ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖል ፖግባ በተደራጀ የወሮበሎች ቡድን ዒላማ መሆኑን ተናገረ
ፖል ፖግባ በተደራጀ የወሮበሎች ቡድን የዝርፊያ እና የማስፈራሪያ ዒላማ መሆኑን ገለጸ።
የጁቬንቱስ እና የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን አማካዩ እሑድ ዕለት በጠበቆቹ በኩል ባወጣው መግለጫ መሠረት ጉዳዩ ለባለሥልጣናት ሪፖርት ተደርጓል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው የፈረንሳይ ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ጀምሯል።
የፖግባወንድም ማቲያስ ቀደም ሲል ስለ ተጫዋቹ ሚስጥሮችን የያዙ ቪዲዮችን እንደሚለቅ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ተናግሯል።
ማቲያስ ፖግባ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሳይሰጥ መረጃው “ግዙፍ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
“[ቪዲዮዎቹ] የተደራጁ ወሮበሎች በፖል ፖግባ ላይ ከሚያደርሱት ዛቻ እና ዝርፊያ ተጨማሪ ናቸው” ብሏል መግለጫው።
"በጣሊያን እና በፈረንሳይ ያሉ አካላት ከአንድ ወር በፊት ተነግሯቸዋል። እየተካሄደ ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ምንም ተጨማሪ አስተያየት አይኖርም።"
ፖግባ እአአ በ2018 ከፈረንሳይ ጋር የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። በዘንድሮው የክረምት የተጫዋቾች ዝውውር ከማንቸስተር ዩናይትድ በነፃ ጁቬንቱስን ተቀላቅሏል።
ማቲያስ በቪዲዮዎቹ ላይ “መላው ዓለም፣ የወንድሜ ደጋፊዎች፣ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና ጁቬንቱስ፣ የወንድሜ የቡድን አጋሮች እና ስፖንሰሮቹ አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ይገባቸዋል” ብሏል።
መረጃዎቹ የፖግባ ወኪል የሆነችው ራፋዬላ ፒሜንታንም እንደሚያካትቱ ተናግሯል።