ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ኤፍ-16 ተዋጊ የጦር ጀት ለቱርክ እንዲሸጥ ፈቀደች
የአሜሪካ መንግሥት 23 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጡ 40 ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶች ለቱርክ በሽያጭ እንዲተላለፉ ፈቀደ።
ቱርክ ተዋጊ ጄቶቹን እንድትገዛ ፍቃድ የተሰጣት ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአባልነት ጥያቄን ከፈቀደች በኋለ ነው።
ቱርክ አዲስ ከምትገዛው 40 ኤፍ-16 ጀቶች በተጨማሪ አሁን በይዞታዋ ላሏት 79 ጀቶች ማሻሻያ ቁሳ ቁስም ትረከባለች።
ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ 40 ኤፍ-35 የጦር ጀቶችን ለግሪክ ለመሸጥ ከውሳኔ ስለመድረሱ ለኮንግረሱ አስታውቋል።
ግሪክ ለኤፍ-35 ጦር ጀቶች 8.6 ቢሊዮን ዶላር ትከፍላለች።
ስዊድን እአአ በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።
ስዊድን ለኩርድ ተገንጣዮች ድጋፍ ትሰጣለች በሚል ቱርክ ኅበረቱን የመቀላቀል ጥያቄዋን አዘግይታው ቆይታለች።
ቱርክ የጦር ጀቶቹን ለመግዛት ጥያቄ አቅርባ የነበረው እአአ 2021 ቢሆንም ለስዊድን ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሳትሰጥ በመቆየቷ የጦር ጀቶቹ ሽያጭም ዘግይቶ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በፊት ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ በቱርክ ፓርላማ አባለት ድጋፍ አግኝቶ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃንም ውሳኔውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል።
ከዚህ በኋላ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኤፍ-16 ጀቶች ሽያጭ መዘግየት እንዳያጋጥመው አሳስበው ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ መፈጸሟ ቱርክን በጥቁር ባሕር አካባቢ የምትገኝ ወሳኝ የኔቶ አባል አገር አድርጓታል።
የጦር መሳሪያ ዝውውር ፍቃድን ከሚሰጠው አራት አባላት ካሉት የኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ዶሞክራቴ ሴናተር ቤን ካርዲን “ቱርክ ኤፍ-16 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ለቀረበችውን ጥያቄ ፍቃድ የሰጠሁት ቱርክ የስዊድን ኔቶ አባልነትን በማጽደቋ ነው” ብለዋል።
“ነገር ግን መዘንጋት የሌለበት፤ በቀላሉ ከዚህ ውሳኔ ላይ አልደረስኩም” ብለዋል።
ዴሞክራቱ ሴናተር ቱርክ የሰብዓዊ መብት አያያዟን ማሻሻል ይኖርባታል ያሉ ሲሆን የሩሲያ መጠነ ሰፊ ወረራንም ለማስቆም አንካራ ሞስኮን ተጠያቂ ማድረግ አለባት ብለዋል።
ስዊድን የኔቶ አባል ለመሆን ላቀረበችው ጥያቄ ምላሽ ያልሰጠች ብቸኛ የኔቶ አባል አገር ሃንጋሪ ሆናለች።
ሃንጋሪም እንደ ቱርክ ሁሉ ፍቃዷን እንድትሰጠ የሚያደርጉ ለውጦች እየታዩ ነው።
በቅርቡም የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከስዊድን አቻቸው ጋር በቡዳፔስት ለውይይት ተቀጣጥረዋል።