አፕል 190 ሺህ ብር ያወጣል ያለውን ‘ኦጊዩሜንትድ ሪያሊቲ’ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ

አፕል ቪዠን ፕሮ የተሰኘው ምርት

የፎቶው ባለመብት, APPLE

አፕል የተባለው ግዙፉ አሜሪካዊ የቴክኖሎጂ ድርጅት ብዙ የተባለለትን ‘ኦጊዩሜንትድ ሪያሊቲ’ ይፋ አድርጓል።

አፕል ቪዠን ፕሮ የተሰኘው ምርት አፕል ከአሥር ዓመታት በኋላ የፈበረከው አዲስ ዕቃ ነው።

የአፕል ዋና ሥራ አስኪያጅ ቲም ኩክ አዲሱ ምርት “እውነተኛውን ዓለም እና ‘ቨርቹዋል ሪያሊቲን’ በፅኑ ያዋሃደ ነው” ብለዋል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ከዚህ ምርት ባለፈ የአይፎን ‘ኦፕሬቲንግ ሲስተም’ እና ማክቡክ ኤይር የተባለው ላፕቶፕ ማሻሻያዎች እንደተደረገላቸው ገልጧል።

ጭንቅላት ላይ የሚጠለቀው አዲሱ ምርት በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ለገበያ ይበቃል።

ዋጋው ደግሞ 3499 ዶላር ነው። በውጭ ምንዛሪ ሲሰላ ከ190 ሺህ ብር ከፍ ይላል።

ይህ ዋጋ ሌሎች ኩባንያዎች ገበያ ላይ ካዋሉት ምርት ዋጋ እጅግ ከፍ ያለው ነው።

የማርክ ዛከርበርግ ሜታ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ኩዌስት የተሰኘው ምርት ዋጋው 499 ዶላር ነው።

አዲሱ ምርት ይፋ የተደረገው ካሊፎርኒያ በሚገኘው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ካለ አንድ መዝናኛ ሥፍራ ነው።

ምርቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የአፕል የገበያ ዋጋ በስሱ ወረድ ብሎ ተስተውሏል።

ቢቢሲ አዲሱ ቴክኖሎጂ ይፋ ሲደረግ በሥፍራው ቢገኝም ምርቱን እስካሁን አልሞከረም።

አፕል ቪዥን ፕሮ ከሌሎች መሰል ምርቶች በቅርፁ ለየት ያለ ሲሆን የበረዶ ሸርተቴ የሚወዱ ሰዎች የሚያጠልቁትን ሰፊ መነፅር ይመስላል።

‘ኦጊዩሜንትድ’ አሊያም ድብልቅ ‘ሪያሊቲ’ የተባለ ስም የተሰጠው እውነተኛውን ዓለም ከቴክኖሎጂው አጣምሮ በመነፅር ውስጥ ስለሚያሳይ ነው።

ተጠቃሚዎች ይህን መነፅር መሰል ቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን ማሰስ፣ ፊልም መመልከት፣ ፅሑፍ መፃፍ ይችላሉ።

ነገር ግን ለዚህ ምርት ገበያው ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለው አጠራጣሪ ነው።

ሥራ አስኪያጁ ቲም ኩክ ንግግር ሲያደርጉ ደንበኞች ይህን ምርት ተጠቅመው “ዲጂታል ይዘቶችን ልክ ፊት ለፊታቸው እንዳለ ማየት፣ መስማት እና ልውውጥ ማድረግ ይችላሉ” ብለዋል።

መሣሪያው የሚንቀሳቀሰው በጣቶች፣ ዓይናንና ድምፅ ቅንብር ነው።

አፕል ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ ምርት ያስተዋወቀው በፈረንጆቹ 2015 አፕል ዋች [የእጅ ሰዓት] ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።