የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኬንያ ገቡ

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ናይሮቢ ሲደርሱ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙትዋ ሲቀበሏቸው

የፎቶው ባለመብት, @DrAlfredMutua

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ናይሮቢ ሲደርሱ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙትዋ ሲቀበሏቸው

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ረቡዕ እኩለ ቀን የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ገቡ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ናይሮቢ ያቀኑት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን ግብዣ ተከትሎ መሆኑን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል ገልጸዋል።

ረቡዕ እና ሐሙስ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናይሮቢ ሲደርሱ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙቱዋ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳሌህ እና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገ/አብ አብረዋቸው ወደ ኬንያ ተጉዘዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ኬንያ ያቀኑት ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መሆኑ ከመገለጹ ውጪ በቆይታቸው ከኬንያ መሪዎች ጋር በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ከኤርትራ በኩል የተባለ ነገር የለም።

የኬንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙቱዋ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ተገናኝተው በአገሮቻቸው ግንኙነት ላይ ይመክራሉ።

ኢሳያስ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ናይሮቢ ለጉብኝት ሲያቀኑ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ፕሬዝዳንቱ እአአ 2018 ላይ ወደ ኬንያ መምጣታቸው ይታወሳል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ወደ አሥመራ በመጓዝ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር።

በዚህም ሩቶ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ ወደ በኤርትራ ተጉዘው የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አድርገው ነበር።

ሩቶ በአሥመራ የሥራ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በንግድ እና በቀጠናዊ ትብብር ላይ ከስምምነት ድርሰው ነበር።

የዊሊያም ሩቶ ጉብኝትን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ይፋ እንዳደረጉት የኤርትራ እና የኬንያ ዜጎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ አገሮቹ መጓዝ እንዲችሉ ተስማምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል።

በቀጠናው በየብስ፣ በባሕር እና በአየር ትራንስፖርት ንግድ እና ኢንቨስትመንት ማጎልበት አስፈላጊነት ላይ ሁለቱ መሪዎች ከመግባባት መድረሳቸውን በሩቶ ጉብኝት ማጠናቀቂያ ላይ ተገልጾ ነበር።

ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ የግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤት ስትሆን፣ በአፍሪካም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል አንዷ ናት።

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ነጻ የወጣችው ኤርትራ በምጣኔ ሀብት ትስስር ይጎላ ገጽታ ያላዳበረች ሲሆን፣ በመብት ጥሰቶች እና በዜጎች ጭቆና በመብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ስትወቀስ የቆየች ናት።