ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ለተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ልምምድ ሲደረግ መድረክ ተደርምሶ በሰው ላይ ጉዳት ደረሰ
በአዲስ አበባ ዛሬ እሁድ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት ለተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ትርዒት ለማቅረብ ቅዳሜ ምሽት ልምምድ ላይ የነበሩ ልጆች ላይ መድረክ ተደርምሶ ጉዳት ደረሰባቸው።
ታዳጊዎቹ የሕዳሴውን ግደብ መጠናቀቅ ተከትሎ ለከተማዋ ነዋሪዎች እና ለተጋባዥ እንግዶች ትርዒት ለማቅረብ እየተዘጋጁ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናት ቁጥር እና የጉዳቱ መጠን ያልታወቀ ሲሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ ያሉት ነገር የለም።
ቢቢሲ ጉዳት የደረሰባቸው ልጆች የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ተወስደውበታል ከተባሉ ሁለት ሆስፒታሎች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ልጆቹ ልምምድ ሲያደረጉበት የነበረው መድረክ የተሠራው ከእንጨት እንደነበር የዓይን እማኞች ለቢቢሲ የገለፁ ሲሆን፣ አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ምሽት 2፡30 ገደማ ላይ በመስቀል አደባባይ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ትርዒት ለማቅረብ ሲዘጋጁ የነበሩት ልጆች ተማሪዎች ሲሆኑ ለበዓሉ ታዳሚዎች የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ለተከታታይ ቀናት ልምምድ ሲያደርጉ ነበር ተብሏል።
አደጋው የደረሰበት መድረክ ከእንጨት የተሠራ እንደነበር የተናገሩት የዓይን እማኞች በርካታ ሕጻናት ወድቀው ጉዳት እንደደረሰባቸው ጨምረው ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ታዳጊዎቹ ጉዳት ቢደርስባቸውም ዛሬ እሁድ ከማለዳው ጀምሮ ለመካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ዝግጅት ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተገኙበት በርካታ የከተማው ነዋሪ በታደመበት ተካሂዷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተገኝተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱን በማስመልከት ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በመዲናዋ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ አስተዳደር አስተናጋጅነት በዋነኛው የመስቀል አደባባይ በተካሄደው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ከከተባዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ንግግር አድርገዋል።
ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ማክሰኞ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ግድቡ በሚገኝበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የተለያዩ አገራት መሪዎች በተገኙበት ነበር።
የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ እሁድ መስከረም 4/2018 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የተገኙበት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።
በዕለቱ የወታደራዊ ትርዒቶች፣የሕጻናት መዝሙሮች እና ንግግሮች ተደርገዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበት የተገነባ ሲሆን፣ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 14 ዓመት ፈጅቷል።
ይህ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት አስፈላጊውን ወጪ በራሳቸው ሸፍነው መሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል።
የግድቡ የግንባታ ሂደት፣ ባለው ከፍተኛ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እና ከግብፅ ጋር ባለው ውዝግብ ምክንያት ምረቃው በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቷል።