እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ሕፃን ልጁን የታቀፈ አባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከደረሱ ወዲህ በየቀኑ በሚደርሱ ጥሰቶች እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እሁድ ጠዋት እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው የአየር ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የሲቪል መከላከያ እና የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በሰሜናዊ ጋዛ ድንኳን ላይ በተሰበሰቡ ሰዎች በደረሰ ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ፤ በደቡባዊ የሰርጡ ክፍል በሌላ ጥቃት ደግሞ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከሐማስ ጋር የተደረሰውን የተኩስ አቁም የጣሱ የሽብር ዒላማዎችን ማጥቃቱን እና በዋሻ ውስጥ ለውስጥ የእስራኤል ጦር ወደሚቆጣጠረው የሰርጡ አካባቢ የዘለቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ከደረሱ ወዲህ በየቀኑ በሚደርሱ ጥሰቶች እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።

የጋዛ ሲቪል መከላከል በአየር ጥቃቱ 11 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልፅ የአል ሺፋ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ከጥቃቱ በተጨማሪ 12ተኛው ሰው በተኩስ ልውውጥ መገደሉን ተናግረዋል።

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ ቢያንስ 600 ሰዎች ተገድለዋል ይላል።

በየካቲት ወር እስራኤል በጋዛ ባደረሰቻቸው አየር ጥቃቶች ቢያንስ 32 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የትናንቱ የእስራኤል ጥቃት ሁለተኛው የተኩስ አቁም ስምምነት ምዕራፍ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት የተፈፀመ ነው።

ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ሰላም ቦርድ በሚል ስያሜ ይፋ ያደረጉት ተቋም በመንግሥታቱ ድርጅት ፈቃድ የጋዛን ድንበር የሚጠብቅ እና የሐማስን ትጥቅ መፍታት የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ ኃይል ያቋቁማል።

በዋሽንግተን የመጀመሪያውን ስብደባ በዚህ ሳምንት ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ቦርዱ ጋዛን የሚያስተዳድረውን መንግሥት ምስረታን እና የድኅረ ጦርነት ግንባታን ይከታተላል።

ከዚህ ስብሰባ አስቀድሞ ትራምፕ እሁድ ዕለት የቦርዱ አባላት ለፍልስጤን ግዛት መልሶ ግንባታ አምስት ቢሊዮን ዶላር ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል።

ትሩዝ ሶሻልስ በተባለው የማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ሐማስ ከዚህ ቀደም ፍልስጤም አገርነት ሆና ስትመሰረት ብቻ ትጥቅ እንደሚፈታ በመግለፅ መሳሪያ የመዘቅዘቁን ጉዳይ ውድቅ አድርጓል።

ባለፈው ሳምንት የሰላም ቦርዱ አባል የሆነችው ኢንዶኔዢያ ሁለተኛውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማሳለጥ ስምንት ሺህ ወታደሮቿን በጋዛ እንደምታሰማራ ተነግሯል።

ጦርነቱ እ.አ.አ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል በፈፀመው ጥቃት የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በዚህ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

እስራኤል ለጥቃቱ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ምላሽ የሰጠች ሲሆን፤ በዚህም እንደ ጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ 71 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።