ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታንያሁ የጋዛ ውይይት ሁሉንም ታጋቾች በአንድ ጊዜ ማስለቀቅ ላይ እንደሚያተኩር ጠቆሙ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የተኩስ አቁም ለመድረስ የሚደረግ ውይይት የተቀሩትን ታጋቾች በሙሉ ማስለቀቅ ላይ እንደሚያተኩር ጠቆሙ።
ቀደም ሲል ውድቅ የሆነው እና ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲደረግ የነበረው ውይይት በሕይወት ያሉትን ታጋቾች በከፊል ማስለቀቅ ላይ ያተኮረ ነበር።
ሐማስ የመሪዎቹ የልዑካን ቡድን ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር "ቅድመ ውይይት" ለማድረግ ካይሮ እንደሚገኙ ተናግሯል።
ዘገባዎች አንደሚጠቁሙት በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ከስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል እድል መኖሩን አደራዳሪዎቹ ተስፋ አድርገዋል።
ባለፈው ወር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተዘዋዋሪ የሚደረጉ ንግግሮች ከፈረሱ በኋላ እስራኤል ወታደራዊ ጥቃቷን ለማስፋት እና ሁሉንም የጋዛ ሰርጥ ለመቆጣጠር አወዛጋቢ እቅድ እንዳወጣች ያስታወቀች ሲሆን ይህም ከሁለት ሚሊዮን በላይ የፍልስጤም ነዋሪዎቿ የተጠለሉባቸውን አካባቢዎች ይጨምራል።
ሆኖም የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ይህ አዲሱ ዕቅድ ወታደራዊ ዝግጅት ስለሚያስፈልገው እና የተጠባባቂ ኃይሉን በስፈፋት መጥራት ስለሚያስፈልግ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ይጀምራል ብለው አይጠብቁም ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ከባድ የእስራኤል ጥቃት የቀጠለ ሲሆን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ቀን ቢያንስ 123 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል።
እስራኤል በተለይ በጋዛ ከተማ ላይ የምታደርሰው ጥቃት የመኖሪያ ቤቶችን ማውደሟን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከጋዛ ከተማ በስተምሥራቅ በሚገኘው ዛይቶን አካባቢ በተፈጸሙ ጥቃቶች የተነሳ የደረሱ ውድመቶችን አሳይተዋል።
ረቡዕ ማለዳ አል ሺፋ ሆስፒታል ከከተማው በስተደቡብ በምትገኘው ቴል አል ሃዋ የመጠለያ ድንኳኖች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰባት ሰዎች፣ አምስቱ ሕጻናት ናቸው፣ ተገድለዋል ብሏል። አል አህሊ ሆስፒታል በከተማዋ በምሥራቅ ዛይቱን አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
የእስራኤል ጦር በዛይቱን አዲስ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር አዛዥ ሌተና ጄኔራል ኢያል ዛሚር በጋዛ ሰርጥ የሚገኘውን የጦሩን የዘመቻ ዕቅድ ዋና ማዕቀፍ አጽድቀዋል ሲል ጦሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት ከአይ24ኒውስ የእስራኤል ቲቪ ቻናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከፊል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆን ተጠይቀዋልል።
"በቅርባችን ያለ ይመስለኛል" ሲሉ መልሰዋል።
"እኛ ሞክረናል፣ ሁሉንም ዓይነት ሙከራዎች አድርገናል፣ ብዙ አሳልፈናል፣ ነገር ግን እያሳሳቱን እንደሆነ ደረስንበት።"
ታጋቾችን በተመለከተም ሲናገሩ "ሁሉንም ማስለቀቅ እፈልጋለሁ" ብለዋል። "አሁን ያለንበት ደረጃ፣ በሕይወት ያሉ እና የሞቱትን ታጋቾች በሙሉ ማስለቀቅ የሚል ነው።"
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ከመስከረም 26 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት ካገታቸው ሰዎች መካከል 50 ያህሎሉ አሁንም በቁጥጥሩ ስር ይገኛሉ።
እስራኤል 20 ያህሉ አሁንም በሕይወት እንዳሉ ታምናለች።
ኔታንያሁ በአገር ውስጥ የታጋቾቹን መለቀቅ እንዲሁም ጦርነቱን ለማስፋት የያዙትን ዕቅድ ላይ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው ነው ።
ባለፈው ሳምንት ስማቸው ያልተጠቀሰ የአረብ ባለስልጣናት እንደተናገሩት የቀጣናው አሸምጋዮች ግብፅ እና ኳታር ጦርነቱ እንዲያበቃ እና የእስራኤል ወታደሮች ለቅቀው እንዲወጡ ለማድረግ የተቀሩትን ታጋቾች በሙሉ መልቀቅን የሚያካትት አዲስ ማዕቀፍ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል ሐማስ ጋዛ ላይ ያለውን ቁጥጥር እንዲተው እንዲሁም ትጥቆቹን እንዲፈታ እየጠየቀች በመሆኑ ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን አስቸጋሪ ይሆናል።
ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ማክሰኞ ዕለት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ካይሮ አሁንም ከኳታር እና ከአሜሪካ ጋር በመሆን ቀደም ብሎ የወጣው ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ትልቅ ጥረት እያደረገች መሆኑን የተናገሩት።
"ዋናው ግብ ወደ ዋናው ምክረ ሃሳብ መመለስ ነው፤ ይህም ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፤ የተወሰኑ ታጋቾችን እና አንዳንድ የፍልስጤም እስረኞችን መልቀቅ እና ያለምንም መስተጓጎል የሰብዓዊ እና የሕክምና እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ መፍቀድ ናቸው" ብለዋል አብደላቲ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የእስራኤል ዓላማ አልተለወጠም ሲሉ ተናግረዋል። ጦርነቱ የሚቆመው ሁሉም ታጋቾች ሲለቀቁ እና ሐማስ እጅ ሲሰጥ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኔታንያሁ አክለውም እስራኤል በጋዛ ላይ ክፍት የሆነ የፀጥታ ቁጥጥር ማድረግ አለባት ብለዋል።
ሐማስ ለረዥም ጊዜ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞች ለማስፈታት እና ታጋቾች ለመልቀቅ የሚያስችል አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረስ ሲጠይቅ ቆይቷል።
በተጨማሪም ጦርነቱ እንዲያበቃ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ጋዛን ለቅቆ እንዲወጣ ይፈልጋል።
ነፃ የፍልስጤም መንግሥት እስካልተመሰረተ ድረስ ትጥቁን ለመፍታት ፈቃደኛ አይደለም።
ኔታንያሁ ከአይ24ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ፍልስጤማውያን "በፈቃደኝነት" ግዛቱን ለቅቀው እንዲወጡ ያላቸውን ሀሳብ በድጋሚ ሲናገሩ "እንዲወጡ እየተገፉ አይደሉም፣ እንዲወጡ ይፈቀድላቸዋል" ብለዋል።
በመቀጠልም "ለፍልስጤማውያን የሚቆረቆሩ እና ፍልስጤማውያንን መርዳት እንፈልጋለን የሚሉ ሁሉ እኛን ማስተማራቸውን ትተው በራቸውን ክፍት ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል።
ፍልስጤማውያን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና በርካታ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ከጋዛ በግዳጅ ሰዎችን ማፈናቀል ዓለማቀፍ ሕግን የሚጥስ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ብዙ ፍልስጤማውያን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1948 የእስራኤል መንግሥት ከመፈጠሩ በፊት እና በኋላ በነበረው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተሰደዱበት ወይም ከቤታቸው የተባረሩበት "ናክባ" (ቀውስ) ብለው የሚጠሩት ወቅት እንዳይደገም ፈርተዋል።
አብዛኛዎቹ የጋዛ ነዋሪዎች የእነዚያ የመጀመሪያ ስደተኞች ቤተሰቦች ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ ባለሙያዎች እስራኤል የምትፈቅደውን የሰብዓዊ እርዳታ መጠን በእጅጉ በመገደቧ የተነሳ በጋዛ ከፍተኛ ረሃብ እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ በጋዛ ያለው ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስጠንቅቋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት እስካሁን 61,722 ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል።
አክሎም 106 ሕጻናትን ጨምሮ 235 ሰዎች በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሞታቸውንም አስታውቋል።