ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐማስ "ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ" ቢያቀርብም ስለ ጋዛ ለመነጋገር ተደራዳሪዎችን እንደሚልኩ ተናገሩ
እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን መልቀቅ ላይ ከሐማስ ጋር በቅርበት ለመነጋገር እሁድ ዕለት ልዑካኗን ወደ ኳታር ለመላክ ወሰነች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ሐማስ የኳታር፣ የአሜሪካ እና የግብፅ አሸምጋዮች ያቀረቡት ዕቅድ ላይ "ተቀባይነት የሌለው" ለውጥ ቢያደርግም ግብዣውን መቀበላቸውን ተናግሯል።
አርብ ምሽት ሐማስ ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ ለቀረበው ሀሳብ "አዎንታዊ ምላሽ" መስጠቱን እና ለድርድር መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ሆኖም አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን ቡድኑ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የሚደረገው ድርድር ካልተሳካ ግጭት እንደማይቀጥል ዋስትና ማግኘትን ጨምሮ ሌሎች ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
በጋዛ በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ በትንሹ 35 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብሏል።
በአል ማዋሲ አካባቢ የሚገኙ የመጠለያ ድንኳኖች በቦምብ ሲደበደቡ አንድ ዶክተር እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን በካን ዮኒስ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን የእርዳታ ማከፋፈያ ድርጅት ሠራተኞች የሆኑ ሁለት አሜሪካዊያን በካን ዮኒስ አካባቢ በተፈፀመ የእጅ ቦምብ ጥቃት ቆስለዋል ።
እስራኤል እና አሜሪካ ሁለቱም ለጥቃቱ ሐማስን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ቡድኑ ግን ምንም ያለው ነገር የለም።
ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የእስራኤል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ በተኩስ አቁሙ ምክረ ሃሳብ ላይ "ሐማስ ሊያደርጋቸው የሚፈልጋቸው ለውጦች" ፤ "በእስራኤል ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም" ብሏል።
ነገር ግን "ሁኔታው ላይ በተደረገው ግምገማ መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርበት ለመነጋገር እንዲሁም ታጋቾቻችንን ለማስመለስ፣ እስራኤል በተስማማችበት የኳታር ሃሳብ መሠረት፣ የቀረበውን ግብዣ ተቀብለው ድርድሩ አንዲቀጥል መመሪያ ሰጥተዋል። ተደራዳሪው ቡድን ነገ ወደ ሥፍራው ያመራል"።
ቀደም ሲል አንድ የእስራኤል ባለስልጣን ሐማስ በሰጠው ምላሽ መሠረት "የሚሰራ ነገር እንዳለ" ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር።
አሸምጋዮች በዶሃ በሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ላይ ቀሪ ክፍተቶችን ለመድፈን ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም።
በቅርብ ቀናት ውስጥ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል አለ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩን በቅርበት ይከታተላሉ።
አርብ ዕለት፣ ስለ ሐማስ ምላሽ ማብራሪያ ከማግኘታቸው በፊት፣ ቡድኑ በጎ ምላሽ መስጠቱ "መልካም" መሆኑን ጠቅሰው "በሚቀጥለው ሳምንት የጋዛ ስምምነት ሊኖር ይችላል" ብለው ነበር።
ሰኞ ዕለት ትራምፕ እና ኔታንያሁ ለመገናኘት ቀጠሮ ያላቸው ሲሆን በዚያን ወቅት ትልቅ መረጃዎችን ይፋ ለማድረግ አጥብቀው እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው።
በጋዛ በሐማስ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው እስራኤላውያን ዳግም የዚህን ድርድር ውጤት በጉጉት እና በጭንቀት ይጠብቃሉ።
ቅዳሜ ምሽት የታጋቾች ቤተሰቦች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው አገራቸው ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የሚያስችል አጠቃላይ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ግፊት ለማድረግ በቴል አቪቭ ሰልፍ አድርገዋል።
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እስራኤል ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ "አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን" ተቀብላለች ብለው ነበር።
በእነዚህ ቀናት ተደራዳሪዎቹ ጦርነቱን ለማቆም እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ዕቅዱ በሐማስ የተያዙ 10 በሕይወት ያሉ ታጋቾችን እና የ18 ሰዎችን አስከሬን ለማስለቀቅ በእስራኤል በእስር ላይ የሚገኙትን ፍልስጤማውያን እስረኞችን መልቀቅን ያካትታል ተብሎ ይታመናል።
በጋዛ እስካሁን 50 ታጋቾች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
ምክረ ሃሳቡ የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴን በማሳተፍ በቂ መጠን ያለው እርዳታ ወዲያውኑ ወደ ጋዛ እንደሚገባም ተካትቶበታል።
ውይይቱን በቅርበት የሚከታተሉ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን አርብ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐማስ በጋዛ የሚከፋፈሉ እርዳታዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአጋሮቹ ብቻ እንዲሆን እና የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ሥራውን ወዲያውኑ እንዲያቆም ጠይቋል።
ባለሥልጣኑ ሌላው ሐማስ የጠየቀው ማሻሻያ የእስራኤል ጦር መውጣትን የሚመለከት ነው ብለዋል ።
የአሜሪካ ምክረ ሀሳብ እስራኤል ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች የምትወጣበትን ያካትታል ተብሎ ይታመናል። ነገር ግን ባለሥልጣኑ ሐማስ የእስራኤል ወታደሮች በመጋቢት ወር መጨረሻ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመፍረሱ በፊት ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ሐማስ ድርድሩ ያለ ስምምነት ቢቋጭም እንኳ እስራኤል በአየር እና በምድር የምትፈጽመው ጥቃት እንድታቆም አሜሪካን ዋስትና እንድትሰጠው እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
አደራዳሪዎቹ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በምክረ ሃሳቦቹ ላይ ኮስተር ያለ ድርድር እንደሚደረግ ዋስትና እንደሚሰጡ እና አስፈላጊ ከሆነም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማራዘም እንደሚችሉ ይታመናል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ታጋቾቹ በሙሉ እስኪለቀቁ እና የሐማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስኪጠፋ ድረስ ጦርነቱ እንደማይቆም ተናግረዋል።
የቀኝ አክራሪዎቹ የካቢኔ አባላትም በቀረበው ስምምነት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልፀዋል።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 እስራኤላውያንን ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ዘመቻ ከፍቷል።
የጋዛ የሐማስ አስተዳደር የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 57,338 ሰዎች ተገድለዋል።