የጋቦን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሃላ ፈጸሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በጋቦን መፈንቅለ መንግሥት የፈጸመው ወታደራዊ ጁንታ መሪ የሆኑት ጀነራል ብሪዝ ኡንጉማ የአገሪቱ ግዚያዊ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሃለ ፈጸሙ።
ጄኔራል ብጊዝ ኡሊጊ ኡንጉማ በቅርቡ ተካሂዶ በነበረ ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ ተደርጎላቸው የነበሩትን አሊ ቦንጎን በኃይል ከመንበር አንስተው ስልጣን የተቆጣጠሩት ባለፈው ረቡዕ ነበር።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የአገሪቱ ዜጎች ለጦር ጀነራሉ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በቃለ መሃላው ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልዩ ጠባቂና ረዳት የነበሩት ጀነራል ብጊዝ ኡንጉማ የጋቦን ግዚያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ምርጫ እስኪከናወን አገር እንዲመሩ ነው ይባል እንጂ ልክ እንደ የቦንጎ ቤተሰብ ስልጣን ላይ የሙጥኝ ይላሉ የሚል ስጋት አለ።
የቦንጎ ቤተሰብ ምዕራብ አፍሪካዊቷን ጋቦንን ለ55 ዓመታት መርቷል። የአሊ ቦንጎ አባት ኦማር 41 ዓመታትን በስልጣን ያሳለፉ ሲሆን እአአ 2009 ላይ ሕይወታቸው ሲያልፍ በልጃቸው አሊ ቦንጎ ተተክተዋል።
ዛሬ ግዚያዊ ፕሬዝዳንት ተብለው የተሾሙት ጀነራል ኡንጉማ ለአሊ ቦንጎ ቅርብ ከመሆንቸው የተነሳ የቅርብ ዘመድ ተደርገው ይታሰቡ ነበር።
ጀነራሉ አሊ ቦንጎን በቁም እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ካሉበት ሆነው በለቀቁት የይድረሱልኝ ቪዲዮ “ወዳጆቼ በሙሉ፣ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አልገባኝም። በዓለም ላይ ያላችሁ ወገኖቼ በሙሉ፣ እባካችሁ ድምጽ ሁኑኝ!” ሲሉ ተማጽነዋል።
ይህን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ሊብረቪል ከፍተኛ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ድምጹ ግን ‘እንኳንም ከእርስዎ ተገላገልን’ የሚል ሆኗል። የጋቦን ወጣቶች በዋና ከተማና ሌሎች ከተሞች ፈንቅለው በመውጣት በደስታ ሲጨፍሩ አድረዋል።
ዛሬ ሰኞ በነበረው ስነ-ስርዓት የጦር ጀነራሉ ወታደራዊ ትዕይነት ተካሂዶላቸው በጋቦን መዲና ሊብረቪል በሚገኘው ቤተ-መንግሥት ቃል መሃላ ፈጽመዋል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ ከዚህ ቀደም በአሊ ቦንጎ ከስልጣን የተወገዱ ሚንስትር መታየታቸው ጋቦናውያንን አስደንቋል።

ጋቦን ባለፉት ሦስት ዓመታት በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከነበሩ እና መፈንቅለ መንግሥት ከተፈጸመባቸው ስድስተኛዋ አገር ሆና ተመዝግባለች። ባለፈው ዓመት በቡርኪናፋሶ ሁለት ጊዜ፣ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በኒጀር፣ በአውሮፓውያኑ 2021 ደግሞ በጊኒ እንዲሁም በማሊ ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥቶች ነበሩ።
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ጋቦን ከአፍሪካ ኅብረት የታገደች ሲሆን መፈንቅለ መንግሥቱም በፈረንሳይ እና በተባበሩት መንግሥታት ውግዘት ገጥሞታል።
የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበረችው ጋቦን በአፍሪካ በነዳጅ ሃብት ከታደሉ ጥቂት አገራት አንዷ ናት። ይሁንና ሕዝቡ በከፍተኛ ድህነት ሲንከላወስ ነው የኖረው።
ጋቦን በምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ ሲሆን ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ 2.4 ሚሊዮን ብቻ ነው።












