ቻይና የአፍሪካ አገራት ምርቶች ወደ አገሯ ከታሪፍ ነጻ እንዲገቡ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቻይና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላት ከ53 የአፍሪካ አገራት በምታስገባቸው ምርቶች ላይ የተጣሉ ታሪፎችን ለማንሳት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።
ቻይና ይህንን ውሳኔዋን ያስታወቀችው የአፍሪካ አገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ሊያጋጥማቸው ይችላል በተባለባት ወቅት በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ስብሳባ ላይ ነው።
ላለፉት 15 ዓመታት ቻይና የአፍሪካ አገራት ከፍተኛዋ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2023 አፍሪካ ወደ ቻይና 170 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ልካላች።
ይህ የቻይና ውሳኔ የተገለጸበት በአህጉሪቱ እና በቻይና ሚኒስትሮች መካከል የተካሄደው ጉባኤ ባወጣው የጋራ መግለጫ ላይ፣ አንዳንድ አገራት የተናጠል ታሪፍ በመጣል "ያለውን የዓለም አቀፍ ንግድ እና ምጣኔ ኃብት ሥርዓት" ለማደናቀፍ እየሞከሩ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ የንግድ አለመግባባቶችን "እኩልነት፣ መከባበር እና የጋራ ጥቅምን" መሠረት ባደረገ ሁኔታ እንድትፈታ ጥሪ አቅርበዋል።
ቻይና የአፍሪካ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ የሆነ ዕድል ሰጥታ ተግባራዊ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት አገሪቱ "በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩ" በሚል ለይታ የታሪፍ ቅናሽ ካደረገችላው 33 የአፍሪካ አገራት ውሳኔ ጋር የሚያያዝ ነው።
የአሁኑ የቻይና ውሳኔ በአፍሪካ ውስጥ ዋነኛ የንግድ አጋሯ የሆኑትን ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያን የሚጨምር ይሆናል። ይህ ወደ ቻይና የሚገቡ የአፍሪካ አገራት ምርቶችን ከታሪፍ ነጻ የሚያደርገው እርምጃ መቼ እንደሚጀመር የተባለ ነገር የለም።
ከዚህ የታሪፍ ተጠቃሚነት የተገለለችው ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ኢስዋቲኒ ስትሆን፣ ምክንያቱም ቻይና የግዛቷ አካል አድርግ የምትቆጥራትን ታይዋን እንደ ነጻ አገርነት ዕውቅና በመስጠቷ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ቻይና ከፍተኛ መጠን ያላቸው ጥሬ ዕቃዎችን ከአፍሪካ ታስገባለች። በተለይ ደግሞ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከጊኒ የምታስገባቸውው ተጠቃሽ ናቸው።
የቻይና ተፎካካሪ የሆነችው አሜሪካ ባለፈው ሚያዝያ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በበርካታ አገራት ላይ የታሪፍ ጭማሪ አድርጋለች። ከእነዚህ መካከል ሌሶቶ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያን ጨምሮ በርካታ አገራት ከፍተኛ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
ይህ የአሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ተግባራዊ አይሆንም። ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር "በቀና ልቦና" ድርድር ለሚያደርጉ አገራት ተግባራዊነቱ ሊዘገይ እንደሚችል የንግድ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት ተናግረዋል።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት አሜሪካ 39.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአፍሪካ አስገብታለች። የተወሰኑት ምርቶችም አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት በፈቀደችው አጎዋ በተባለው ነጻ የንግድ ዝውውር መንገድ ከታሪፍ እና ቀረጥ ነጻ የገቡ ናቸው።















