ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለመስቀል የተለቀቀው ‘ዓለም ብሬ’ ዘፈን እና ድምጻዊቷ ሳሌሚያ
ሰሞኑን አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ በየሱቁ የሚሰማው ዘፈን ‘ዓለም ብሬ’ ነው።
ነጋዴዎች ሙዚቃውን ሞቅ አድርገው ይከፍቱታል።
ድምጻዊቷ ለመስቀል በዓል እንዲደርስላት አስባ ነው ዘፈኑን የለቀቀችው። ከበዓሎች ሁሉ በጣም የምትወደው ደግሞ መስቀልን ነው።
እንደተመኘችውም ከበዓሉ አራት ቀናት ቀድማ ‘ዓለም ብሬ’ን አውጥታለች።
ሳሌሚያ ትባላለች። የስሟ ትርጉም ሰላም ማለት ነው።
የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዋን ስትለቅ የተደረገላት አቀባበል ለዓመታት ከዘፈኑት የማይተናነስ ነው።
‘ዓለም ብሬ ነይ ነይ’ ታዋቂ የሕዝብ ዜማ ነው። በየበዓሉ፣ በየሰርጉ የሚያስጨፍር ጉራግኛ ዘፈን።
በተለይ አርጋው በዳሶ ሲዘፍነው ዝናው ናኝቷል።
ሳሌሚያ ደግሞ መግቢያውን እንግሊዘኛ አድርጋ ከዚያም በአማርኛ ዳግመኛ ሠርታዋለች።
ቀዩ ሻንጣ
የሙዚቃ ቪድዮው ከመርካቶ የንግድ ግርግር ይነሳና ጉራጌ ዞን፣ ቡኢ ከተማ ኮባ ሥር ባለ ጎጆ ፊት ሳሌሚያ ትታያለች።
ከዚያም ቀይ ሻንጣ እናያለን። ቀዩ ሻንጣ ተምሳሌታዊ ነው።
በታታሪ ሠራተኛነት የሚወደሰው የጉራጌ ሕዝብ ለመስቀል ሻንጣውን ሸክፎ ከየቦታው ወደቀዬው ይመለሳል።
ሳሌሚያ መስቀልን የምትወደው አንድም ድባቡ ደማቅ ስለሆነ እና ማኅበረሰቡን ስለሚያስተሳስርም ነው።
የመስቀል ሰሞን በአፍሪካ ትልቁ የአደባባይ ገበያ ጭር ብሎ ነጋዴው ትውልድ መንደሩ የሚገባበት ነው።
“ሰው እቃ ገዛዝቶ፣ ስጦታውን ይዞ አገር ቤት የሚገባበት ጊዜ ነው። ከቤተሰብ ጋር ለመተሳሰር የሚደረገው ጥረት የመስቀል በዓልን በጣም የምወድበት ዋነኛ ምክንያት ነው” ትላለች።
ቀዩ ሻንጣ የሙዚቃው መጀመሪያ ወንበር ላይ ከዚያም አንድ አያት ይዘውት፣ ሁለት ልጅ ከበዋቸው ይታያል።
በጉራጌ ማኅበረሰብ የመስቀል ዝግጅት የሚጀመረው ቀደም ብሎ ነው።
“. . . ቂቤ ማንጠርን ጨምሮ የምግብ ዝግጅት ሦስት ወር ቀድሞ ነው የሚጀምረው። ሦስት ወር ቀድሞ የተዘጋጀ ምግብ ጉልበት ይሆናል። መጨረሻ ላይ የተሠራ ግን ቃር ይሆናል የሚል አባባል አለ።”
ይህ የበዓል ዝግጅት ለድምጻዊቷ ትልቅ ዋጋ አለው። የሚፈጥረው ማኅበረሰባዊ ትስስርም ጭምር።
ሳሌሚያ እንደምትለው፣ ዘፈኑ ለአያት ቅድመ አያቷቾ መወድስ፣ መታሰቢያም ነው።
“ቅድመ አያቴ ‘ዓለም ብሬን’ ትዘፍንልን ነበር”
ልጅ ሳለች ቅድመ አያቷ ይሄን ዘፈን ይዘፍኑላት እንደነበር ታስታውሳለች።
ዘፈኑን ተከትሎ በደንብ የጨፈረ ሰው ደግሞ ከቅድመ አያቷ ብር ይሸለማል።
“በደንብ ጨፍሩ ይባላል. . . በቃ ‘work ethic’ እንደሚባለው” ትላለች በትውስታ።
ጭፈራው ላይ የበረታ ሰው አንድ ብር ይሰጠዋል።
“ያኔ በዘመኑ አንድ ብር ትልቅ ነበር” ትላለች ሳሌሚያ እየሳቀች።
“Go back and see my line አዬ ብሬ ብሬ. . . All my ancestors rise. . . አዬ ብሬ ብሬ. . . Cause they no never sleep አዬ ብሬ ብሬ. . . And they know how to build አዬ ብሬ ብሬ. . . Dream big when you are low then you just might fly. . .” ስትል ቀደምት አያቶቿን ታወድሳለች።
“ሙዚቃው ያደግኩበት ነው። ቅድመ አያታችን እየተጫወተችልን ነው ያደግነው። እሷ ያደገችበት መንደር ሄጄ ነው የቀረጽኩት” ትላለች።
ቅድመ አያቷ አዲስ አበባ ከሄዱ በኋላ አራት ተከታታይ ትውልድ እዚያው አዲስ አበባ እየኖረ ነው።
ቅድመ አያቷ የጉራጌን ባህል እያስተማሩ ነው ያሳደጓቸው።
ዘፈኑ ቅድመ አያቷን እያወደሰ ቡኢንም የሚያሳይ ነው።
“ከትምህርት ቤት ስንመለስ በየቀኑ ከሰዓት ይሄን ሙዚቃ ትጫወትልን ነበር። መሰባሰቢያችን ነበር” ትላለች።
ዘፈኑን ሲሰሙት ቤተሰቦቿ ደስታ በደስታ ሆነዋል።
በተለይ እናቷ የሚነግዱበት ሰፈር ያሉ ነጋዴዎች ያደምጡታል።
“ቤተሰቦቼ በተቻለው በጣም እየደገፉኝ ነው። እነሱ ለቤተሰብም፣ ለጓደኛም እየተላላኩ መሰለኝ ዩቲዩብ ላይ ዘፈኑን እያዩት ያሉት” ትላለች ድምጻዊቷ ሳቅ ሳይለያት።
ዘፈኑ በወጣ በአራት ቀናት ብቻ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ዩቲዮብ ላይ ተመልክተውታል።
“ዘፈኑ ‘አስለቅሶናል’ ያሉኝ አሉ”
ዩቲዩብ ላይ ከተሰጧት አስተያየቶች መካከል “ዘፈኑ ስሜታዊ አድርጎኛል፣ አስለቅሶኛል” የሚሉት በጣም አስደስተዋታል።
ዘፈኑ ብዙዎችን በትዝታ ወደኋላ መመለሱ፣ የጉራጌ ማኅበረሰብን ትውስታ መቀስቀሱ ደግሞ የበለጠ አስደስቷታል።
የዘፈኑን ቪድዮ ለመቅረጽ ወደ ቡኢ ሲያመሩ የታሪክ መስመር ነድፈው እንደነበር ሳሌሚያ ትናገራለች።
ቀዩ ሻንጣ ኮባ ሥር ሆኖ ያለውን እና የገበያ ትዕይንትን ለመቅረጽ አስበው ነው የሄዱት። ድንገት የተገኙም ትዕይንቶች አሉ።
“ቪድዮውን የሠራነው መንገድ ላይ ያገኘናቸውን ሰዎች አስገብተን ነው” ትላለች።
ማኅበረሰቡ ውስጥ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎችን “ባሉበት ነው በብዛት የተቀረጸው” ትላለች ሳሌሚያ።
“ሁሉም በራቸውን ከፍተው ነው የተቀበሉን” የምትለው ድምጻዊቷ እንዲያውም ለቪድዮው “ቆይ ዘንጠን እንምጣ” እንዳሏት ታስታውሳለች።
እሷ ግን፣ በየትኛውም መደበኛ ቀን ያለውን ድባብ ማሳየት ስለፈለገች “እንደዚሁ በሥራ ልብሳችሁ እያላችሁ ነው የምፈልጋችሁ” ብላ ቀረጻውን ቀጠሉ።
የመንደሩ ነዋሪ መሸ ብሎ እንኳን ቤቱ ሳይገባ አብሯቸው ሠርቷል።
ወደ 50 ሰዎች ባሳተፈው ቪድዮ ቀረጻ ላይ ከልጅ እስከ አዋቂ ለድጋፍ ሲረባረብ እንደነበር ሳትጠቅስ አላለፈችም።
ቀርጸው ሲጨርሱ “በቃ ልትሄዱ ነው” ብለው እያዘኑ ነበር የሸኗቸው።
“ቪድዮው ላይ የሚታዩት ሕጻናት ናቸው ወደ ፏፏቴው የወሰዱን” ትላለች ድምጻዊቷ።
በእርግጥ እንግሊዘኛ ደባልቃ ሙዚቃውን መሥራቷ “አማርኛ እና ጉራግኛውን ጠብቆ ማቆየት የሚፈልገው ማኅበረሰብን ያስቆጣው ይሆን?” ብላ ማሰቧ አልቀረም።
ግን “በጣም በበጎ መንገድ ነው የተቀበሉን። ተመርቀን ነው የተመለስነው” ብላለች።
በእሷ ዕይታ ዜማ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ እንግሊዘኛው መኖሩ መልካም ነው። በዚያ ላይ አድማጯን ያበዛዋል።
“ቴምፖው በአማርኛም በእንግሊዘኛም ተሠርቶ ነበር። የእንግሊዘኛው ይሠራል። ስለዚህ ዕድሉ ከመጣ ከአገሩም ውጭ ያለ ሰው ሊቀበለው ይችላል ብዬ አሰብኩኝ።”
ቪድዮው የተለቀቀው አዲስ እና አንድም ‘ሰብስክራይበር’ በሌለው ዩቲዮብ ገጽ ላይ ነው።
እንዲያው ሰዎች ጋር አይደርስ ይሆን? ብላም ነበር።
ገና የመጀመሪያው ቀን ግን ከማኅበረሰቡ ‘ትልቅ’ የሚባል ሰው ደውሎ “በጣም ደስ ብሎናል፤ እንደግፍሻለን” እንዳላት ትናገራለች።
ቪድዮውን መጀመሪያ ጓጉታ ያሳየችው ለእናቷ ነበር። ለምን እንግሊዘኛ ሆነ? ብለው ቢጠይቁም ኋላ ላይ ግን ወደውታል።
ሳሌሚያ “. . . አብዛኛው ቤተሰቤ አሁን የሚደውሉልኝ እየዘፈኑ ነው። የሚያዋሩኝ ‘ዓለም ብሬሬሬ’ እያሉ ነው” የምትለው በረዥም ሳቅ ታጅባ ነው።
‘ዓለም ብሬ ነይ ነይ’ በጉራጌ ማኅበረሰብ ታዋቂ እና ታታሪነትን የሚያወድስ ዘፈን ነው።
“ያላቸውን ጥንካሬና መንፈሳቸውን ነው የሚገልጸው። ለትውልድ የተሻገረ ታታሪነታቸውን ለማመስገን ነው ያሰብኩት።”
የብር ነገር. . .
አርጋው በዳሶ “ዓለም ሁሌም ብር ናት” ያለበት ቃለ መጠይቅ አለ።
ሳሌሚያ፣ ብር ያስፈላጊነቱን ያህል ጭልጥ አድርጎ የሚወስድ አባዜ እንዳይሆን በሚል የብርን የተቃርኖ ባህሪ በግጥሟ ትዳስሳለች።
“ያላገኙሽ ስም ሰጡሽ
ክፉ አድርገው እየሳሉሽ
ለያዙሽም አትሆኚ
ከነግሥሽ አታስተኚ
እንደው ብትግደረደሪ
ትመጫለሽ አትቀሪ
እንዳላማርር አልጣሽ
አሁንም ነይ ነይ ልጥራሽ. . .”
በድምጻዊቷ ቤተሰብ ውስጥ ለሥራ መትጋት ይበረታታል። ጥረት ይመሰገናል።
“ሰው ለፍቶ ብር ካላገኘ ያማርራል። ከልኩ ሲያልፍም ብሩን ለመጠበቅ እንቅልፍ ያጣል። ማለት የፈለግኩት አማካዩን መንገድ መከተል ያዋጣል ነው። ሥራ ጥሩ ነው ግን ሱስ መሆን የለበትም።”
ከታታሪው ቤተሰብሽ ምት ተማርሽ? ተብላ ስትጠየቅ “እኛ ቤት ያለው ‘work ethic’ ጥሩ ነው። ውጤት ወዲያው ባታይም ሳትደክሚ ሞክሪ ትባያለሽ። ለምን አልተሳካልሽም? ሳይሆን ለምን ጥረት አላደረግሽም? ነው ጥያቄው። ባንቺ በኩል የተቻለሽን ካደረግሽ በቂ ነው። እኔም እሱን ነው ለማድረግ የምሞክረው” ብላ ትመልሳለች።
ሙዚቃውን ለማጠናቀቅ አምስት ወራት ወስዶባታል።
በቪድዮው፣ መርካቶ ጣሪያ ላይ ወጥተው የቀረጹትን ትዕይንት ትወደዋለች።
ከጀርባ ያለው የሥራ ግርግር እና ሱቆች ይታዩበታል።
እሱን ትዕይንት ለማግኘት “ቀላል አልነበረም” ትላለች።
“. . .ባለ ሱቆች እቃቸውን የሚያስቀምጡት ኮርኒስ ላይ ስለሆነ፣ ለሌባ ይዳረግብናል ብለው አንፈቅድም ብለውን ነበር። እንደምንም መጨረሻ ላይ ፈቀዱልንና ቀረጽን።”
ሳሌሚያ እስከዛሬ የት ነበረች?
ከዚህ ቀደም ከፈንድቃ እና ከባህል ማዕከላት ውጪ ሙዚቃ ስታቀርብ አልታየችም።
እንዲያውም ወደ ንግዱ አመዝና ቆይታለች።
የተመረቀቸው በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ነው።
ከዚህ በኋላ ግን ወደ ሙዚቃው ጠቅልላ እንደምትገባ ተስፋ አድርጋለች።
በቅድሚያ ግማሽ አልበም ከዚያ ደግሞ ሙሉ አልበሟን ለማውጣት ዝግጅት ላይ ናት።
“እስካሁን ተደብቄ ነበር. . . አሁን ብዙ ሙዚቃዎቼን ለሰው ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ” ትላለች።
ለምን ተደበቅሽ? ተብላ ስትጠየቅ “ትክክለኛውን ድምጼ እና ትክክለኞቹን ሰዎች እስካገኝ። ምክንያቱም ካወጣሽው በኋላ ሊቆጭሽም ስለሚችል” ስትል ትመልሳለች።
ጊዜዋን ወስዳ የምትወደውን ነገር ለመሥራት መቆየቷን ትናገራለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ዘፈኗን ያቀረበችው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ፈንድቃ ነበር።
ፈርታ እንደነበር ታስታውሳለች። አቀባበሉ ግን አበረታች ነበር።
ከዚያ በኋላ በሌሎች መድረኮችም ላይ ማቅረብ ጀመረች።
“ቤት ውስጥ ያስተሳስረን የነበረው ሙዚቃ ነበር። ሳላስበው ሕጻን እያለሁ ነው ወደ ሙዚቃ የተሳብኩት” ትላለች።
የኮሌጅ ተማሪ ሳለች ነው የሙዚቃ ስቱዲዮ መሄድ፣ የሙዚቃ ግጥም መጠየቅ የጀመረችው። “ጥሩ ድምጽ አለሽ” ትባል እንደነበር ታስታውሳለች።
ከዚያም የራሷን ግጥምና ዜማ መጻፍ ጀመረች።
ጎማ ነጋዴዋ ድምጻዊት
ለአሁኑ የጎማ ነጋዴ ናት።
ሙዚቃ “ራሴን እንዳስተዳድር ካስቻለኝ የሙሉ ጊዜ ሥራዬ ይሆናል” ትላለች።
ሙዚቃን “ከሐሳቤ ጋር የምገናኝበት መንገድ ነው” ብላ ነው የምትገልጸው።
ከሰዎች ጋር ለመተሳሰር፣ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያዩ ለማድረግ፣ ማኅበረሰባቸውን እንዲመለከቱ ለማስቻል፣ ያሳለፉትን ታሪክ ለማስታወስ ይረዳኛል ብላ ታምናለች።
ለዚህም ነው “በሙዚቃ ራሴን መግለጽን እወደዋለሁ” የምትለው።
ሕልሟ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የራሷን ድርሻ ማበርከት እንደሆነ ትገልጻለች።
“ከቻልኩኝ፣ ሰው የሚተሳሰርበት ሙዚቃ መሥራት እፈልጋሁ። ለራሴ ታማኝ ሆኖ መቀጠል ነው የምፈልገው” በማለት ትገልጻለች።
ሳሌሚያ ከምትወዳቸው ድምጻውያን መካከል አስቴር አወቀ፣ አብነት አጎናፍር፣ አበባ ደሳለኝ እና ሮፍናንን ትጠቅሳለች።
አበባ፣ ቪድዮዎቿን ስለምትወዳቸው ሮፍናን ደግሞ “በተቻለው መጠን ከሳጥኑ ወጥቶ እየለፋ ስላለ” ታደንቃቸዋለች።
እሷ ሙዚቃ ስትሰማ የምትወደውን ዜማ መስማት እንደምትፈልገው ሁሉ ለገበያም ማቅረብ የምትፈልገው ያንኑ ዓይነት ሙዚቃ ነው።
በእርግጥ ‘ከሳጥኑ መውጣት’ ቀላል አይደለም።
“ገበያው የማይቀበለውን ሥራ አትሥሪ እባላለሁ። ግን ለራስሽ ታማኝ ስትሆኚ ገበያው ይቀበለዋል ብዬ አስባለሁ” ትላለች።
ሳሌሚያ እንደምትለው፣ ራስን ሲገልጹ ለራስ ታማኝ መሆን አዋጪው መንገድ ነው።
“ስለዚህ በተለመደው ሳጥን ውስጥ ታጥሬ መቀመጥ አልፈለግኩም። ከሳጥን መውጣት ከሌለ አዲስ ድምጽ፣ አዲስ ዜማ፣ አዲስ ሙዚቃ አይመጣም። ከተመለደው መውጣት ቀላል ባይሆንም መልካሙ መንገድ ነው።”