ከ60 ዓመታት በላይ ብረት ሳጥን ውስጥ በተገጠመ መተንፈሻ የኖረው ፖል አሌክሳንደር

ፖል አሌክሳንደር

የፎቶው ባለመብት, GoFundMe

ፖል አሌክሳንደር ገና የስድስት ዓመት ሕፃን ሳለ ነው ሰውነቱ ብረት ውስጥ ሆኖ ጭንቅላቱ ብቻ ብቅ ብሎ ያገኘው።

እንዲህ ጠፍሮ የያዘው ነገረ ምን እንደሆነ ለማወቅ መንቀሳቀስ አልቻለም። ድረሱልኝ ብሎ ለመጮህ ሲሞክር ነው ድምፅ እንደሌለው ያወቀው።

ፖል ከልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ቢያገግግም ሰውነቱ የመንቀሳቀስ ችግር አይደለም የገጠመው። ድንገተኛ ቀዶ ህክምና ካደረገ በኋላ ነው ከብረት የተሠራ ሳንባ ካልተገጠመለት በቀር መተንፈስ አንደማይችል የተረዳው።

በቅርቡ በ78 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የለተየው ፖል ከሰባት አሥርታት በላይ የኖረው ብረት ውስጥ ነው። ሌሎች የብረት ሳንባ የተገጠመላቸው ሰዎች ይህን ያህል ዘመን አልኖሩም።

እና ፖል ከመሰሎቹ የሚለው ምንድነው? እንዴትስ ይህን ሁሉ ዘመን በብረት ሳንባ ሊኖር ቻለ?

ፖሊዮ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20 ክፍለ ዘመን መባቻ በርካታ ሕፃናትን ያዳረሰ ወረርሽኝ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1952 በአሜሪካዋ ቴክሳስ ፖል እና ሌሎች ሕፃናት በዚህ በሽታ ምክንያት ሆስፒታሎችን ሞልተውት ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በፖሊዮ ከተያዙ 200 ሕፃናት መካከል አንዱ ሊድን የማይችል የሰውነት መሽመድመድ ያጋጥመዋል።

ከእነዚህ መካከል ለ5 አስከ 10 በመቶ የሚሆኑት የመተንፈሻ ጡንቻቸው ከተነካ ሊሞቱ ይችላሉ።

ዕጣ ፈንታ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፖል ሁለት ዓመት ያህል ሆስፒታል ውስጥ ከቆየ በኋላ ዶክተሮች ዕጣ ፈንታው ያሳስባቸው ጀመር።

ይሄኔ ነው ቤተሰቦቹ ከብረት ለበሱ ሳንባው ጋር ወደ ቤት ይዘውት ለመሄድ የቆረጡት። ይህን ያደረጉት እዚህች ምድር ላይ የቀረችውን ጊዜ በሰላም እንዲያሳልፍ በሚል ነበር።

ነገር ግን ከዛሬ ነገ ሊሞት ይችላል የተባለው ፖል ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለስ ጭራሽ እየጠነከረ መጣ።

በሞተር የሚንቀሳቀሰው የብረት ሳንባ ከሲሊንደር አየር ተቀብሎ ለበሽተኛው ሳንባ በማቀበል ነው የሚሠራው። ይህ ሞተር የሚሠራው በኤሌክትሪክ ሲሆን፣ የሚበራው መብራት ሲቋረጥ በእጅ እየተገፋ ሊሠራ ይችላል።

በአካባቢው መብራት ሲጠፋ የፖል ጎረቤቶች እየመጡ ያግዛሉ። የፖል አባት ፖል እርዳታ ሲሻ የሚጠራበት መሣሪያም አዘጋጅቷል።

ታናሽ ወንድሙ ፊሊፕ ለቢቢሲ ሲናገር ቡችላ ይሰጥሀል ሲባል እየጎበዘ በመምጣት ማሽኑን እንዴት መጠቀም እንዳለበት እየተረዳ መጣ ይላል።

“ምናልባት አተነፋፈሱን አላውቅበት ይሆናል ብሎ ይፈራ ነበር። ነገር ግን ሦስት ደቂቃ መቆየት ከቻልክ ቡችላ ይሰጥሀል” ተብሎ እንደነበር በዚያ እንደለመደ ወንድሙ ይናገራል።

በልብ መተማመኑ እየጨረ አቅሙም አየጠነከረ ሲመጣ ከብረት ለበሱ ሳንባ እርዳታ ውጪ ብዙ ደቂቃዎችን በራሱ መተንፈስ መልመድ ጀመረ። ይህ ሲሆን ተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ላይ ሆኖ በመውጣት ከጓደኞቹ ጋር እንዲጫወት ተፈቀደለት። ሲደክመው ግን ወደ ብረት ሳንባው መመለስ አለበት።

“ለእኔ እንደማንኛውም ወንድም ነበር። እንጣላለን፤ አንጫወታለን፣ እንዋደዳለን፣ እንጨፍራለን፤ ወደ ኮንሰርት እንሄዳለን” ይላል ፊሊፕ።

ፖል ቤት ውስጥ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ኮሌጅ በማቅናት ሕግ አጥንቷል።

ፊሊፕ እንደሚያስታውሰው ፖል በኦስቲን ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ቆይታ “አስደናቂ” ነበር። ቤተሰቦቹ ፖል የብረት ሳንባውን ይዞ ወደ ኮሌጅ እንዲሄድ አገዙት። ከዚያ በኋላ ግን እነሱ ሲመለሱ እሱ ቀረ።

“ሥራዬ ብሎ የሚያግዘው አልነበረም። የዶርም እና የክፍል ጓደኞቹ አንዳንዴ ያግዙታል። ዊልቼሩን እየገፉ ወደ ክፍል ይወስዱታል” ሲል ፊሊፕ ያስታውሳል።

ፖል ሕግ አጥንቶ ከተመረቀ በኋላ ሥራ ጀመረ። ደንበኞች ወደ ቢሮው ሲመጡ እና የብረት ሳንባውን አይተው ሲደነግጡ ትዝ ይለዋል።

“እርግጥ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታይ ያስደነግጣል። ሙሉ ሰውነትህ ብረት ውስጥ ሆኖ ጭንቅላት ብቻ ሲታይ ግራ ያጋባል። ብዙ ሰዎች ወንድሜን አይተው ሲደንግጡ ተመልክቻለሁ።”

ፖል የአዋቂነቱን ዘመኑን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ብቻውን ነው። መሠረታዊ የሆኑ እንደ መፀዳጃ ቤት መሄድ እና መጠጥ ማግኘት የመሰሉ ነገሮችን እንዲያገኝ የሚረዱት ሰዎች አልነበሩም።

ፖል እና ወንድሙ ፊሊፕ አሌክሳንደር

የፎቶው ባለመብት, Philip Alexander

እርዳታ

ፖል በእጅጉ እርዳታ በሚያሻው ጊዜ ነው አንድ ሰው ወደ ሕይወቱ ብቅ ያለው።

በ2015 የፖል ብረት ለበስ መተንፈሻ መሣሪያ ማፍሰስ ጀመረ። ማሽኑ ብዙም የማይገኝ ስለሆነ የሚጠግን ሰው ማግኘት በጣም አዳጋች ነው። በዚያ ላይ በፍጥነት መገኘት አለበት።

ይሄኔ ነው ፖልና ቤተሰቦቹ የእርዳታ ጥሪ የለጠፉት። በጣም ብዙ ሰዎች ከዓለም ዙሪያ እናግዝሀለን የሚል ምላሽ ሰጡ።

ዳላስ ከሚገኘው የፖል አፓርታማ ብዙም ሳይርቅ ብሬዲ ሪቻርድስ አንድ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ሥራን የሚያከናውንበት መጋዘን አለው።

ሪቻርድስ መጋዘን ውስጥ ሁለት የብረት መተንፈሻዎች ነበሩት። ሪቻርድስ የፖልን ማሽን ወስዶ አንዳንድ መለዋወጫ ራሱ ሠርቶ የተቀረውን ደግሞ መጋዘን ውስጥ ከነበሩት ጠጋግኖ መለሰለት።

ነገር ግን በዚያኑ ቀን ምሽት ፖል ደውሎ ማሽኑ እየሠራልኝ አይደለም በማለት ለሪቻርድስ ነገረው። ሪቻርድስ መጥቶ ሲመለከተው አንድ ብሎን መላላቱን አስተዋለ።

ሪቻርድስ ማሽኑን መልሶ እስኪጠግነው ድረስ ፖል አነስ ያለ መተንፈሻ መሣሪያ ቢኖረውም እንደ ትልቁ ማሽን አመቺ አይደለም።

ልክ እንደ ፖል ሌሎችም በፖሊዮ ምክንያት ሳንባቸው ላይ በደረሰው ጉዳት ተጨማሪ መተፈንሻ አድርገው ሕይወታቸውን ይገፋሉ።

ባለፈው ዓመት ፖል በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝጋቢ ድርጅት በብረት ሳንባ ለብዙ ዘመናት የኖረ የሚል ዕውቅና ተሰጥቶታል።

ፖል ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በ78 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።