በትዳር ውስጥ የልጅ መወለድ ለምን በጥንዶች ግንኙነት ላይ መሻከርን ይፈጥራል?

ሆሊ መንታ ልጆች እንዳረገዘች ስታውቅ ሕይወቷ እስከ ወዲያኛው እንደሚቀየር ተገንዝባለች። መውለዷ ከአምስት ዓመት አጋሯ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚለውጠው ግን አልጠበቀችም።

ከወለደች በኋላ እስከ መለያየት የሚያደርስ ጸብ ውስጥ ይገቡ ጀመር።

ካናዳ የምትኖረው ሆሊ እንደምትለው የማያግባባቸው ዋነኛው ነገር የሥራ ክፍፍል ነው።

አጋሯ ቤት በማጽዳት፣ ልብስ በማጠብ እና በማብሰል ቢያግዛትም፤ እሷ ድጋፍ የፈለገችው ከልጆች አስተዳደግ ጋር በተያያዘ ነበር።

“በቀዶ ሕክምና ነው የወለድኩት። ሰውነቴ ተዳክሞ ነበር። ሁለት ልጆች ቀኑን ሙሉ አጠባ ነበር። አልተኛም። የትዳር አጋሬ ግን ማገዙን ትቶ ልጆቹ እኔን ብቻ እንደሚፈልጉ ይነግረኛል” ስትል ትገልጻለች።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጥንዶች ልጅ ከወለዱ በኋላ ግንኙነታቸው ይለወጣል።

እአአ በ2021 በበርን ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ልጅ ከተወለደ በኋላ የጥንዶች ግንኙነት ውጣ ውረድ ሲገጥመው፣ ልጅ ቢወልዱም ባይወልዱም በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ትስስራቸው ይቀንሳል።

ልጅ ያላቸው ጥንዶች ከሌላቸው ጥንዶች ባነሰ እንደሚደሰቱ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይ ጨቅላ ሕጻናት ያሏቸው እናቶች ደስታ እስከ 38 በመቶ ዝቅ ይላል።

አግብተው ያልወለዱ ሴቶች ደስታ ወደ 62 በመቶ ይጠጋል ይላል።

ልጅ ሲመጣ የጥንዶች ግንኙነት መፈተኑ አይቀርም።

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት መነጋገር፣ መቀራረብ እና አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ልጆች ሲወለዱ ይቀንሳሉ። በዚያ ላይ እንቅልፍ ማጣት እና የገንዘብ ውስንነት ይጨመራል።

ስለዚህ በየጊዜው መጋጨት እየበዛ ይሄዳል።

ይህ ጉዳይ እምብዛም ስለማይወራ ጥንዶች ግንኙነታቸው ሲሻክር ይደናገጣሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታዩት ከልጆቻቸው ጋር የሚስቁ ወላጆች ናቸው። ስለ ወላጅነት ትምህርት ሲሰጥም ልጅ ከመውለድ በኋላ የሚመጣው መራራቅ አይወራም። በቤተሰብ ዘንድም ተድበስብሶ ነው የሚያልፈው።

ጥንዶች የሚጣሉት ልጅ በመውለዳቸው ብቻ አይደለም። የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ስቴሲ ሽሬል እንደምትለው፣ ልጅ ከመምጣቱ በፊት ጥንዶች በቅጡ የማይግባቡ ከሆነ ልጅ ሲወለድ ስንጥቁ ይሰፋል።

“ከመጀመሪያውም ጥሩ የወሲብ ሕይወት የሌላው ጥንዶች፣ ልጅ ከወለዱ በኋላ የበለጠ ችግራቸው ይጎላል” ትላለች።

ከጥንዶቹ አንዳቸው የነበራቸው አናዳጅ ባህሪ ልጅ ከተወለደ በኋላ ለሌላኛቸው ጎልቶ ይታያል።

ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ጥንዶችም መፈተናቸው ግን አይቀርም።

ስለ ወላጅነት ግልጽ ውይይት እና ንግግር እንዲኖር ባለሙያዋ ታበረታታለች።

ኒው ዮርክ የምትኖረው ጋዜጠኛ ጃኔስ ዱን፣ ልጅ ከወለዱ በኋላ ስለሚፈጠር የትዳር መቃቃር መጽሐፍ ጽፋለች።

10 ዓመት አብረው ኖረዋል። ትስስራቸው ጠንካራ እንደሆነ ያምኑ ነበር። አንዳቸው ስለሌላቸው ጠንቅቀው እንደሚያውቁም አስበዋል።

የቤት ውስጥ ሥራ እኩል ስለሚካፈሉ የልጅ እንክብካቤም እንደዚያ እንደሚሆን ነበር የገመቱት።

ሊገጥማቸው የሚችለውን ፈተና አስቀድመው ቢነጋገሩም እርስ በእርስ ከመጠላላት አልዳኑም።

ልጅ አስተዳደጉን ለእሷ ሲተው፣ እሷ ደግሞ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ስትሞክር ነገሮች ተባባሱ።

“50 በመቶው ችግር የእኔ ነበር። አሁን ሳስበው ከፍተኛ ቁጣ ውስጤ ነበር” ትላለች። ባሏን ስትቆጣው እሷን ትቶ ስልኩ ላይ ጊዜ ማጥፋት ጀመረ። እያንዳንዱ ንግግር ወደ ጸብ ያመራ ነበር።

ለንደን የሚኖረው አንዲም ተመሳሳይ ታሪክ አለው። ከባለቤቱ ጋር በጣም ቢቀራረቡም ሁለት ልጆች ከወለዱ በኋላ ነገሮች እንደ ቀድሞው አልሆኑም።

የመጀመሪያ ልጃቸው ካልታቀፈ አይተኛም ነበር።

ሁለተኛ ልጅ ሲወልዱ የኃላፊነት መጠኑ ከፍ አለ።

“ብዙ ሥራ ነበረብን። ከአቅሜ በላይ ሆነ። ሁሌ ማልቀስ ብቻ ሆነ” ሲል ያስታውሳል።

ፆታን መሠረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል ባለበት ማኅበረሰብ ልጅ ሲወለድ የሥራ ጫናው በሴቶች ላይ ይበረታል።

ልጅ ሲወለድ የቤተሰቦች ባህሪ ላይም ለውጥ ይመጣል።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ እንደምትለው፣ ወላጆች እንዴት ባህሪያቸው እንደሚለወጥ ላያውቁ ይችላሉ።

የሰውነት እና የባህሪ ለውጥ ይስተዋላል። ይህንን ለውጥ መረዳት ያልቻሉ ሰዎች ከአጋራቸው ጋር ለመግባባት ይቸገራሉ።

ወላጅ ከመሆን ጋር አብረው የሚመጡ የሥነ ልቦና ለውጦችም አሉ።

ድባቴ እና ሌሎችም ችግሮች የሚገጥሟቸው እንዳሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ከአራት እናቶች አንዷ እና ከአስር አባቶች አንዱ ይህ ድባቴ ይገጥማቸዋል።

ሚሺጋን የሚኖረው ማት አባት ሲሆን፣ ባለቤቱ ልጅ ከወለደች በኋላ የገጠማት ድባቴ (postpartum) ዘለግ ያለ ጊዜ እንደወሰደ ይገልጻል።

“የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከባድ ነበሩ። በተለይ የቤተሰብ ድጋፍ ከሌለ በጣም ያስቸግራል። ባለቤቴ ከፍተኛ ጭንቀት ገጥሟት ነበር። ልጃችን መታመሙ ደግሞ ሌላ ጭንቀት ፈጠረ” ይላል።

ማትም ጭንቀት ገጥሞት ነበር።

ልጃቸውን ሲያቅፍ ጭንቀቱ ቢለቀውም ልጃቸው ሲተኛ ተመልሶ ወደ ጭንቀት ይገባ ነበር።

በዚህ ምክንያት ባለቤቱን በአግባቡ ማናገርም አልቻለም።

እሷም ቁጣው የበለጠ ያስቆጣታል።

በስድስት ዓመታት ግንኙነታቸው እንዲህ በተደጋጋሚ ተጣልተው አያውቁም ነበር።

ልጃቸው በተወለደ በሁለተኛው ዓመት ግን እርስ በእርስ ለመግባባት የተሻለ መንገድ አገኙ። ይህም ግንኙነታቸውን አጠናከረው።

አካላዊ ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ባይታደስም መነጋገር ችለዋል።

“እናት ከመሆን ጋር ተያይዞ የመጣ ሊሆን ይችላል ትላለች። ግን እንደ ቀድሞው አሁን አንተቃቀፍም። የወሲብ ሕይወታችንም እንደ ድሮው አይደለም” ይላል።

ባለቤቱ በራስ መተማመኗ እንደቀነሰ ብትነግረውም፣ እሱ የሚያስበው ፍቅሯ እንደቀነሰ ነው።

ቨርጂንያ ውስጥ የምትኖረው ኤሪን ከሁሉም በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያስደስታት ሰው ናት።

ነፍሰ ጡር ሆናም ስፖርት ታዘወትር ነበር።

ስትወልድ ግን ለራሷ የምትሰጠው ጊዜ እና ቦታ ተነነ።

በወለደች በአምስተኛው ሳምንት ድባቴ ውስጥ ገባች።

“የቀድሞ ሕይወቴ ይናፍቀኝ ጀመር። ያጣሁትን ማሰብ ጀመርኩ። ደስታ ራቀኝ” ስትል ነው የምትገልጸው።

ባለቤቷ ከእሷ በተቃራኒው ሕይወትን የሚያጣጥም ሆነ። ከልጃቸው አይለይም።

ጥንዶቹ ብቻቸውን የሚያሳልፉት ጊዜ አልነበረም።

ልጃቸው የበለጠ የሚቀርበው አባቱን ሆነ።

ነገሮች ተደራርበው ግንኙነታቸውን አጠለሹት።

ብዙ ወላጆች የሚገጥማቸውን ችግር አምነው እርዳታ አይጠይቁም።

ለጓደኞቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው መንገርም ያሳፍራቸዋል።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ካነጋገረቻቸው ጥንዶች ወደ 95 በመቶ ግንኙነታቸው እንደሻከረ ነግረዋታል።

ሆሊ በባለቤቷ መበሳጨት እንደጀመረች ለሌሎች ቤተሰቦች ስትናገር እምብዛም የተቀበላት አልነበረም። ችግሩ የእሷ እንደሆነ እንዲሰማት ያደረገ አጋጣሚ ነበር።

ሌላዋ የሥነ ልቦና ባለሙያ ጃኒና ቡህለር “ሰዎች በግንኙነታቸው ሁሌም ደስተኛ እንዲሆኑ መጠበቅ ስህተት ነው። ሁሌ ደስታ የለም” ትላለች።

ጥንዶች የገጠማቸውን ችግር ካላወሩ ወደ ሥነ ልቦና ባለሙያ መሄድ አይችሉም።

ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ የበይነ መረብ ገጾችም አሉ።

ወላጆች የሚገጥማቸውን ፈተና በማውራት እርስ በእርስ ሊማማሩ እና ሊደጋገፉ ይችላሉ።

ሆሊ እሷን የሚመስሉ ወላጆች ስታገኝ ነው እፎይታ የተሰማት።

“ከእኔ ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ እንዳሉ ገባኝ። ሰዎች ስለማያወሩ ነው እንጂ ችግሩ የጋራ ነው” ትላለች።

አንዳንድ ጥንዶች ችግራቸውን መፍታት ሳይችሉ ቀርተው ይለያያሉ።

ትዳራቸውን ለማዳን ቢሞክሩም አይሳካም። መሰናክሉን የሚያልፉ ጥንዶችም አሉ።

ስሜትን በግልጽ መነጋገር፣ መረዳዳት፣ መደማመጥ እና የጋራ ጊዜ ማሳለፍም ይመክራሉ። አንድ ሰው ምሉዕ እንዳልሆነ ተረድቶ ከአጋር ፍጹምነትን አለመጠበቅ ሌላው ነው።

ወደ ጥንዶች የሥነ ልቦና አማካሪ መሄድ ሌላው አማራጭ ተደርጎ ይቀመጣል።

ሆሊ እና አጋሯ የወሰዱት አማራጭ ባለሙያ ማነጋገር እንደነበር ትናገራለች።

“ልጆቼ እኔን ሁሌ ይፈልጉኛል። ያለኝን ሰዓት ከአጋሬ ጋር በመጣላት ማሳለፍ የለብኝም ብዬ ወሰንኩና ወደ ባለሙያ ሄድን። በጣም ነው ባለሙያው የረዱን” ስትል ተሞክሮዋን ታካፍላለች።

አንዲ ከአጋሩ ጋር ግንኙነታቸው የተሻሻለው በግልጽ መነጋገር ሲጀምሩ እንደሆነ ይናገራል።

“አንዳችን ሌላችን ላይ የማንወደው ነገር ስናይ መነጋገር ጀመርን” ይላል።

ከዓመታት ጥረት በኋላ ግንኙነታቸውን ማደስ የሚችሉ ጥንዶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ሁሉም ሰው ወደ ሥነ ልቦና አማካሪ መሄድ ወይም ልጆቹን የሚንከባከብለት ሰው አግኝቶ ከአጋሩ ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ አይቻል ይሆናል።

ነገር ግን ችግሩን መፍቻ አማራጭ መንገዶች ብዙ ናቸው።