አሜሪካ እና ቻይና የገቡበትን የንግድ ጦርነት ለማቆም ለምን አሁን ንግግር ጀመሩ?

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ዢ ፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ እና የቻይና የንግድ ጦርነትን ሊያስቆም የሚችል ንግግር በስዊዘርላንድ ተጀምሯል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ቻይና ላይ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ በተደረገው የመጀመሪያ ንግግር የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የንግድ ባለሥልጣናት ቅዳሜ ዕለት ተገናኝተዋል።

ቤጂንግ በፍጥነት አጸፋዊ ምላሽ በመስጠቷ ሁለቱ አገራት እርስ በርስ ታሪፍ በመጨመራቸው ውጥረት ነግሷል።

ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ስትጥል አንዳንድ አሜሪካ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች ላይ ደግሞ 125 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባቸዋል።

ሁለቱም ወገን ሌላውን የበለጠ ተስፋ የቆረጠ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክሩ ቆይተዋል።

አሁን ግን ወደ ክብ ጠረጴዛ ተመልሰዋል።

ለምን?

ገጽታን መጠበቅ

የታሪፍ መጣል አዙሪቱን ሁለቱም ወገኖች ለመስበር እንደሚፈልጉ ምልክት ሲያሳዩ ቆይተዋል። ማን ቀድሞ እጅ ይሰጣል የሚለው ነው ግልጽ ያልነበረው።

በሲንጋፖር አይኤስኢኤኤስ-ዩሱፍ ኢሻክ ተቋም ባልደረባ እና የአሜሪካ የንግድ ተደራዳሪ የነበሩት ስቴፈን ኦልሰን "ሁለቱም ወገኖች ከአቋማቸው ፈቀቅ ያሉ መሆናቸውን ማሳየት አይፈልጉም" ብለዋል።

"ንግግሮቹ እየተካሄዱ ያሉት ሁለቱም አገራት ወደ ሌላኛው ወገን እጅ የሰጡ ሳይመስሉ ወደፊት መሄድ እንደሚችሉ በመገመታቸው ነው።"

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት "ንግግሮቹ የተካሄዱት በዩናይትድ ስቴትስ ጥያቄ ነው" ብለዋል።

የንግድ ሚኒስቴሩ ደግሞ ለዋሽንግተን ውለታ አስመስሎ በማቅረብ "የአሜሪካን የንግድ ድርጅቶች እና የሸማቾች ጥሪዎችን" እየመለሰ ነው ብሎታል።

የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ "ኢኮኖሚያቸው እየፈራረሰ" በመሆኑ "ቢዝነስ ለመስራት የሚፈልጉት የቻይና ባለስልጣናት ናቸው" ብሏል።

"የጀመሩት እነሱ ናቸው አሉን? ደህና ወደ ኋላ ተመልሰው መረጃዎቻቸውን ማጥናት ያለባቸው ይመስለኛል" ሲል ትራምፕ ከዋይት ሐውስ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

በንግግሩ ወቅት የቻይናው መሪ ሩስያ ተገኝተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግግሮቹ እየተቃረቡ ሲሄዱ ግን ፕሬዚዳንቱ የበለጠ ዲፕሎማሲያዊ መንገድን በመምረጥ "ሁላችንም ጨዋታዎችን መጫወት እንችላለን። የመጀመሪያውን ፍላጎት ማን አሳየ? ማንስ ፍላጎት አላሳየም የሚለው እዚህ ግባ አይባልም። ዋናው ነገር በዚያ ክፍል ውስጥ የሚወሰነው ነገር ብቻ ነው" ሲሉ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ጊዜው ለቤጂንግ ቁልፍ ነው ምክንያቱም ዢ ሞስኮን እየጎበኙ ያለበት ወቅት ነው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን ላይ የተቀዳጁትን ድል 80ኛ ዓመት ለማክበር በሞስኮ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር።

ዢ ከግሎባል ደቡብ ከተውጣጡ መሪዎች ጎን ታይተዋል። ቻይና ሌሎች የንግድ አማራጮች እንዳላት ብቻ ሳይሆን ራሷን እንደ አማራጭ ዓለም አቀፍ መሪ እያቀረበች እንደሆነ ለትራምፕ አስተዳደር መልዕክት ለማስተላለፈ ነው።

ይህ ቤጂንግ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ስታመራ ጥንካሬን እንድታገኝ ያስችላታል።

ጫና መፈጠር ጀምሯል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ታሪፉ አሜሪካን የበለጠ ያጠናክራል ብለው አጥብቀው ተከራክረዋል።

ቤጂንግ ደግሞ "እስከ መጨረሻው ለመታገል" ቃል ገብታለች። እውነታው ግን ቀረጡ ሁለቱንም አገራት ጎድቷል።

በቻይና የሚገኙ የፋብሪካ ምርቶች አሽቆልቁለዋል ሲል የአገሪቱ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ሳምንት በዜና ማሰራጫው ካይክሲን የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የአገልግሎት ሰጪዎች እንቅስቃሴ ካለፉት ሰባት ወራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ቢቢሲ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ቻይናውያን ላኪዎች በታሪፍ ጭማሪው ከመጎዳታቸውም በላይ ምርቶቻቸው በመጋዘኖች ውስጥ እየተከማቹ ነው። ከአሜሪካ ውጭም ገበያ እያፈላለጉ ነው።

"[ለቻይና] ስምምነቱ ካለምንም ስምምነት የተሻለ እንደሆነ የተገነዘበች ይመስለኛል" ሲሉ በሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የምሥራቅ እስያ ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር የሆኑት በርት ሆፍማን ተናግረዋል።

"ስለዚህ 'እሺ' እነዚህ ንግግሮች እንዲቀጥሉ ማድረግ አለብን'" ብለዋል።

እናም በቻይና በድምቀት የሚከበረው የላብ አደሮች ቀን ሲጠናቀቅ የቤጂንግ ባለስልጣናት ለመነጋገር ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ወስነዋል።

በሌላ በኩል በታሪፍ ፉክክሩ ምክንያት የተፈጠረው ጫና የአሜሪካን ኢኮኖሚ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቀንስ አድርጓል።

በተለይ በቻይና በተመረቱ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች በጣም ስጋት ገብቷቸዋል።

በሎስ አንጀለስ የሚገኝ የአሻንጉሊት ኩባንያ ባለቤት ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የአቅርቦት ሰንሰለቱን አጠቃላይ ሁኔታ እየተመለከቱት ነው።"

የአሜሪካ ሸማቾች ጫናው እንደሚሰማቸው ትራምፕም አምነዋል።

የአሜሪካ ልጆች "ከ30 አሻንጉሊቶች ይልቅ ሁለት አሻንጉሊቶች ሊኖራቸው ይችላል" ሲሉ በዚህ ወር የካቢኔ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

"ሁለቱ አሻንጉሊቶችም ከወትሮው በሁለት ዶላር የበለጠ ዋጋ ሊኖራቸው ይችላል" ብለዋል።

የትራምፕ ተቀባይነትም በዋጋ ንረት እና ሊከሰት ይችላል በሚባለው የኢኮኖሚ መውደቅ ምክንያት አሽቆልቁሏል።

ከ 60 በመቶ በላይ አሜሪካውያን ፕሬዝዳንቱ ታሪፍ ላይ አተኩሯል ብለዋል።

"ሁለቱም አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለሚሄደው የገበያዎች፣ የንግዶች እና የአገር ውስጥ ክልሎች ትንሽ ማረጋገጫ እንዲሰጡ ግፊት አለባቸው" ብለዋል ኦልሰን።

"በጄኔቫ ውስጥ ለሁለት ቀናት የሚደረጉ ስብሰባዎች ለዚሁ ዓላማ ያገለግላሉ።"

በቻይና የሚገኘው ትልቁ የአሻንጉሊት መሸጫ

የፎቶው ባለመብት, BBC/Xiqing Wang

ቀጥሎ ምን ይከናወናል?

ንግግሮቹ ተስፋዎችን ቢፈነጥቁም፣ ስምምነቱ ተግባራዊ ለመሆን ትንሽ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

ንግግሮቹ ባብዛኛው "መሰረትን የመንካት" ጉዳይ ናቸው ያሉት ሆፍማን፤ ይህ "የአቋም መለዋወጥ" ሊመስል ይችላል። በጥሩ መልኩ ከሄደ ደግሞ "ለወደፊት ንግግሮች አጀንዳ ያዘጋጃል" ብለዋል።

በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን እንደተከሰተው ሁሉ ድርድሩ ወራትን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ለሁለት ዓመታት ከሚጠጋ የታሪፍ መጣል ፉክክር በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና አንዳንድ ቀረጦችን ለማቆም ወይም ለመቀነስ በ2020 መጀመሪያ ላይ "የደረጃ አንድ" ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚያን ጊዜም ቢሆን የቻይና መንግሥት ለቁልፍ ኢንዱስትሪዎች የሚሰጠውን ድጎማ ወይም የተቀሩትን ታሪፎች የማንሳት ነገሮችን አላካተተም።

በእርግጥ ብዙዎቹ በጆ ባይደን ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመንም እንዳሉ ቆይተዋል። የትራምፕ የቅርብ ጊዜ ታሪፎች በእነዚያ የቆዩ ክፍያዎች ላይ የተጨመሩ ናቸው።

በዚህ ጊዜ ሊፈጠር የሚችለው "የደረጃ አንድ ስምምነት በስቴሮይድ ላይ" ነው ብለዋል ኦልሰን።

ይህ ማለት ከቀደምት ስምምነት አልፈው ዋና ነጥቦችን ለመፍታት ይሞክራል።

ይህም ዋሽንግተን ቻይና እንድትቆጣጠረው ከምትፈልገው ሕገወጥ የፌንታኒል ንግድ ጀምሮ ከሞስኮ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያካታት ነው።

ይህ ሁሉ ግን ከመስመሩ የራቀ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ኦልሰን አክለውም "የዩናይትድ ስቴትስ-ቻይና የንግድ ግንኙነትን የሚያበላሹት ስርአታዊ አለመግባባቶች በቅርቡ አይፈቱም።"

"ጄኔቫ 'ስለግልጽ ውይይቶች' እና ንግግር የመቀጠል ፍላጎትን በተመለከተ መግለጫዎችን ብቻ ታዘጋጃለች።"