብር እፎይታ በጫና ለማስቀየር አስበዋል።
“ታዳሽ ያልሆነ ኃይል ግብር ይጣልበት” የሚል መልዕክት ያዘሉት ግሬታ ተንበርግና ሌሎች ሰልፈኞች ቅዳሜ ዕለት ዘ ሄግ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ከዚህ ቀደም ሌሎች ሰልፈኞች ይህን መንገድ ዘግተው ድምፃቸውን ቢያሰሙም የቅዳሜው ሰልፍ ብዙ ትኩረት ያገኘው ታዋቂዋ ‘አክቲቪስት’ በመሳተፏ ነው።
በማርሽ ባንድ የታጀቡት ሰልፈኞች ባሕላዊ የደች ሙዚቃ የአየር ንብረት ለውጥን በሚያቀነቅን ግጥም አድርገው ሲያዜሙ ተደምጠዋል።
የከተዋማ ነዋሪዎች ሰልፈኞቹ በጣም ሞቃታማ በሆነ ቀን ወደ ባሕር ዳርቻ እንዳንሄድ ከልክለውናል ሲሉ ብስጭታቸውን መግለጣቸውን አንዳንድ ጋዜጦች አስነብበዋል።
ሰልፈኞቹ ከከተማዋ መሐል ተነስተው ወደ አውራ ጎዳናው ሲያቀኑ አድማ በታኝ ፖሊስ ጠብቋቸዋል።
አንዳንድ ሰልፈኞች የፖሊስን አጥር ጥሰው ለማለፍ ቢሞክሩም የካቴና ሲሳይ ከመሆን አላመለጡም።
“ዛሬ ተቃውሞ ማድረጋችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እየኖርን ያለን ፕላኔታችን የአደጋ ጊዜ ላይ ባለችበት ወቅት ነው” ስትል ግሬታ ተንበርግ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግራለች።
“ይህን ቀውስ ለማስወገድ እና የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን።”
ግሬታ በእሥራቱ ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰባት ተናግራለች።
ተማጋቿ ከፖሊስ ባስ ከተለቀቀች በኋላ መልሳ የተቃውሞ ሰልፉን በመቀላቀል ለሁለተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሏ የሚጠቁሙ ዘገባዎች ነበሩ።
ፖሊስ አንዳንድ ሰልፈኞች ከተለቀቁ በኋላ መልሰው ሰልፉን በመቀላቀላቸው ድጋሚ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለቢቢሲ ቢናገርም የግሬታን ስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
ግሬታ ተንበርግ ከ15 ዓመቷ ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ድምጿን በማሰማት ትታወቃለች።












