ገንዘብ ማተም ምንድን ነው? ለኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትስ መፍትሔ ይሆናል?

ጎረቤት አገር ኬንያ ክፉኛ በዕዳ መዘፈቋን ተከትሎ አንድ ሰሞን የአገሪቱ ወጣቶች ወደ ማኅበራዊ ሚድያው ዘመቱ።

ወጣቶቹ በተለይ ትዊተር በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ “ኬንያ ዕዳ ካስጨነቃት ለምን ብዙ ብር አታትም?” ሲሉ ጠየቁ።

የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ በፈረንጆቹ 2021 ባወጣው ዘገባ መሠረት አገሪቱ ከ8 ትሪሊዮን ሽልንግ ወይም ከ72 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ አለባት።

ነገር ግን ኬንያ ብር አትማ ዕዳዋን ከመክፈል ይልቅ አጠቃላይ አገራዊ ምርቷን ለማሳደግ እንደምትሠራ አሳወቀች።

በአንድ አገር ገበያ ላይ የሚሽከረከረው የገንዘብ መጠን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር እኩል መሆን እንዳለበት የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ያስተምራል።

ልክ እንደ ኬንያ ሁሉ ከፍተኛ ዕዳ ያለባት ኢትዮጵያ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበትን ለመግታት ብር ማተም አለባት የሚሉ ድምፆች መሰማት ጀምረዋል።

የዋጋ ግሽበት የአንዲት አገር የገንዘብ አቅርቦት ከምጣኔ ሃብታዊ ምርት በላይ በፍጥነት ሲያድግ የሚከሰት ነው።

በአንዳንድ አገራት ገበያው ላይ ያለው ገንዘብ ሲበዛ የዋጋ ግሽበት በመከሰት ፈንታ ‘ሃይፐርኢንፍሌሽን’ አሊያም ‘ዲፍሌሽን’ ይከሰታል።

‘ሃይፐርኢንፍሌሽን’ ማለት የዋጋ ግሽበቱ በጣም በፍጥነት ሲያድግና ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን የሚከሰት የምጣኔ ሃብት ቀውስ ነው። ብዙውን ጊዜ ወርሃዊ የዋጋ ንረት መጠኑ ከ50 በመቶ በላይ ሲሆን ‘ሃይፐርኢንፍሌሽን’ ይባላል።

‘ዲፍሌሽን’ ደግሞ የምርት ዋጋ ቀስ በቀስ ሲቀንስ እና የገንዘብ የመግዛት አቅም ሲጨምር የሚከሰት ነው።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ብር ብታትም የዋጋ ግሽበቱ ይቀንሳል ወይስ ይብሳል? ተጨማሪ ገንዘብ ማተምስ መፍትሔ ይሆናል?

ገንዘብ ማተም

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት የመገበያያ ገንዘባቸውን አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ባሉ ኩባንያዎች አሳትመው ወደ ማዕከላዊ ባንካቸው ያስገባሉ፣ ለዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ።

ነገር ግን እንደ አሜሪካ ያሉ የምጣኔ ሃብት ኃያላን የሚባሉ አገራት የባንከ ኖቶቻቸውን አገር ውስጥ የማተም ግዴታ አለባቸው።

ለመሆኑ ገንዘብ አትሞ ወደ ገበያ ማሰራጨት ማለት ምን ማለት ነው?

ቴድሮስ መኮንን (ዶ/ር) የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር የኢትዮጵያ ወኪል ናቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካሪ ሆነውም ያገለግላሉ። አልፎም የኢትዮጵያ ጆርናል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኃላፊ ናቸው።

በተለምዶ ገንዘብ ማተም ተበሎ የሚጠራው ሐሳብ የአንድ አገር ማዕከላዊ ባንክ አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ሲያሰራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ይህንን በአገር ቤት ምሳሌ ሲያስረዱ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት ብድር ሲሰጥ ወይም ደግሞ ለባንኮች ‘ሊኩዊዲቲ’ ሲለቅ፤ አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው እየገባ ነው ማለት እንችላለን” ይላሉ።

ይህ ገንዘብ ከዚህ ቀደም ታትሞ በማዕከላዊው ባንክ ቋት (ሪዘርቭ) ውስጥ የተቀመጠ አሊያም ደግሞ እንደ አዲስ የታተመ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ምሑሩ እንደሚያስረዱት ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ የሚኖረው ገንዘብ ማተሙ ሳይሆን ከብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ወደ ገበያ ሲሰራጭ ነው።

ብሔራዊ አሊያም ማዕከላዊ ባንኮች ዋና ዓላማቸው ዋጋ ማረጋጋት አሊያም ምጣኔ ሃብቱ የተረጋጋ እንዲሆን ማድረግ ስለሆነ፣ የሚያትሙትን ገንዘብ የሚመጥኑት በአገር ውስጥ ምን ያህል ምርት ተመርቷል፤ አንድ ዕቃ ለመግዛት ምን ያህል ብር ያስፈልጋል የሚለውን ከግምት አስገብተው ነው።

አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አዲስ ገንዘብ አትሞ ወደ ገበያው ለማሰራጨት አሊያም ገበያው ላይ ያለውን ገንዘብ ለመቆጣጠር አንዱ አስፈላጊ አጀንዳ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ምሑራን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከታክስ እና ከሌሎች ገቢዎች እንዲሁም ከብድር እና ከእርዳታ በሚያገኘው ገንዘብ ወጪውን ይሸፍናል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ተደምሮ ወጪውን ለመሸፈን በቂ ካልሆነ ከብሔራዊ ባንክ ይበደራል።

“መንግሥት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ተበደረ ማለት አዲስ ገንዘብ እየወሰደ ነው ማለት ነው። ይህ በጣም ከበዛ የዋጋ ንረት ያመጣል” ይላሉ ቴድሮስ (ዶ/ር)።

አዲስ ገንዘብ እና የኑሮ ውድነት

የምጣኔ ሃብት ምሑራን በተለያየ ነገር ላይስማሙ ይችላሉ። በአንድ ነገር ግን አቋማቸው ተመሳሳይ ነው። “አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ማሰራጨት የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል እንጂ አያረጋጋውም” በሚለው።

ተሾመ ተፈራ (ዶ/ር) የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ናቸው። ሁሉም አገራት ገንዘብ ማተም ቢችሉም፣ ነገር ግን በፈለጉት ጊዜ እየተነሱ ማተም እንደማይችሉ ይናገራሉ።

“ለዚህ ነው ገንበዝ ማተም አዲስ ነገር ባይሆንም የኑሮ ውድነትን ሊያመጣ ስለሚችል ከምጣኔ ሃብት ጋር መጣጣም አለበት የምንለው” ይላሉ።

ምሑሩ እንደሚያስረዱት ገንዘብ ማተም አሊያም አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ማሰራጭት እና የኑሮ ውድነት ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው።

“ለምሳሌ ብዙ ገንዘብ ሲታተም ሰዎች ኪስ ውስጥ ገንዘብ ይበዛል ማለት ነው። ገበያው ውስጥ ያለው ምርት እና አልግለግት ግን ውሱን ነው።”

ቴድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት አንደኛው ተጠያቂ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው ገንዘብ እንደሆነ ያምናሉ።

“በእኛ አገር በሚያሳዝን ሁኔታ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበት ልምድ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰተው የዋጋ ንረት አንዱ መንስዔ ይህ ነው። መንግሥት ለተለያዩ ወጪዎች ስለሚያስፈልገው አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ይለቀቃል።”

ሁለቱም ያናገርናቸው ምሑራን እንደሚያስረዱት ገበያው ላይ ያለው የገንዘብ መጠን ከምርት እና አገልግሎቱ ጋር ካልተጣጣመ የብር የመግዛት አቅም እየተዳከመ የምርት እና የአገለግሎት ዋጋ ግን እየናረ ይሄዳል።

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መጠን (ኢንፍሌሽን) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቷል። ለምሳሌ በፈረንጆቹ 2021 የዋጋ ንረቱ 26 በመቶ ደርሶ እንደነበር የዓለም ባንክ ዘገባ ያሳያል። በ2022 ደግሞ ወደ 37 በመቶ እንዳደገ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቴድሮስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ‘ኢንፍሌሽን’ ወደ ‘ሃይፐርኢንፍሌሽን’ (የከፋ የዋጋ ንረት) እያመራ ነው ይላሉ።

“በርካታ አገራት ከ7 እስከ 15 በመቶ የዋጋ ግሽበት ነው ያላቸው። ለዚያውም ዓለም በከፍተኛ የዋጋ ንረት እየተናጠች ባለችበት በዚህ ወቅት። አሁን ባለው ሁኔታ ወደዚያ (ሃይፐርኢንፍሌሽን) እያመራን ነው ማለት ይቻላል።”

ተሾመ (ዶ/ር) እንደሚሉት ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በ1930ዎቹ ምዕራባዊያን ካጋጠማቸው ‘ግሬት ዲፕሬሽን’ (ታላቁ የምጣኔ ሃብት ድቀት) ጋር ይመሳሰላል ይላሉ።

እንደ ምሑሩ ገለጻ በ1930ዎቹ ምዕራባውያን ሁለት ነገር ነው ያጋጠማቸው። የኑሮ ውድነት እና የምጣኔ ሃብት መቀንጨር። በዚህ ወቅት አገራቱ አዲስ ገንዘብ አትመው ወደ ገበያው አሰራጭተው እንነበር ያወሳሉ።

ስለዚህ ገንዘብ አትሞ ወደ ገበያው በማሰራጨት የገንዘብ አቅርቦትን ጨምሮ ያንቀላፋውን ኢኮኖሚ መቀስቀስ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ሊሆን ይችል የሚል እምነት አላቸው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ገበያው ላይ ያለው ገንዘብ እና ባንኮች ውስጥ የተቀመጠው (ዲፓዚት) ገንዘብ 1.3 ትሪሊዮን ብር ገደማ እንደደረሰ ይናገራሉ።

እየተዘዋወረ ያለው ገንዘብ “በዚህ መጠን እየጨመረ ባለበት ወቅት ሌላ ብር ማተም ትልቅ ጥያቄ የሚያነሳ ጉዳይ ነው።”

መፍትሔው ምን ይሆን?

“አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ማስገባት በምንም ተዓምር የዋጋ ግሽበቱን አይገታም። ገንዘብ መሰብሰብ ግን የዋጋ ግሽበቱን ይገታል” ይላሉ ቴድሮስ (ዶ/ር)።

የዋጋ ግሽበቱን ለመግታት መንግሥት የገንዘብ ልቀቱን፤ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ እና ወጪውን መቀነስ እንዳለበት ይመክራሉ።

“የተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ ሁከቶች አጋጥመውታል። ለምሳሌ የኮቪድ ወረርሽኝ እና ከግጭት። መንግሥት ያወጣቸው ብዙ ወጪዎች አሉ። ወጪዎቹ ከሚቀሩ የዋጋ ግሽበት ይሻላል በሚል እሳቤ እንጂ ብር መልቀቁ የዋጋ ንረት እንደሚያመጣ መንግሥት ሳያውቀው ቀርቶ አይመስለኝም።”

እንደመፍትሔ ‘ሊኩዊዲት ማኔጅመንት’ የተባለ ሐሳብ ያነሳሉ። በቀላል አማርኛ እንዲያስረዱን ጠየቅናቸው።

ብሔራዊ ባንኩ ገንዘብ ይሰበስባል። ይህ ማለት ባንኮች ያላቸውን ትርፍ ብር ለብሔራዊ ባንኩ በወለድ (ኢንተረስት) እንዲሰጡት ያደርጋል። ባንኮች ያላቸውን ትርፍ ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ ያስገባሉ።

“ይህ ሲሆን ሲስተሙ ውስጥ ያለው ገንዘብ ይቀንሳል ማለት ነው። የወለድ መጠኑን ከፍ በማድረግ ሰዎች ወጪ ከማድረግ ይልቅ ገቢ እንዲያደርጉ ማድረግ ይቻላል። የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር አንዱ መንገድ ነው” ሲሉ ይተነትናሉ።

ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ (አጠቃላይ አገራዊ ምርትን) ግን የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንጂ የአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደማይሆን ምሑራኑ ይስማማሉ።

ተሾመ (ዶ/ር) መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ፣ መስናን በመቀነስ፣ ሥራ በመፍጠር እና ኢንቨስተሮችን በመጋበዝ እንጂ ገንዘብ በማተም የኑሮ ውድነት መግታት አይችልም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው።

ቴድሮስ (ዶ/ር) ደግሞ “ዋጋ ንረቱን መቀነስ ቅድሚያ የሚሰጠው ከሆነ መንግሥት ወጪዎቹን ማቆም አለበት። ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን አቁሞ፣ እንዲያውም ባንኩ መሰብሰብ አለበት” ሲሉ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ይጠቁማሉ።