በኢትዮጵያ "የዘፈቀደ ግድያዎች" እና "ኢሰብአዊ ቅጣቶች" መቀጠላቸውን የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት አመለከተ

መሳሪያ ታጥቆ የቆመ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እና ታጣቂዎች በዜጎች ላይ "ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች" መፈጸማቸውን የሚያሳዩ "ታማኝ መረጃዎች" መኖራቸውን የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ትግበራ ሪፖርት አመለከተ።

ሪፖርቱ መንግሥት በፀጥታ ኦፕሬሽኖች ወቅት "ስቅይት" መፈጸሙን እና በባለሥልጣናት ላይ "ተጠያቂነት" ማስፈን አለመቻሉን መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ገልጿል።

በዜጎች ላይ ተፈጽመዋል በሚል ከጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል የግሰለቦች "ስወራ"፣ "ስቅይት" እና "ኢሰብአዊ" ቅጣቶች ይገኙበታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 በላይ ሀገራትን እና ግዛቶችን በተመለከተ በየዓመቱ የሚያወጣው ይህ ሪፖርት ይፋ የተደረገው ማክሰኞ ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም. ነው።

ሪፖርቱ፤ በአውሮፓውያኑ 2024 የነበረውን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚዳስስ ነው። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ሪፖርት የሚያጠናቅረው እንደ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች እና መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያሉ "ታማኝ" የመረጃ ምንጮች በመጠቀም ነው።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ውስጥ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ "በርካታ ከሕግ እና ከፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች" መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እነዚህ ግድያዎች የተፈጸሙት "በግጭት አውድ" ውስጥ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ጠቅሷል።

በዋንኛነት በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ የዚህ አዋጅ ተግባራዊነት ቢያበቃም "በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች [የሚፈጸሙ] በደሎች ቀጥለዋል" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሪፖርቱ በሁለቱ ክልሎች "የተስፋፋ ሕገ ወጥ የንጹሃን እና የባለሥልጣናት ግድያ" መስተዋሉን የገለጸ ሲሆን፣ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የአማራ ፋኖ ታጣቂዎችም" እነዚህን ድርጊቶች ከፈጸሙት መካከል መሆናቸውን አስረድቷል።

በትግራይ ክልልም "የንጹሃን ግድያን ጨምሮ ከሕግ ውጪ ግድያዎች" መስተዋሉን ያሰፈረው ሪፖርቱ እነዚህ ድርጊቶች "በኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ ታጣቂዎች" የተፈጸሙ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጿል።

በተጨማሪም በምዕራብ ትግራይ "የተስፋፋ የንጹሃን ግድያ፣ ጅምላ የግዳጅ መፈናቀል፣ የዘር ማጽዳት፣ መድፈር" መፈጸማቸውን ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱ ጠቅሷል። ሪፖርቱ መረጃዎችን በመጥቀስ "የአማራ ታጣቂዎች እና ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችን" ተጠያቂ አድርጓል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት እና የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን በመጥቀስም፤ መንግሥት በሚያከናውናቸው "የፀጥታ ኦፕሬሽኖች" ወቅት "ስቅይት ውስጥ ተሳትፏል" ሲል ከስሷል።

ተመሳሳይ ምንጮች በመጥቀስም "የዘፈቀደ ወይም ሕገወጥ ግድያ፣ ስወራ፣ ስቅይት ወይም የጭካኔ ተግባር፣ ኢሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዞች ወይም ቅጣቶች" መፈጸማቸውን በሪፖርቱ አስፍሯል።

"ስቅይት በመፈጸም የሚከሰሱ የመንግሥት አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ አለመቻሉን" መረጃዎች እንደሚያሳዩ በመጥቀስም ወቅሷል።

መንግሥት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ "ባለሥልጣናትን ለመለየት እና ለመቅጣት የወሰደው እርምጃ የተገደበ" እንደሆነም በሪፖርቱ ተካትቷል።

ከእነዚህ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ መንግሥት "ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የተወሰኑ ባለሥልጣናት እንደተከሰሱ" መግለጹን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ እነዚህ እርምጃዎች በተመለከተ ያለው ዝርዝር መረጃ ትንሽ መሆኑን አስፍሯል።