ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ምን ብለው ነው የአረብ አገራትን ያስቆጡት?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሠራዊታቸው በጋዛ ውስጥ በሚያካሂደው ጦርነት ምክንያት በተፈጠረው የሰላማዊ ሰዎች ሞት እና የረሃብ አደጋ ከፍተኛ ትችት እና ተቃውሞን ከወዳጆቻቸው ሳይቀር እየደረሰባቸው የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሌላ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸዋል።
ባለፈው ማክሰኞ አይ24 ከተባለው የአገራቸው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት አስተያየት በበርካታ የአረብ አገራት ዘንድ ቁጣን ከመቀስቀሱ በተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ እየተጠየቁ ነው።
የመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት ኔታኒያሁ "የታላቋ እስራኤል" ካሉት ራዕይ ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት በማንሳት ይህንንም ተልዕኮ ለማሳካት እንሚጥሩ መናገራቸው ለሉዓላዊነታቸው ስጋት የሚደቅን መሆኑን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በቃለ ምልልሳቸው ላይ የታላቋ እስራኤል ራዕይ "ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ተልዕኮ" አድርገው እንደሚቆጥሩት እና "ወደዚህ ለመምጣት የሚያልሙ የነበሩ እና ከእኛም በኋላ የሚመጡ ያሏቸው" የአይሁድ ትውልዶች ራዕይም መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ታላቋ እስራኤል የሚለው ስያሜ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ የአገሪቱን ግዛት ከማስፋፋት ጋር የሚያያዝ ተደርጎ ይታያል።
ይህም ዌስት ባንክን፣ ጋዛን እና የሶሪያን ጎላን ተራሮችን የሚጨምር ሲሆን በአንዳንድ በኩልም የግብፅን ሲናይ ባሕረ ገብ አካባቢን እዲሁም የተወሰኑ የዮርዳኖስ ግዛቶችን የሚያካትት መሆኑ ይነገራል።
ሁለት ዓመት ሊሞላ ትቂት ወራት በቀሩት እና እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ኔታኒያሁ ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ዕቅድ አውጥተው ለተግባራዊነቱ እየሠሩ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ባለፉት ወራት በዌስት ባንክ የአይሁድ ሰፈራዎች እየተስፋፉ መሆናቸው እየተነገረ ሲሆን፣ የሶሪያ የጎላን ተራሮች በእስራኤል ቁጥጥር ስር ከገቡ አስርታት ተቆጥረዋል።
እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የታላቋ እስራኤል ራዕይን ቀስ በቀስ እያስፈጸሙ ነው የሚል ስጋትን ከመፈጥሩ ባሻገር አረብ አገራት ተቃውሞ እያቀረቡ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "በቀጠናው አለመረጋጋትን የሚያባብስ እና ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርግ ነው" በማለት ማብራሪያ ጠይቃለች።
የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የኔታኒያሁን ንግግር "አደገኛ ጠብ የመጫር እና ማባባስ" በማለት "ለአገራት ሉዓላዊ ስጋት፣ የዓለም አቀፍ ሕግን እና የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር የሚጥስ" በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል።
የፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰነዘረውን አስተያየት "የፍልስጤማውያንን ሕጋዊ መብቶችን ችላ የሚል" እና "የቀጠናውን ደኅንነት እና መረጋጋት የሚያናጋ ጠብ አጫሪነት" በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁን ንግግር "ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንቦችን ጥሰት እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚፈታተን" ያለው ደግሞ የየመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኔታንያሁን አስተያየት "[የእስራኤል] በእብሪተኝነት ላይ የተመሠረተ የወረራ ስልት ማራዘሚያ፣ ግጭትን እና ቀውስን የሚያባብስ እንዲሁም በማን አለብኝነት የአገራትን ሉዓላዊነት አንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ" ሲሉ ነቅፈውታል።
ሚኒስቴሩ ኳታር "በቀጠናው ፍትሃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የታለሙ ጥረቶችን በሙሉ" ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።
የሳዑዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእስራኤል ባለሥልጣናት የሚራመዱትን "የመስፋፋት ሃሳቦች እና ፕሮጀክቶችን" ውድቅ በማድረግ "ወንድም የሆነው የፍልስጤም ሕዝብ በምድራቸው ላይ ነፃ እና ሉዓላዊ አገራቸውን የመመሥረት ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቱን" እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
የአረብ ሊግ ባወጣው መግለጫ የእስራኤልን "አውዳሚ እና የመስፋፋት ዝንባሌዎች" በማውገዝ "ለጋራ የአረብ ብሔራዊ ደኅንነት ከባድ አደጋ" ሲል አውግዟል።
የእስልምና ትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) ባወጣው መግለጫ ደግሞ "የእስራኤልን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች እንደ ወራሪ ኃይል ለማምለጥ እና የፍልስጤም ሕዝብ ሕጋዊ መብቶችን እየጣሰች ለመቀጠል የሚደረግ ሙከራ ነው።
"ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና በ1967 ድንበሮች መሠረት ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማቸው አድርገው ገለልተኛ አገር የመመሥረት መብታቸው ነው" ብሏል።
"ይህ የቅኝ ግዛት፣ የተስፋፊነት ንግግሮች ለአካባቢያዊ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ስጋት የሚፈጥሩ፣ የግጭት አዙሪት እንዲባባስ እና በአካባቢው ያለውን ግጭት የሚያራዝም እና የሚያሰፋ" ንግግር ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ የኔታንያሁን አስተያየት "ይህ ፋሽስታዊ አካል በሁሉም የአካባቢው አገራት እና ሕዝቦች ላይ የሚፈጥረውን አደጋ እና የትኛውንም መንግሥትን የማያስተርፈውን የማስፋፊያ ዕቅዶቹን በግልፅ ያሳያል" ብሏል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ በርካቶችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ ወዲህ እስራኤል ባካሄደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ እንደ ሐማስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እስካሁን ድረስ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ61 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ባለፈው ኅዳር ወር ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በጋዛ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል የእስር ማዘዣ አውጥቷል።















