በየቀኑ የእግር ጉዞ ማድረግ ያለዕድሜ ከሚከሰቱ 10 ሞቶች አንዱን ያስቀራል - ጥናት

ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ የጤና ጥቅም ለማግኘት ሯጭ ወይም ስፖርተኛ መሆን አይጠበቅብዎትም ይላል አንድ በዩናትደ ኪንግደም (ዩኬ) የተሰራ ጥናት።

ጥናቱ እንደሚለው ለጤናማ ሕይወት በቀን ውስጥ ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ በቂ ነው።

እያንዳንዱ ሰው በቀን ውስጥ ለ11 ደቂቃዎች እንቅስቃሴ ቢያደርግ ያለ ዕድሜ ከሚከሰቱ አስር ሞቶች ውስጥ አንዱን ማስቀረት እንደሚቻል ጥናቱ ጠቁሟል።

ይሁን እንጂ አብዛኛው ሰው በሳምንት ውስጥ ማድረግ የሚጠበቅበትን ዝቅተኛው የ150 ደቂቃ እንቅስቃሴ አያደርግም።

የአካል በቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው የሚሉት የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፤ ምንም እንቅስቃሴ ካለማድረግ ግን የተወሰነ እንቅስቃሴ ማድረግ የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ።

የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎትም (ኤንኤችኤስ) ማንኛውም ሰው በሳምንት የልብ ምትን የሚጨምር ከ150 እስከ 300 ደቂቃ የሚወስድ የአካል እንቅስቃሴ አሊያም ከ75 እስከ 150 ደቂቃ የሚወስድ ብዙ ትንፋሽ የሚያስወጡ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ ይመክራል።

የጥናት ቡድኑ በአካል እንቅስቃሴ ጥቅሞች ላይ ቀደም ብለው የተሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናቶችን የተመለከተ ሲሆን፣ ከሚመከረው መጠን ግማሽ ያህሉን እንኳ እንቅስቃሴ ማድረግ በልብ በሽታ ከሚያዙ 20 ሰዎች የአንዱን፣እንዲሁም በካንሰር ከሚያዙ 30 ሰዎች መካከል የአንዱን ማስቀረት እንደሚያስችል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ለዚህም የሚያስፈልገው በሳምንት 75 ደቂቃ ወይም በቀን ለ11 ደቂቃ እንደ ሳይክል መጋለብ፣ ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ተራራ መውጣት፣ መደነስ፣ ቴኒስ መጫወት እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ነው።

ጥናቱን የመሩት ዶ/ር ሶረን ብራጅ “እንቅስቃሴ ስትሰሩ እየተንቀሳቀሳችሁ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይገባል። ልባችሁ በፍጥነት ይመታል። ግን የመተንፈስ ችግር አይገጥማችሁም” ብለዋል።

ጥናቱ ያስቀመጠውን መጠን ያህል የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ለልብ በሽታ እና ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድልን በ17 በመቶ፣ እንዲሁም ለካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ደግሞ በ7 በመቶ እንደሚቀንስ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሰውነት ስብን እና የደም ግፊትን ለመቀነስ እና የአካል ብቃትን፣ እንቅልፍን እና የልብ ጤናን በረጅም ጊዜ ያሻሽላል ብሏል።

የአካል እንቅስቃሴ እንደ የጭንቅላት፣ የአንገት፣ የጨጓራ፣ የአጥንት እና የደም ካንሰር ዓይነቶችን ለመከላከል ከፍተኛ ጥቅም ያለው ሲሆን ለሳንባ፣ ለጉበት፣ ለጡት፣ ለማህጸን እና ለአንጀት ካንሰር ጠቀሜታው እምብዛም እንደሆነም ጥናቱ ጠቁሟል።

በእንግሊዝ የስፖርት ሕክምና ጆርናል ላይ የታተመው ይህ ጥናት፣ መረጃዎችን ለማሰባሰብ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ የተሰሩ ቀደም ብለው የታተሙ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ሰፊ ጥናቶችን እና ወደ 200 የሚጠጉ አጫጭር ጥናታዊ ጽሑፎችን ተመልክቷል።

በጥናቱ የተካተቱ ሁሉም ሰዎች በሳምንት ለ10 ደቂቃዎች እንቅስቃሴ እንዲሰሩ ቢደረግ፣ ከስድስቱ ሰዎች ውስጥ አንዳቸውን ያለዕድሜ ከሚከሰት ሞት መከላከል እንደሚቻል ተሰልቷል።

አጥኚዎቹ የተወሰኑ ልማዶችን መለወጥ እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

ለአብነትም ወደ ሥራ አሊያም ወደ ሱቅ ለመሄድ መኪና ከማሽከርከር ይልቅ ሳይክል መጋለብ፣ አሊያም የእግር ጉዞ ማድረግ እንዲሁም ከልጆች ጋር በሚያሳልፉበት ጊዜ በንቃት መንቀሳቀስ፣ በእረፍት ቀናትም በእንቅስቃሴ የተሞላ ጊዜን ማሳለፍ ጠቃሚ ነው ብሏል።

ብሔራዊው የጤና አገልግሎት በበኩሉ አዋቂዎች እንደ ዮጋ፣ ክብደት ማንሳት፣ የመሳሰብ እና የመተጣጠፍ እንቅስቃሴዎች፣ የሸመቱትን እቃ የሞሉበትን ከባድ የገበያ ዘንቢሎችን መሸከምን ጨምሮ ጡንቻዎቻቸውን የሚያጠነክሩ እንቅስቃሴዎችን በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲያደርጉም መክሯል።