የወሲብ ቪድዮዎች ሾልከው የወጡበት ባልታዛር የስምንት ዓመት እስር ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, La Vice Press
የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ ዘመድ የሆነው እና ከወራት በፊት ሾልኮ የወጣ የወሲብ ቪዲዮን ተከትሎ መነጋገሪያ የነበረው ባልታዛር በገንዘብ ማጭበርበር ወንጀል የስምንት ዓመት እስር ተፈረደበት።
የቀድሞው የብሔራዊ ፋይናንስ ምርመራ ኤጀንሲ ኃላፊ የነበረው ባልታዛር ኢባንግ ኢንጎንጋ የመንግሥት ገንዘብ ለግል ጥቅሙ አውሏል ሲል ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
መልከ መልካም መሆኑን ተከትሎ "ቤሎ" በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ባልታዛር፣ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ሴቶች ጋር ወሲብ ሲፈጽም የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች ይፋ ከሆኑ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን እና የማኅበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከባልታዛር ጋር ወሲብ ሲፈጽሙ የሚታዩት ሴቶች ባለትዳር እና የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሚስቶች እና ዘመዶች የሆኑ ሴቶች መሆናቸው በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ቪዲዮዎቹ ሾልከው የወጡት ባልታዛር በእስር ላይ እያለ ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የተጭበረበረ ገንዘብ በካይማን ደሴቶች ውስጥ በተከፈተ በምሥጢራዊ አካውንት አስቀምጧል በሚል ተወንጅሏል።
ባልታዛር ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ገንዘቡ ለጉዞ አበል የተፈቀደ ነው ካሉ ሌሎች አምስት ባለሥልጣናት ጋር ሲሆን፣ የገንዘብ መጠኑም ከ9,000 እስከ 220 ሺህ ዶላር የሚደርስ ነው ተብሏል።
ባልታዛር በቁጥጥር ሥር የዋለው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን፣ የቀረበበት ክስ ደግሞ ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመመዝበር ካይማን ደሴቶች ላይ ወዳለ አካውንት አዛውሯል የሚል ነው።
ባልታዛር ከበርካታ ሴቶች ጋር ወሲብ ሲፈጽም የሚያሳዩ ቪድዮዎች ይፋ የሆነበት በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው ማዕከላዊ አፍሪካ አገር ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቀውን ሰው ለማጣጣል ነው የሚሉ ማላምቶችም ይሰጣሉ።
አገሪቷን በአውሮፓውያኑ ከ1979 ጀምሮ የመሩት ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ የባልታዛር አጎት ሲሆኑ፣ ፕሬዝዳንቱን ወደፊት ይተካሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች መካከልም ባልታዛር አንዱ ነበር።
ባልታዛር ብላክ ቢች ወደ ተባለው በዋና ከተማዋ ማላቦ ወደሚገኝ ስሙ የጠለሸ እስር ቤት የተላከ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስባቸው እዚህ እስር ቤት እንደሆነ ይነገራል።
የባልታዛር ስልኮች እና ኮምፒውተሮች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው የወሲብ ቪድዮዎቹ በይነ መረብ ላይ በስፋት መሠራጨት የጀመሩት።
ቪድዮዎቹ አንድ በአንድ የተለቀቁት በቴሌግራም ላይ ወሲባዊ ምሥሎችን በሚለጥፍ ገጽ አማካይነት ነበር።
ኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ደግሞ በስፋት የተሠራጩት በዋትስአፕ ገፆች ሲሆን የቪዲዮዎቹ ትክክለኛነት ግን እስካሁን አልተረጋገጠም።
ፍርድ ቤቱ በባልታዛር ላይ የእስራት ቅጣት ከማስተላለፉ በተጨማሪ የ220 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንደጣለበት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬስ ዳይሬክተር የሆኑት ሂላሪዮ ሚቶጎ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል - ኤኤፍፒ ዘግቧል።














