ዩናይትድ ኪንግደም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን በሽብር ድርጅትነት ልትፈርጅ መሆኑ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ዩናይትድ ኪንግደም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ሽብርተኛ ድርጅት ነው በማለት በይፋ ለመሰየም እየተዘጋጀች መሆኑ ተገለጸ።
የኢራን ዋነኛው የወታደራዊ ኃይል የሆነውን አብዮታዊ ዘብ ጓድን ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በሕግ በሽብርተኛ ቡድንነት የምትፈርጀው ከሆነ፣ በግዛቷ ውስጥ ሆኖ የቡድኑ አባል መሆንም ሆነ እንቅስቃሴዎቹን መደገፍ የወንጀል ድርጊት ይሆናል።
የዩኬ መንግሥት ምንጮች እንዳሉት ቡድኑን በሽብርተኝነት ለመሰየም የሚያስፈልጉ ዝርዝር ጉዳዮች እየተዘጋጁ በመሆናቸው በቅርቡ ይፋ ላይሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድን ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ለመሰየም እየተዘጋጀ መሆኑ እውነት መሆኑን ምንጮቹ አረጋግጠዋል።
ዩኬ የኢራንን ወታደራዊ ኃይልን ሽብርተኛ የምትለው ከሆነ፣ ተመሳሳይ ውሳኔን ከአራት ዓመት በፊት ካሳለፈችው ከአጋሯ አሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ አገር ትሆናለች።
ይህም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ኢራን በበርካታ ዜጎቿ እና በግዛቷ ባሉ ሰዎች ላይ ስታሴር እንደነበር በመግለጽ ቀጥተኛ ስጋት ሆናለች በማለት የደኅንት ተቋሞቿ ሪፖርት ማድረጋቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ያሻክረዋል።
ኅዳር ወር ላይ የኢራን ገዳይ ቡድን አንድ ትውልደ ኢራናዊ የብሪታኒያ ዜጋ ጋዜጠኛን ዒላማ ለማድረግ ለንደን ውስጥ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ባለፉት ወራት ኢራን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰባት ሰዎች በአብዮታዊ ዘቡ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
አንድን ድርጅት ሽብርተኛ ነው ብሎ መሰየም በዩናይትድ ኪንግደም የሽብር ሕግ መሠረት መደበኛ የሕግ ሂደት ነው።
በዚህ ሂደትም መንግሥት የቡድኑን የሽብር ተግባራትን መጠን ብቻ ሳይሆን በተለይ ለዩናይትድ ኪንግደም እና በውጪ አገራት ላሉ ዜጎቿ በተለይ የሚደቅነውን ስጋት ይመረምራል።
በተጨማሪም ሕጉ አንድ ግለሰብ የቡድኑ አባል በመሆን ብቻ ሳይሆን፣ የቡድኑን ዓላማ እንደሚደግፍ መግለጽ፣ ከአባላቱ ጋር መገናኘት ወይም ሰንደቅ ዓላማውንና አርማውን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ማሳየት ተጠያቂ ያደርጋል።
ይህ በዩናይትድ ኪንግደም የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጓድን ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ መሰየም፣ የተቋረጠውን የኢራንን የኒውክሊየር ፕሮግራምን ለማስቆም የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጓድ የአገሪቱን እስላማዊ አብዮት ለመጠበቅ ከአርባ ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ካሉ በጣም ኃያል ወታደራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።
ወታደራዊው ጓድ በአካባቢው ያሉ ወዳጅ መንግሥታትን እና ታጣቂ ቡድኖችን ለመደገፍ የሚያስችለው ግዙፍ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የምጣኔ ሀብት አቅም አለው።
በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጄንስ ክሌቨርሊ በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ላይ ሙሉ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቀው ነበር።
በተጨማሪም የዩኬ ፓርላማ በቡድኑ ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት እየተደረገ ነው።
የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ወታደራዊ ቡድኑ በሽብር ቡድንነት እንዲፈረጅ ጥያቄ አቅርቧል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከጥቂት ወራት በፊት ለመሪነት ከሊዝ ትረስ ጋር እየተፎካከሩ በነበረበት ጊዜ “የኢራን አብዮታዊ ዘብን በሽብር ለመፈረጅ በቂ ምክንያት አለ” ብለው ነበር።
ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ከተረከቡ በኋላ ስለዚህ ጉዳይ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።
የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሽብር ቡድንነት ሊፈረጅ እንደሆነ በተጠየቁበት ጊዜ ግልጽ ያለ መልስ ከመስጠት መቆጠብን መርጠዋል።
“በሽብር የተፈረጁ ቡድኖችን ዝርዝር መንግሥት በየጊዜው የሚከልስ በመሆኑ፣ አንድን ድርጅት በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ነው ወይም አይደለም የሚል አስተያየት አንሰጥም” ብለዋል።












