ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፖላንድ ቀጥላ ሮማኒያ የሩሲያ ድሮኖችን የአየር ክልሏን ጥሰው በመግባት ከሰሰች
ሮማኒያ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የአየር ክልሌን ጥሰው ገብተዋል ስትል ክስ አቀረበች።
ሮማኒያ የሩሲያ ድሮኖች የአየር ክልሌን ጥሰዋል ያለቸ ሁለተኛዋ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል አገር ሆናለች።
ቅዳሜ ዕለት የሮማኒያ ተዋጊ ጄቶች በዩክሬን የተፈጸመውን የሩሲያ ጥቃት በመከታተል ላይ ሳሉ በደቡባዊ ድንበር አካባቢ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ማየት መቻላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጥሰቱ ስህተት ሊሆን አይችልም ያሉ ሲሆን "በሩሲያ የታየ ጦርነት የማስፋት ግልፅ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ሩሲያ አስካሁን በሮማኒያ ውንጀላዎች ላይ አስተያየት አልሰጠችም።
ረቡዕ ዕለት ፖላንድ ወደ አየር ክልሏ የገቡትን ቢያንስ ሦስት የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
የሮማኒያ መከላከያ ሚኒስትር ሁለት ኤፍ-16 ጄቶች አገሪቱ ከዩክሬን ጋር ያላት ድንበር አካባቢ ቅኝት በሚያደርጉበት ወቅት "ሩሲያ በዩክሬን ዳኑቤ የሚገኘውም መሠረተ ልማት ካጠቃች በኋላ" ድሮኖቿን በአየር ክልላቸው ውስጥ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
ድሮኖቹ የታዩት በደቡብ ምዕራብ ቺሊያ ቪቼ በተባለ መንደር 20 ኪሎ ሜትር ላይ ሲሆን፣ ወዲያው ከራዳር ዕይታ መሰወራቸው ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ አክሎም ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ አለመብረራቸውን ወይንም ግልጽ የሆነ አደጋ አለመደቀናቸውን አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ሁኔታውን "ሌላ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ሉዓላዊነት ጥሰት" ሲሉ ኮንነውታል።
ቅዳሜ ዕለት ፖላንድ የሩሲያ ድሮኖችን በሚመለከት ላለባት ስጋት ምላሽ ሰጥታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ "ፖላንድ እና አጋሮቿ የአየር ክልላችንን የመከላከል ዘመቻ ጀምረዋል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
"በምድር ላይ ያሉ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ናቸው" ሲሉም አክለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጦሩ በፖላንድ ውስጥ የሚገኙ ተቋማትን የማጥቃት "ዕቅድ እንደሌለው" አስታውቆ ነበር።
የሩሲያ የቅርብ አጋር የሆነችው ቤላሩስ ረቡዕ ዕለት ወደ ፖላንድ የገቡት ድሮኖች የበረራ መስመራቸው ላይ መታፈን ከገጠማቸው በኋላ በስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
እሁድ ዕለት ቼክ ሪፐብሊክ ወደ ፖላንድ ልዩ ዘመቻውን የሚያግዝ ሂሊኮፕተር መላኳን አስታውቃለች።
ቡድኑ ሦስት ኤምአይ-171ኤስ ሂሊኮፕተሮች ያካተተ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 24 ሰዎችን እና ለውጊያ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን የመጫን አቅም አላቸው ተብሏል።
ይህ እርምጃ የመጣው ሩሲያ የኔቶን ምሥራቃዊ ክፍል የአየር ክልል መጣሷን ተከትሎ መሆኑን የቼክ መከላከያ ሚኒስትር ጃና ሴሬኖቾቫ ተናግረዋል።
በቅርቡ የተፈጠረውን የአየር ክልል ጥሰትን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሲናገሩ የሩሲያ ጦር "ድሮኖቹ ወዴት አንደሚሄዱ እና በአየር ላይ ምን ያህል እንደሚቆዩ ጠንቅቀው ያውቃል" ብለዋል።
በተደጋጋሚ ምዕራባውያን አገራት በሩሲያ ላይ ጠበቅ ያለ ማዕቀብ እንዲጥሉ ሲጠይቁም ተደምጠዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩሲያ የሌላ ሉዓላዊ አገር የአየር ክልል መጣሷን በተመለከተ ሲናገሩ ጠንካራ ማዕቀብ ለመጣል "ዝግጁ" መሆናቸውን አስታውቀው፤ የኔቶ አባል አገራት ከሩሲያ የነዳጅ ዘይት መግዛት እንዲያቆሙ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የፈጸመችው በአውሮፓውያኑ የካቲት ወር 2022 ሲሆን፣ ቀስበቀስ የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠር ችላለች።
በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ዶናልድ ትራምፕ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ሩሲያ ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን ከአሜሪካው አቻቸው ጋር በአላስካ ከተገናኙ በኋላ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።